Sunday, April 14, 2024

አወዛጋቢው የኤርትራ ፕሬዚዳንት መግለጫና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አክብረት ጎይቶም (ስሟ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል) ተወልዳ ያደገችው በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ነው፡፡ በ1988 ዓ.ም. የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረች ታስታውሳለች፡፡ አባቷ በአስመራ ከተማ በመንግሥት ትምህርት ቤት መምህር፣ እናቷ ደግሞ የቤት እመቤት እንደነበሩ ትገልጻለች፡፡ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ጎበዝ ተማሪ እንደነበረችና ዶክተር ሆና አገሯን የማገልገል ሕልም እንደነበራት ትናገራለች፡፡

በ1989 ዓ.ም. ክረምት አዲስ አበባ የምትኖር ታላቅ እህቷ በመውለዷ ሳቢያ እሷን በሥራ ለማገዝ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን፣ እናትና አባቷ ሁለት ልጆች ብቻ እንዳላቸውም ትናገራለች፡፡ ያኔ እህቷ ስትወልድ እናትና አባቷ እህትሽን እስከምትጠነክርና ትምህርት እስከሚከፈት ድረስ በሥራ አግዣት በማለት ወደ አዲስ አበባ እንደላኳት በትዝታ ትገልጻለች፡፡ እናትና አባቷ በመኪና አሳፍረው ሲሸኙዋት የነበራቸው ስሜት አሁንም ድረስ ከውስጧ ሊወጣ እንዳልቻለ ታስረዳለች፡፡ አክብረት ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ በ1989 ዓ.ም. ክረምት ላይ የወለደች እህቷን ለመንከባከብ ከመጣችበት በኋላ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት በመከፈቱ ወደ አገሯ ተመልሳ መሄድ እንዳልቻለች በተሰበረ ልቧ ትናገራለች፡፡ የእናትና የአባቷ ሁኔታ ሰላሟን እንደነሳትም ታስረዳለች፡፡ ወደ ኤርትራ ለመሄድ ሙከራ ብታደርግም እንዳልተሳካላት ትገልጻለች፡፡

ይኼ ከላይ የቀረበው የአክብረት በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ በመኪና መምጣት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ቅርርብ ምን ያህል እንደነበር ለማሳየት አንድ ምሳሌ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ከመተሳሰር ባሻገር በደም ትስስር እንደነበራቸው ታሪክ ያስረዳል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ኤርትራ ድረስ በመሄድ ይሠራ እንደነበር፣ እንዲሁም አንድ ኤርትራዊ ኢትዮጵያ በመምጣት የሚሠራበት ጊዜ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን ይኼ የሁለቱ አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ከመቋረጡም በላይ፣ በመንግሥታቱ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት ገብተው በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከሁለቱም ወገን ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡

በ1990 ዓ.ም. በድንበር ይገባኛል ጥያቄ በሁለቱ አገሮች መካከል ተቀስቅሶ በነበረው ጦርነት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ከመጥፋቱና አካል ከመጉደሉ ባሻገር፣ አሁንም ድረስ በአጣብቂኝ ውስጥ ያሉ አገሮች ሆነዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት ሊያስገቡ የሚችሉ ምልክቶች እየታዩ ስለመሆናቸው የሚጠቁሙ ጉዳዮች እንዳሉ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ በተለይ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጥር 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአገሪቱ ሚዲያዎች የሰጡት መግለጫ፣ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት ግንኙነት ያለበትን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን ያመለክታል፡፡

አወዛጋቢው የኤርትራ ፕሬዚዳንት መግለጫና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ  

 

በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን የጂኦ ፖለቲካ ውጥረት እንዲባባስና ቀጣናው የአሸባሪዎች መናኸሪያ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ኤርትራ እጇ ረዥም መሆኑን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በተለያየ ጊዜያት ያወጣቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ኤርትራ ለረዥም ዓመታት የተመድ የማዕቀብ ሰለባ ሆናለች፡፡ ኢኮኖሚዋ ከመዳከሙ ዜጎች ለስደት እየተዳረጉ መሆኑን ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በአገሪቱ ለሚገኙ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ ግብፅ ኤርትራ ውስጥ የጦር ቀጣና እንደሌላት አስተባብለዋል፡፡ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ካይሮ አቅንተው በነበረበት ወቅት ከግብፅ አቻቸው ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ባደረጉት ምክክር፣ ሁለቱ አገሮች በቀይ ባህር አካባቢ ስለሚኖራቸው የጋራ የጦር ቀጣናና ሌሎች ጉዳዮች መምከራቸውን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይኼን መረጃ ቢያጣጥሉትም፣ ከግብፅ ጋር በፈጠሩት አዲስ ወታደራዊ አጋርነት የልብ ልብ ስላገኙ ነው በኢትዮጵያ ላይ ይኼን መሰል መግለጫ ለማውጣት የበቁት ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ ግብፅ ለኢትዮጵያ ተኝታ እንደማታውቅ ይናገራሉ፡፡ በቀጥታም ሆነ ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ኢትዮጵያን ለማዳከም ኤርትራና ግብፅ በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸውን የጠቆሙት አቶ ልዑልሰገድ፣ አሁን ያለው የፖለቲካ ትኩሳትም ያንን እንደሚያሳይ አውስተዋል፡፡

