Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይበል የሚያሰኘው የአየር መንገዱ ዘመናይነት

እንደ ብሔራዊ ኩራት ከምንጠቅሳቸው አገር በቀል ኩባንያዎች ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀድመን እናነሳለን፡፡ ከ75 ዓመታት በላይ በበጎ አገልግሎቱ ስሙ የሚነሳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከአገር ውስጥ አልፎ በአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው የአፍሪካ ግንባር ቀደም ለመሆን በቅቷል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ አሠራሮችን እያስተዋወቀ በተወዳዳሪነት የዘለቀው አየር መንገዱ፣ በኢንዱስትሪው ትልቃ ስም በማትረፍ በዓለም የሚጠቀስ ተቋም ለመሆን በቅቷል፡፡ በየጊዜው የሚያገኛቸው ሽልማቶችም ለዚህ ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የዘመኑ ጥበብ የፈጠራቸውን አዳዲስ አውሮፕላኖችን አስመጣ ሲባል መስማት ደስ ይላል፡፡ የበረራ መስመሮቹን አበዛ ሲባልለት፣ ደንበኞቹን ለማርካት እንዲህና እንዲያ ያለውን ሥራ ተገበረ ሲባልም እንረካለን፡፡ የዓመቱ ምርጥ አየር መንገድ በመባል ተሸለመ የሚለውን ዜና መስማትም ደስታን ያጭራል፡፡ ኢትዮጵያን በአወንታዊነት የሚገልጽና የሚወክል፣ ዓለም አቀፍ ብቃት ያለው ተቋም ባለቤት መሆናችን ቢያኮራን አያስገርምም፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የተለያዩ ዕርምጃዎች መውሰዱም ያስመሰግነዋል፡፡ በቅርቡም ‹‹ወረቀት ለምኔ፤›› በማለት የወረቀት ንክኪ ሥራዎችን በማስቀረት ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት መዘርጋቱ፣ የዘመናዊነት አካሄዱን የሚያሳይ ነው፡፡

አየር መንገዱ ወረቀት አልባ ዘመናዊ ሥርዓት ለመፍጠር መነሳቱና ሥራውን መጀመሩም ቢደነቅም፣ የበለጠ ማድረግና መፈጸም የሚገባው ነገር ግን አይጠፋም፡፡  በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን፣ በመላው ዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ እንዲህ ያለው አገልግሎት መምጣቱ ተገቢ ነው፡፡

ወረቀት አልባው አገልግሎት የአየር መንገዱን ውስጣዊ አሠራር ይበልጥ ቀልጣፋ እንደሚያደርገው ይታመናል፡፡ አንድ ጉዳይ ለመፈጸም ሲፈለግ በተዋረድ የሚሰጡ ውሳኔዎች በኦላይን ይካሄዳሉ፡፡ የተንዛዛ ቢሮክራሲያዊ አሠራር ይገታል ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ በመልዕክት የሚደረጉ ምልልሶችና የደብዳቤ ልውውጦች ይቀንሳሉ፡፡ አንድ የሥራ ኃላፊ በቢሮው ከሌለና እሱ ካልፈረመበት በቀር ውሳኔው ተፈጻሚ ስለማይሆን ቢሮው እስኪገባ መጠበቅ፣ ቀጠሮ መስጠት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ሁሉም ነገር በኦላይን የተያያዘ በመሆኑ የሥራ ኃላፊው ባለበት ቦታ ሆኖ ይፈርማል፡፡ ኃላፊው የሉም ብሎ ማሳበብ ታሪክ ሆነ ማለት ነው፡፡

ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የሥራው ሒደት ማን ጋር ተንቀረፈፈ? ማን ያዘው? ማን አከናወነው ወዘተ. የሚለውንም ጥያቄ አዲሱ አሠራር ቁልጭ አድርጎ ስለሚመልስና ስለሚያሳይ ተጠያቂው ማን ነው? የሚለውንም በቀላሉ ይመልሳል፡፡ ስለዚህ አውጫጭኝ መቀመጥ ቀረ ማለት ነው፡፡ ይህ የአዲሱ አሠራር ጠቀሜታ በጥቂቱ ሲገለጽ ነው፡፡ ይህ ዘመናዊነት ምናለበት በመሬት አስተዳደርና በመሳሰሉት መሥሪያ ቤቶችም ቢተገበርና ከጣጣችን በገላገለን ያሰኛል፡፡ የአየር መንገዱ ጅምር ለሌሎችም ምሳሌያዊ ተግባር ነው፡፡ አዲሱ አሠራር ከአየር መንገዱ ደንበኞች ጋር የተያያዘም መሆኑ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ ከእኔ ጋር ስትበሩ ዘመናዊ አሠራሬን ተከተሉ የሚል አንድምታም ያለው ነው፡፡

