ትናንት ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. የቃና ዘገሊላ በዓልን ለማክበር በወጡ ወጣቶችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታወቀ፡፡ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ እንዳስታወቁት፣ የሞቱት ሰዎች ቁጥርና ምክንያቱ ምን እንደነበር ገና ይጣራል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች ከስፍራው እንዳስታወቁት፣ በዓሉን ለማክበር የወጡ ወጣቶች ፖለቲካዊ መልዕክት ያላቸውን ዘፈኖች ሲዘፍኑ እንደነበርና በፀጥታ ኃይሎች እንዲያቆሙ ቢነገራቸውም ለማቆም ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ግጭቱ ተቀስቅሷል፡፡
ግጭቱ ትናንትና የጀመረ ቢሆንም፣ በከተማው ግን እስካሁን ድረስ የሚሰማ የተኩስ ድምጽ እንዳለ የሪፖርተር ምንጮች ከስፍራው ገልጸዋል፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላትም በግጭቱ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ሐዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