የኤርትራና የግብፅ ግንኙነት ምንድነው ተብሎ ቢመረመር ምንም ፋይዳ እንደሌለው፣ የሁለቱ ግንኙነት ኢትዮጵያን የመክበብ ወይም ደግሞ ከሱዳን ጋር ያላቸውን ውዝግብ አስመልክቶ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደማይችልና ከጀርባቸው ያለው ድብቅ አጀንዳና ዓላማ ኢትዮጵያንና አካባቢውን ማተራመስ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ተማሪና የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ አበበ ዓይነቴ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ኤርትራ አሸባሪዎችን አስታጥቆ ከመላክና ከመደገፍ የተለየ ተልዕኮ እንደሌላት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከሽብር ቡድኖች ጋር ባለው ንክኪ ሲወነጀሉ ነበረ በፊት ይፋዊ አልነበረም፡፡ አሁን ይፋ አድርገው ፊት ለፊት ለመምጣት ካልሆነ በስተቀር የተለየ ነገር የለውም፤›› ብለዋል፡፡

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ቱርክ በሱዳን ወታደራዊ ሠፈር እንዲኖራት ፍላጎት እንዳላት ጠቁመው፣ ለዚህ ጉዳይ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ነገር ግን ተሯሩጦ ስም መስጠትና መወንጀል እንደማያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የቀድሞው የኢዴፓ አመራርና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ ኢሳያስ ግብፅ ሄደው ያደረጉት ነገር ኢትዮጵያን ለማንበርከክና ሕዝቦቿን ለመጉዳት ካለ ተነሳሽነት እንደሆነ ጠቁመው፣ ይኼን ለማድረግ ደግሞ ከማንም መንግሥት ጋር ለመሠለፍ ወደ ኋላ የማይሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይኼ የሚያሳየው ደግሞ ግብፅ የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጉዳት ከኤርትራ ጋር ተሠልፋለች ወይ? ከተባለ መልሴ አዎ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ምንጩ ኢሕአዴግ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ላይ ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው ትኩረት ሰጥተው ከተናገሯቸው ጉዳዮች ሌላው ከኢሕአዴግ ጋር የትግል አጋር እንደነበሩ አስታውሰው፣ ነገር ግን አሁን እንደ ካዳቸውና የአሜሪካና የአውሮፓን አገሮች ራዕይ ለማስፈጸምና በቀጣናው ኃያል ሆኖ ለመታየት እንደሚሯሯጥ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግር መፍታት እንደተሳነው፣ እሳቸውም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመው ችግሩን ለማስተካከል ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጫቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ፣ ‹‹የእሳቸውን አስተየየት አልሞት ባይ ተጋዳይ ዓይነት አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰጡ አስገራሚ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዴሞክራሲም ሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታ ኤርትራ ውስጥ ካለው የተሻለ ነው ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ስለዴሞክራሲ ብናወራ ከኤርትራ ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ዴሞክራሲ አለ፡፡ ስለዚህ ስለኢትዮጵያ የሚተቹበት ምንም ዓይነት ሞራል የላቸውም፡፡ አስተያየት መስጠት ይችላሉ ወይ? የሚለው የመጀመርያው ጥያቄዬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ የምርጫ ሕግ አለ፡፡ ታቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ያደርጋሉ (የዕድገት ደረጃውን የጠበቀ ባይሆንም)፡፡ በተቃዋሚዎችና በመንግሥት መካከል ድርድር ይካሄዳል፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን የኤርትራው ፕሬዚዳንት መቼም አያዩም፣ አይሰሙም ብዬ አላስብም፡፡  ኤርትራ ውስጥ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የለም፡፡ ይኼ በሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ አስተያየት መስጠትና ኢሕአዴግን ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞክሩበት ሁኔታ ጥላቻቸውን ከመግለጽ ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ‹‹ከዚህ ቀደም ከሚሰጧቸው መግለጫዎች ዋና የተለየ ነገር አይኖረውም፡፡ የሆነ ኮሽታ በተሰማ ቁጥር መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ በሚል እሳቤ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ትርጉም ሊሰጠው የሚችልና ኢትዮጵያን ሊያሳስባት የሚችል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ኢትዮጵያን እየመራ ያለው መንግሥት የሕዝቡን ጥቅም ያስከበረ አይደለም፡፡ መስተካከል አለበት፡፡ እንዲስተካከል ደግሞ አስፈላጊውን ዕርምጃ እስከ መውሰድ እንሄዳለን፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው? ተብለው የተጠየቁት አቶ ሙሼ ሲመልሱ፣ ይኼ  በሌሎች አገሮች ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ መግባት ነው ብለዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለሻዕቢያ ድጋፍ ያደረገበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ በመጀመርያዎቹ ዓመታት፡፡ በኤርትራ ላይ የተፈጸመ ጥቃትን በኢትዮጵያ ላይ እንደተፈጸመ ጥቃት እንወስደዋለን፡፡ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ ጥቃት በኤርትራ ላይ እንደተቃጣ ጥቃት እንወስደዋለን የሚሉ ስምምነቶችን ተፈራርመው ነበር፤›› ያሉት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ኢሳያስ መንግሥት ከመሆኑ በፊትም ሆነ በኋላ የጠብ አጫሪነት ድርጊት የተላበሰ መሪ መሆኑን የሚጠቁም ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ምንጩ ኢሕአዴግ ወይም ሕወሓት እንደሆነ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ስለተናገሩት አቶ ልዑልሰገድ፣ ‹‹ልክ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ለችግሮች ተጠያቄ እኔ ነኝ፣ አመራሩ ነው ብሎ ያመነበት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ እሳቸው መጮሃቸው ነገሩን ያባባሱ መስሏቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተበታትና ማየት የሚፈልግ ሰው የሚናገረው ነገር አድርጌ ነው የምወስደው እንጂ ቦታ የሚሰጠው ነው ብዬ አላስብም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሙሼ ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻው በሻዕቢያና በኢሕአዴግ መካከል የነበረው ግንኙነት ውጤት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሻዕቢያና ኢሕአዴግ አብረው በነበሩበት ጊዜ ሻዕቢያ የፈጠረው አስተሳሰብና የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ የሄደበት መንገድ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ እየከፈለችው ያለው ዋጋ ውጤት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሻዕቢያ ሁልጊዜ የመጨረሻውን ጦርነት የማሸነፍ አጀንዳ ያለው መንግሥት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት የተፈጠሩት ግንኙነቶች በመርህ ላይ የተመሠረቱ አልነበሩም፡፡ ሻዕቢያ የባድመን ጉዳይ ወደ ጦርነት ለመውሰድ የሞከረበት ምክንያት፣ ኢትዮጵያን በጦርነት አሸንፋለሁ ብሎ በማሰቡ ነው፡፡ በቂ ድጋፍ በተለያየ መንገድ በማግኘቱ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያ መንግሥትን በኃይል እናስወግዳለን ብለው ያስተላለፉት መልዕክት የተስፋ መቁረጥ ምልክት እንደሆነ አቶ ልዑልሰገድ ጠቁመዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ያስወግዳል የሚል ግምት እንደሌላቸው፣ ይኼን መሰል መግለጫ መስጠቱ ከግብፅ ጋር ከፈጠሩት ትብብር በመነሳት እንደሆነና ይኼ ደግሞ የሚያዛልቅ አይደለም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀርቶ በመላው አፍሪካ ደረጃ በወታደራዊ አቅም የተሻለ ደረጃና ተክለ ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የ2 ዓመታት ጉዟቸው ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ እንደነበር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው መንገድ የተሳሳተ እንደሆነና የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች እንደለያያቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለምንድነው አሥር ጊዜ ሻዕቢያ እንዲህ አደረገን፣ እንዲያ እያደረጉ ነው የሚሉን? በጋራ እየሠራን እያለን ታንኮቻችንን አዲስ አበባ ድረስ ይዘን ስንሄድ ለምን ጣልቃ ገባችሁብን አይሉም ነበር?›› ሲሉ ይከሳሉ፡፡

አቶ ልዑልሰገድ በዚህ ሁኔታ ሁለቱ አገሮች ይግባባሉ ማለት ከባድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ለዚህ ሁሉ ችግርና መንስዔ የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ አስመራ ላይ ሆነው የሚፈቱትና የሚቋጥሩት ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ የልብ ልብ አግኝተው በቃላት መጨፈርና የኢትዮጵያን መንግሥት ጥፋተኛ አድርጎ የማቅረብ አባዜ ከኤርትራ መንግሥት የተሳሳተ ድምዳሜ የመነጨ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ አቶ ሙሼ ይኼ ክስ የትም ሊያደርስ እንደማይችል ጠቁመው፣ ‹‹ይኼ የሚያሳየው ሻዕቢያ ያልበሰለና ያላደገ መንግሥት መሆኑን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይኼን መሰል መግለጫ መስጠት በደም የተሳሰረን ሕዝብ ተለያይቶ እንዲኖርና ግንኙነት እንዲኖረው ካለመፈለግ የመነጨ እንደሆነ ተንታኞቹ ገልጸዋል፡፡ አቶ አበበ ይኼ ነገር አንድ ቦታ ላይ መቆም ካልቻለ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ በኩል በርካታ ሥራዎች መከናወን ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለሕዝቦች ግንኙነት ቅድሚያ እንደ ሰጠች፣ በኤርትራ መንግሥት በኩል ግን ቦታ እንዳልተሰጠው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በኤርትራ በኩል የኃይል አማራጮች ናቸው እየተመረጡ ያሉት፡፡ ሻዕቢያ የሕዝቡን ሳይሆን የመንግሥትን ፍላጎት ነው እያስከበረ ያለው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል ያለውን የፖለቲካ ልዩነት አስወግዶ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲፈጠርና አገሮችም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካዊ ጉዳዮች በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ልዑልሰገድ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል ያለው ችግር ሳይውል ሳያድር መፈታት አለበት ይላሉ፡፡

አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ሁለቱም መንግሥታት ለሁለቱ ሕዝቦች ጥቅም ሲባል ልዩነታቸውን ወደ ኋላ በማለት በመነጋገር መፍታት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ሙሼ ከዚህ የተለየ አስተያየት አላቸው፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ሻዕቢያን ወንበር ላይ እንዳስቀመጠው ሁሉ ይኼን ሊፈታው የሚችለው እሱ ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ኤርትራን በተመለከተ ሁለት ፖሊሲዎችን ስትከተል መቆየቷ ይታወሳል፡፡ የመጀመርያው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ ናቸው፡፡ በ2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ ያለውን አቋም ሊቀይርና የተለየ ፖሊሲ ሊከተል እንደሚችል በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገር ተሰምቶ ነበር፡፡ አዲሱ ፖሊሲ ምን እንደሆነ እስካሁን ባይታወቅም፣ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ጥላቻ ከመግለጽ አለመቆጠቡ ብዙዎችን ያሳስባል፡፡

የኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበረ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ባለፉት ሁለት ዓመታት ችግር ገጥሞታል፡፡ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት በርካቶች ሲሞቱ፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል፡፡ ከዚህ ቀውስ ውስጥ ለመውጣት ገዥው ፓርቲ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ በመግባት የተለያዩ ውሳኔዎች ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለአሥራ ሰባት ቀናት ባካሄደው ዝግ ስብሰባ ለተፈጠሩ ችግሮች ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድና ለተፈጠረው ችግርም መላ የአገሪቱን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ሥር የዋሉና የተፈረደባቸውን እስረኞች አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባል ለመፍታት መወሰኑና በዚህም እስረኞችም እየተፈቱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ድህነትን ለማስወገድ ብላ እየገነባች ያለው የህዳሴ ግደብ ከ60 በመቶ በላይ ግንባታው እንደተጠናቀቀ የሚታወቅ ሲሆን፣ የግድቡን ግንባታ ግብፅ በፅኑ ስትቃወመው ይሰማል፡፡ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በፊት የነበሩ መሪዎች በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እናውጃለን የሚል መልዕክት ሲያስተላልፉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ አብዱልፈታህ አልሲሲም ቢሆኑ ‹ናይል የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው› ሲሉ ከመደመጣቸው በላይ፣ ከኤርትራ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጠናከሩና እያደሱ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ቀውስ እንዳይፈጠር ያሠጋል፡፡ አወዛጋቢው የኤርትራ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያን መንግሥት ለመውቀስና ለመኮነን ያበቃቸው ጉዳይ፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ከግብፅ መንግሥት በተሰጣቸው ‹ከጎንህ ነን› በሚል አረንጓዴ ካርድ መነሻ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -