የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ተቃውሞና ድምፀ ተአቅቦ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ፡፡
አዋጁ በ67 ተቃውሞና በ30 ድምፀ ተአቅቦ ፀድቋል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ በነበሩት አምስት የምርጫ ጊዜያት በተመረጡ የፓርላማ አባላት ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞና የድምፀ ተአቅቦ ቁጥር ነው፡፡
በዋናነት ተቃውሞ ሊያስነሳ የቻለው በአዋጁ የታክሲ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት የአሥረኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና መውሰድ በአስገዳጅነት የተደነገገ መሆኑ ሲሆን፣ ይህ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ አሁን በታክሲ ሥራ ላይ ተሰማርተው ያሉ ወጣቶችን የሚያፈናቅል ነው ሲሉም በርካታ አባላት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