Friday, February 14, 2025
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሮሚያ ክልል በአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ረቂቅ አዋጅ ላይ ለፓርላማ ያቀረበው የሕጋዊነት ጥያቄ...

የኦሮሚያ ክልል በአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ረቂቅ አዋጅ ላይ ለፓርላማ ያቀረበው የሕጋዊነት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

ቀን:

spot_img
  • ረቂቁ ባስቀመጠው የትምህርት ደረጃ ሳቢያ 67 ተቃውሞና 30 ተአቅቦ ቀርቦበታል

የኦሮሚያ ክልል በፌዴራል መንግሥት ተረቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ረቂቅ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊ  አለመሆኑን በመጥቀስ እንዳይፀድቅ በተደጋጋሚ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከፍተኛ ማሻሻያ ተደርጎ በፓርላማው ፀደቀ።

የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ረቂቅ አዋጁ በሕገ መንግሥቱ ለክልሎች የተሰጠውን ሥልጣን ከግምት ያላስገባና ለመተግበር አስቸጋሪ ሆኖ በመዘጋጀቱ ሊፀድቅ እንደማይገባው በመጥቀስ የሕግ ሰነዱን ላመነጨው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ እንዲሁም ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር እየተመለከተ ለነበረው የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አቤቱታውን በደብዳቤ በተደጋጋሚ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።

የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ካቀረባቸው የሕጋዊነት ጥያቄዎች መካከል ክልሎች በሕገ መንግሥት የተቋቋሙ ራሳቸውን የቻሉ መንግሥት ሆነው ሳለ፣ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ረቂቅ አዋጅ በአንቀጽ 2(18) ላይ የፈቃድ ሰጪ አካላትን ትርጓሜ ሲሰጥ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የዕውቅና ሰርተፊኬት የተሰጠው የመንግሥት አካል ማለቱ፣ የክልልን ሥልጣን ከግንዛቤ ያላስገባና ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረን ነው የሚለው በዋነኝነት ይጠቀሳል።

በአዋጁ አንቀጽ 6(1)(2) ደግሞ ባለሥልጣኑ የፈቃድ ሰጪ አካላት ማሟላት የሚገባቸውን መሥፈርት ያወጣል፣ በመሥፈርቱ መሠረት ፈቃድ ሰጪው መሥፈርቱን ስለመሟላቱ ተመልክቶ የዕውቅና ሰርተፊኬት ይሰጠዋል፣ ሰርተፊኬቱን ይሰርዛል፣ ያግዳል፣ በማለት የተቀመጠው ድንጋጌም በሕገ መንግሥት የተቋቋመን ክልል ሥልጣን በአዋጅ የተቋቋመው ባለሥልጣን የሚጋፋ ነው የሚል የሕጋዊነት ጥያቄም አንስቶ ነበር።  በሌላ በኩል የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ለፌዴራል መንግሥቱ ለብቻ የተሰጠ ባለመሆኑ፣ ክልሎች የአስፈጻሚ አካላትን በሚያቋቁምበት አዋጅ እንደ ተግባር ይዘው ሥራዎችን እያከናወኑ ባሉበት ሁኔታ ይህ አዋጅ እንዲህ መውጣቱ የክልልን ሥልጣን እንደመቀማት ስለሚቆጠር ከዚህ አንፃርም እንዲታይ ጠይቆ ነበር።

በአዋጁ አንቀጽ 8(6) የታክሲ አገልግሎት የአሽከርካሪዎች ሥልጣን በተመለከተ ባለሥልጣኑ የሚያዘጋጀውን ልዩ ሥልጠና በመውሰድ የምስክር ወረቀት መያዝ ያስፈልጋል ማለቱ፣ ከኦሮሚያ ክልል ስፋት አንፃር ይህ አገልግሎት በባለሥልጣኑ ብቻ እንዲሰጥ ወይም በባለሥልጣኑ በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረት አገልግሎት እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ፣ አገሪቱ ከምትከተለው የፖለቲካ ርዕዮት አንፃር ሥልጣን አንድ ቦታ እንዲሰበሰብ የሚያደርግ አዝማሚያ የሚታይበት በመሆኑ እርምት ሊደረግበት እንደሚገባም የክልሉ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጠይቆ ነበር።