‹‹ወረቀት ለምኔ›› ብሎ ካወጀ ወዲህ፣ የአየር መንገዱ ደንበኞች በእጅ ስልካቸው ወይም በኮምፒውተራቸው አማካይነት የጉዞ ትኬት እንዲቆርጡ ማድረግ የለውጡ አንድ አካል ነው፡፡ በእርግጥ በኦላይን የበረራ ትኬት መሸጥ ቀደም ብሎ ቢጀመርም፣ አዲሱን አሠራር ልዩ የሚያደርገው ግን ወረቀት አልባ መሆኑ ነው፡፡

ደንበኞች የበረራ ትኬት ለመቁረጥ ወደ ትኬት መሸጫ ቢሮዎች ማቅናት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ፡፡ አገልግሎቱን በቅጥልፍና ለማቅረብ ያለመ በመሆኑ፣ ከዚህ አሠራር ጋር አብረው የሚጠበቁ ለውጦችም ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ከአየር መንገዱ የበረራ ትኬት የሚፈልጉ ደንበኞችን የሚያስተናግዱት የትኬት መሸጫ ቢሮዎች አስፈላጊነት እየሟሸሸ መሔዱ ይታሰባል፡፡

ይህ በመሆኑም ደንበኞች አዲሱን አሠራር የቲኬት መሸጫ ቢሮዎች ሳያስፈልጉት መጠቀም ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ በተጨባጭም አየር መንገዱ ወደ ኤሌክትሮኒክ የትኬት ሽያጭ እንደተሸጋገረ ካሳወቀበት ጊዜ ወዲህ፣ የትኬት ቢሮዎችን አስፈላጊነት እያስቀረ መምጣቱ አያጠያይቅም፡፡ እነዚህ ቢሮዎች ሙሉ ለሙሉ ከተዘጉ ደግሞ ደንበኞች ወደዱም ጠሉ አየር መንገዱ ባመጣው ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ መሠረት መገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይህ ከሆነም አየር መንገዱ ዘመናዊ አገልግሎቱን ሁሉም ደንበኞቹ ያለ እክል ይጠቀሙበታል ማለት ስለማይቻል፣ አሠራሩ እክል ሊገጥመው ይችላልና፣ ወረቀት አልባ አገልግሎቱን ሁሉም ደንበኛ እንዴት መጠቀም እንደሚኖርበት የሚያስገነዝብ በቂ ትምህርት ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ የአየር መንገዱ ደንበኞች በተለይ የአገር ውስጥ በረራ ተጠቃሚዎች በእጅ ስልካቸው አማካይነት ትኬት ለመቁረጥ ወይም ሌሎች  መረጃዎችን በቀላል መንገድ ማግኘት ካልቻሉ፣ ግራ በመጋባት ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ከሆነም አገልግሎቱ ሊወሳሰብና መጉላላትን ሊያስከትል ይችላልና፣ አየር መንገዱ በዚህ ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ በቂ ሥራ ሠርቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ዘመናዊ አገልግሎቱ የሚሰምረው ተገልጋዮች ያለ ችግር መጠቀም መቻላቸው ሲረጋገጥ ጭምር ነው፡፡ ሁሉም ደንበኛ ሊገነዘበው በሚችል መልኩ መረጃ መስጠት ከአየር መንገዱ ይጠበቃል፡፡ አሠራሩ በሁሉም ኅብረተሰብ ዘንድ በቅጡ እስኪለመድ ድረስ ጎን ለጎን የተለመደውን አሠራር ማስኬዱ ክፋት የለውም፡፡

ደንበኞች በቀጥታ መረጃ ለማግኘት በሚጠቀሙበት የስልክ መስመር መረጃውን ለማግኘት ‹‹ደንበኞችን እያስተናገዱ ስለሆነ ትንሽ ጠብቁ፤›› ተብሎ ምላሽ ለማግኘት የሚወሰደው ጊዜ አንዳንዴ ያማርራል፡፡ ትንሽ ይጠብቁ ተብሎ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ አንዳንዴም ከዚያ በላይ መጠበቅ አለና፣ እንዲህ ያለውን የሚጎረብጥ አሠራር ቀልጣፋ ለማድረግ አየር መንገዳችን ብልኃት ያጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይችንም ነገር እግረ መንገዱን እንዲያያት ማስታወሱ መልካም ነው፡፡

ዘመናዊትን የታጠቀው አየር መንገድ፣ ደንበኞቹን የዘመናዊ አገልግሎቱ ተቋዳሽ ለማድረግ ይበልጥ ይሥራ፡፡ ይበርታ፤ ይልመድበት እንላለን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት