Thursday, June 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕይወት ሳይጠፋ ችግሮችን መፍታት ለምን ያቅታል?

ሰሞኑን በወልዲያ ከተማ የጥምቀት በዓል ሲከበር በተቀሰቀሰ ግጭት የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በርካታ ዜጎች በተለያዩ ሥፍራዎች በደረሱ ግጭቶች ሞተዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እያቃተ፣ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት በከንቱ እየተቀጠፈ ነው፡፡ ሕይወት ሳይጠፋ ችግሮችን መፍታት ለምን እንደሚያቅት ግራ እያጋባ ነው፡፡ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ወይም ብስጭታቸውን ሲገልጹ፣ የፀጥታ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው መረጋጋት በመፍጠር ነው፡፡ ችግር ባጋጠመ ቁጥር ጠመንጃ መተኮስ ሕይወት ከማጥፋት በተጨማሪ፣ በአገር ሰላምና መረጋጋት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የሰላም መደፍረስ፣ ከዚህ ዓይነቱ ድርጊት የመነጨ መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ መሆን ሲገባው፣ በተቃራኒ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሰዎች ሲገደሉ ሰላም ይደፈርሳል፣ አገር ይተራመሳል፡፡ እየሆነ ያለውም ይኼ ነው፡፡

በቅርቡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ፣ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ እስካሁን ለደረሰው ጥፋት ሁሉ የድርጀቱን አመራር ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባልም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት እንደሚፈቱ፣ ለዓመታት የዜጎች ማሰቃያ የነበረው ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተዘግቶ ሙዚየም እንደሚሆንና ለብሔራዊ መግባባት የሚረዱ የተለያዩ ጠቃሚ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱም ገልጸው ነበር፡፡ ለሕግ የበላይነት ትልቅ ትኩረት በመስጠትም በስፋት ማብራሪያ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ የእነሱ ቃል ከተሰማ በኋላ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬ ቢኖርም፣ በበጎ ጎኑ በመመልከት በተስፋ የመጠበቅ አዝማሚያ መታየቱም አይረሳም፡፡ ነገር ግን የወልዲያው ክስተት ሲሰማ ግን ድንጋጤ ነው የተፈጠረው፡፡ ጭልጭል ይል የነበረው ተስፋም ተሟጦ ንዴት ነው የተንፀባረቀው፡፡ በመንግሥት ላይ የነበረው እንጥፍጣፊ አመኔታም አብሮ ነው የጠፋው፡፡ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እየተቻለ የበለጠ ማወሳሰብ ለአገር አይጠቅምም፡፡

መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ለሚከናወኑ ማናቸውም ድርጊቶች ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለበት፡፡ በተለይ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል የፀጥታ ኃይሉን መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡ ማናቸውም ዓይነት የሕዝብ ጥያቄም ሆነ ቅሬታ በአግባቡ መስተናገድ ያለበትን ያህል፣ ሁከት ሲቀሰቀስም ከምንም ነገር በላይ በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት መድረስ የለበትም፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ሰላም ማስከበር ሲኖርባቸው በረባ ባረባው የሰው ሕይወት ሲያጠፉ ለሕግ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች በተፈጸሙ ግድያዎችና የማፈናቀል ድርጊቶች እጃቸው አለበት የተባሉም ሆኑ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች የዜጎችን ሕይወት ያጠፉ የመንግሥት አመራሮችና የፀጥታ ኃይሎች ሕግ ፊት ቀርበው ሊዳኙ ይገባል፡፡ ምትክ የሌለው የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ መቀጠል አይቻልም፡፡ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እየጠፋ ሁከት በተቀሰቀሰ ቁጥር ሰው መሞት የለበትም፡፡ የአንድም ሰው ሕይወት እንደ ዋዛ ሊጠፋ አይገባም፡፡ ሕዝብ ጥያቄ ሲያነሳም ሆነ ቅሬታውን ሲያቀርብ ምላሹ ኃይል መሆን የለበትም፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› አድርጌያለሁ ካለ በኋላ በአገሪቱ መፈጠር የነበረበት ብሔራዊ መግባባት መሆን ሲገባው፣ በተቃራኒው የበለጠ ቅራኔ የሚያባብሱ ድርጊቶች ይታያሉ፡፡ መታደስ ምን ማለት እንደሆነ ግራ እስከሚያጋባ ድረስ የኃይል ተግባራት ውጤት የሆኑ ሞት፣ የአካል ጉዳትና መፈናቀል በስፋት ታይተዋል፡፡ ሰሞኑን በወልዲያ ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ያጋጫቸው ጉዳይ ለሞት የሚያበቃ አልነበረም፡፡ በሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ላይ ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ ስሜትን መግለጫ ዘፈኖች ሲቀነቀኑ ዝም ብሎ ማሳለፍ ማንን ይጎዳ ነበር? በወቅቱ ፀጥታ በማስከበር ላይ የነበሩ ሰዎች ቃታ ከመሳባቸው በፊት ውጤቱን ቢያስቡ ኖሮ፣ የሰው ክቡር ሕይወት በከንቱ አይጠፋም ነበር፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ሥምሪት የዜጎችን ሕይወት ከአደጋ መታደግ መሆን ሲገባው ውጤቱ ሞት ከሆነ ሕዝብና መንግሥት እንዴት ይስማማሉ?  እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እየተደጋገሙ መንግሥት እንዴት አድርጎ ነው አገር የሚያስተዳድረው? ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እየተቻለ በየቦታው የሞት መርዶ እየተሰማ ከሕዝብ ጋር መታረቅስ ይቻላል ወይ? ይህ ጉዳይ በአፅንኦት ሊመከርበት ይገባል፡፡

