Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበወልዲያ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት የሰባት ሰዎች ሕይወት አለፈ

  በወልዲያ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት የሰባት ሰዎች ሕይወት አለፈ

  ቀን:

  • የከተማውን ከንቲባ መኖሪያ ቤት ጨምሮ የንግድ ተቋማት በእሳት ወድመዋል

  በወልዲያ ከተማ ቅዳሜ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ታቦት አጅበው ሲሄዱ በነበሩ ወጣቶችና በወቅቱ በሥምሪት ላይ በነበሩ የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት፣ የሰባት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡

  ተከስቶ በነበረው ግጭት ከሰባት ሰዎች ሕይወት ሕልፈት በተጨማሪ፣ የከተማዋን ከንቲባ መኖሪያ ቤት ጨምሮ የተለያዩ የንግድ ተቋማት በእሳት መውደማቸው ሲረጋገጥ፣ በግጭቱ ምክንያት የአንድ የፀጥታ አባልና የስድስት ግለሰቦች ሕይወት መጥፋቱም ታውቋል፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች እንደገለጹት፣ ግጭቱ በተከሰተበት ወቅት ወጣቶችን ለመበተን የፀጥታ ኃይሎች መሣሪያ ተጠቅመዋል፡፡

  ግጭቱ  ሲጀመር ዮሴፍ እሸቴ የተባለ የ13 ዓመት ታዳጊና ገብረ መስቀል ጌታቸው የተባለ ግለሰብ በፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

  ከግጭቱ በኋላ የክልሉ የፀጥታ አካላትና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከተማዋን ለማረጋጋት መሰማራታቸውን፣ የሰሜን ወሎ ዞን የፀጥታ ጉዳዮች መምርያ ኃላፊ አቶ አደራ ፀዳሉ ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

  በወቅቱ የፀጥታ ኃይሎች ግጭቱን ለማብረድ አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅመው እንደነበር፣ በግጭቱ የሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ የከተማዋ ፀጥታ ወደ አስከፊ ሁኔታ እንደተቀየረ፣ ከዚያም የተሰባሰቡ ወጣቶች የንግድ ተቋማትንና የግለሰቦች ቤቶችን ማቃጠል መጀመራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

  በእሳት ከተቃጠሉት መካከል የከተማዋ ከንቲባ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ አርሴማ ሆቴል፣ መቻሬ ሆቴል፣ ኃይላይ ሕንፃ፣ ማኅተመ ሕንፃና ሌሎች መኖሪያ ቤቶች እንዳሉበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የደረሰውን የንብረት ጉዳት በተመለከተ የዞኑ የፀጥታ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አደራ ገና እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ የክልሉ መንግሥት ሰባት እንደሆኑ ቢገልጽም፣ ቁጥራቸው ከእዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ይናገራሉ፡፡

  ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ እሑድ ጥር 13 ቀን 2010 ዓ.ም. የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወልዲያ በመሄድ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶችና ከዞኑ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላም የታሰሩ ወጣቶች እንዲለቀቁ መደረጉንና በከተማዋ መጠነኛ መረጋጋት እንደሰፈነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የከተማዋ ፀጥታ በመጠኑም ቢሆን መሻሻሉ ቢታወቅም፣ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ማክሰኞ ምሽት ድረስ አብዛኛዎቹ የንግድ ተቋማት አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም፡፡ በተለምዶ ማክሰኞ ተብሎ የሚታወቀው የገበያ ሥፍራ ውስን እንቅስቃሴ ብቻ እንደታየበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ኅብረተሰቡ ከተማዋ እንድትረጋጋ ዕገዛ እያደረገ መሆኑን አቶ አደራ አክለው ገልጸዋል፡፡

  ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በደረሰው አደጋ መንግሥት ማዘኑን ጠቁመው፣ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት ሳይጠፋ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ለዘላቂ ሰላም አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቅረብ እንዳለባቸው፣ የፀጥታ ኃይሎችም የሰው ሕይወት ሳይጠፋና አካል ሳይጎድል የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ በመገንዘብ የመፍትሔ አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የፀጥታ አካላት የጥምቀት በዓልን በሚያከብሩ ሰዎች ላይ ኃይል በመጠቀማቸው እንዳዘነ፣ እንዲሁም የተቃውሞ መፈክሮችንና ዘፈኖችን ስላሰሙ ብቻ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ በተከሰተው ግጭት የሞቱት ሰዎች ጉዳይ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አሳስቧል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...