በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ትናንት ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. እና ዛሬ ጥር 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎችና የቃና ዘገሊላ በዓልን ለማክበር በወጡ ሰዎች መካከል በተከሰተው ግጭት እስካሁን የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አማረ ጎሹ ለአማራ ቴሌቪዥን በሰጡት የስልክ ማብራሪያ ገለጹ፡፡
አንድ የፀጥታ ኃይል አባልና ሌሎች ስድስት ሰዎች ሞተዋል ያሉት ኮማንደሩ፣ ሁለት የፖሊስ አባላት ከፍተኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 15 ሰዎች መሆናቸውንም ኮማንደሩ አስታውቀዋል፡፡
ኮማንደሩ አክለውም ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በነበረ ግጭት መኪኖች፣ ቤቶችና ሆቴሎች መቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ የፀጥታ ኃይል ግጭቱ እዚህ ደረጃ ሳይደርስ ለማስቆም ጥረት ሲደረግ የነበረ ቢሆንም፣ የተወሰኑ የበዓሉ ተሳታፊዎች የፖሊስ አባላትን አሳደው በድንጋይ ለመደብደብ ባደረጉት ሙከራ ይህን ያክል ጉዳት ሊደርስ ችሏል ብለዋል፡፡