ዜጎች ለሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች ከመንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሲያጡ ብስጭት ይፈጠራል፡፡ አገሪቱን ከሁለት ዓመታት በላይ እየናጣት ያለው ችግር የተፈጠረው በተጠራቀሙ ብሶቶች ምክንያት ነው፡፡ መንግሥት ሕዝብን ማዳመጥ ስለተሳነው ሁከቶች ተቀሰቀሱ፣ በርካቶች ሞቱ፣ አካላቸው ጎደለ፣ ተፈናቀሉ፡፡ ላጋጠሙ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሔ ተፈልጎ መሞት ይብቃ ቢባልም፣ አሁንም ክቡር የሰው ሕይወት እንደ ቅጠል ይበጠሳል፡፡ እዚህም እዚያም ግጭቶች ሲያጋጥሙ ተመጣጣኝ ዕርምጃ መወሰድ ሲገባ፣ ከመጠን በላይ የኃይል ዕርምጃ እየተወሰደ ብዙ አደጋ ደርሷል፡፡ መንግሥት ችግሩን በማመን ተገቢን ዕርምጃ እንደሚወስድ ቃል ቢገባም፣ የበለጠ ሲብስ እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡ ሌላው ቀርቶ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በስሜት ውስጥ ሆነው ካሁን በፊት ያጋጠሙ ጥፋቶች እንደማያጋጥሙ በተናገሩ ማግሥት፣ ሌላ የሞት መርዶ ሲነገር አገርን ያስደነግጣል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አዙሪት ውስጥ መውጣት እንዴት ያቅታል? ቃል የተገባው ተኖ ሲቀር እኮ ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው፡፡ ይህ አሳዛኝ ድርጊት በፍጥነት ታርሞ ሰላም ማስፈን ካልተቻለ ማንን ተስፋ ማድረግ ይቻላል? አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡

ይህች ታሪካዊት አገርና ይህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ አሁን የሚታየው አሳዛኝና አሳፋሪ ነገር አይመጥናቸውም፡፡ አገሪቷም ሆነች ይህ ኩሩ ሕዝብ በሥርዓት መተዳደር አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ መሆኑ በእርግጠኝነት ሊታመንበት ይገባል፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚቻለው የሕግ የበላይነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በእኩልነት የሚኖሩበት ሥርዓት ሲፈጠር ነው፡፡ ከብሔርተኝነት በላይ የጋራ አገር መኖር ሲረጋገጥ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት አገር መኖር የምትችለው፣ ሕዝቧ ዳር እስከ ዳር በገዛ አገሩ የባለቤትነት ስሜት ሲፈጠርለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዕውን መሆን የሚችለው የጋራ መግባባት መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ አንድነቷ ከብረት የጠነከረ አገር እንድትኖር ልጆቿ ልዩነቶቻቸውን ውበት አድርገው የጋራ ራዕይ ሊይዙ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ አስተዋይ ሕዝብ ልዩነቶቹ ሳይበግሩት በጠንካራ አንድነቱ ዘመናትን የዘለቀው ለአገሩ በነበረው ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡ ይህንን ኩሩ ሕዝብ ይዞ አገርን በዴሞክራሲና በብልፅግና ታላቅ ደረጃ ላይ ማድረስ ሲገባ፣ ነጋ ጠባ የሞት መርዶ መስማት ያሳምማል፡፡ ከእዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ አረንቋ ውስጥ በፍጥነት መውጣት ይገባል፡፡ ይህንን አስተዋይ ሕዝብ አይመጥንም፡፡ ለዚህም ነው ሕይወት ሳይጠፋ ችግሮችን መፍታት ለምን ያቅታል ተብሎ ደጋግሞ መጠየቅ የሚገባው!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢንቨስተሮች አደጋ ሲገጥማቸው ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለው መመርያ ተሻረ

በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች በኢንቨስተሮች ንብረት ላይ አደጋ ቢከሰት፣...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...

የባንኮች ብድር አሰጣጥ ፍትሐዊና ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በተቻለ መጠን ፍትሐዊ፣ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያማከለና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...