ረቂቁን  በዝርዝር እንዲመለከትና የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ የተመራለት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በርካታ ወራት የፈጀ ምርመራ በረቂቁ ላይ ካከናወነ በኃላ፣ በኦሮሚያ በኩል ሲቀርብ የነበረውን የሕጋዊነት ጥያቄ ከግምት ያስገቡ ማሻሻያዎችን በረቂቁ ላይ በማድረግ የውሳኔ ሐሳቡን ለፓርላማው ጠቅላላ ጉባዔ ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. አቅርቧል። 

ፈቃድ ሰጪ ማለት በሕግ አግባብ የተቋቋመና በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ብቃቱ የተረጋገጠለት የመንግሥት ተቋም እንደሆነ በረቂቁ መቀመጡ፣ በክልል መንግሥታት የተቋቋሙ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮዎችን ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዕውቅና እንዲያገኙ ትርጓሜ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ባለሥልጣኑ ለክልል ተቋማቱ ውክልና ከመስጠት ውጪ በአስተዳደር እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ በግልጽ ተለይቶ ማሻሻያ ተደርጎበታል። በዚህም መሠረት ፈቃድ ሰጪ ማለት በሕግ አግባብ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጥ በሕግ የተቋቋመና ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ውክልና የተሰጠው፣ ማንኛውም የፌዴራል ወይም የክልል ትራንስፖርት ተቋም ወይም ማንኛውም  የመንግሥት ተቋም ነው ተብሎ ተሻሽሏል። 

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ለሚሰጡ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ እንደሚሰጥ፣ ፈቃድ እንደሚያድስና እንደሚሰርዝ በረቂቁ የሠፈሩ አገላለጾች እንዲወጡና ውክልና ይሰጣል ተብለው እንዲተኩ ቋሚ ኮሚቴው ማሻሻያ አድርጓል። በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙ የክልል ተቋማት በባለሥልጣኑ ዕውቅና እንዲንቀሳቀሱ ትርጉም የሚሰጥ አገላለጽ መሆኑን በምክንያትነት አስቀምጧል። ይሁን እንጂ በፌዴራል ደረጃ የሚሰጥ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫን በተመለከተ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የዕውቅና ሰርተፊኬት የመስጠት፣ የብቃት ማረጋገጫን የማገድና የመሰረዝ ኃላፊነት እንደሚኖረው ተደርጎ ተሻሽሏል። 

ታክሲ የማሽከርከር የብቃት ማረጋገጫን በተመለከተ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሚሰጠውን ልዩ ሥልጠና መመዘኛ መሥፈርት መሠረቶች ማሟላት እንዳለባቸው በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው፣ ከክልል ፈቃድ ሰጪ ተቋማት ዘርፉን የማስተዳደር ተግባር ጋር የሚቃረን በመሆኑ ማሻሻያ ተደርጎበታል። 

በዚህም መሠረት ለታክሲ አገልግሎት የተመደቡ ተሽከርካሪዎችን ማሽከርከር የሚቻለው የፌዴራሉ ባለሥልጣን በሚያወጣው መመዘኛ መሠረት፣ ከፈቃድ ሰጪ አካላት ልዩ ሥልጠና የወሰዱና የታክሲ ማሽከርከር ሰርተፊኬት የተሰጣቸው ተብሎ ተሻሽሏል። ታክሲ የማሽከርከር ፈቃድ ለማግኘትም አስረኛ ክፍል የትምህርት ደረጃን ማጠናቀቅና በአውቶሞቢል ወይም በሕዝብ ምድብ  ቋሚ የማሽከርከር ብቃት ማረጋገጫ ያለው መሆን እንደሚገባ አካቷል። 

ታክሲ ለማሽከርከር አሥረኛ ክፍልን ማጠናቀቅ አስገዳጅ ሆኖ መቅረቡ በምክር ቤቱ ከፍተኛ ሌላው የክርክር ርዕስ ነበር። በርካታ የምክር ቤቱ አባላት የትምህርት ደረጃ መሥፈርቱ ነባራዊ ሁኔታውን የሚገልጽ እንዳልሆነ፣ በአሁኑ ወቅት በታክሲ አሽከርካሪነት የሚተዳደሩ በርካታ ወጣቶችን ከሥራ የሚያፈናቅል መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል። በረቂቁ ላይ የማፅደቂያ ውሳኔ ሐሳብ ያቀረበው የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ የሕግ ሰነዱ የብቃት ማረጋገጫ የሚጠይቀው ዕድሜና የትምህርት ደረጃን የማሽከርከር ሙያ ከሚጠይቀው ክህሎት ጋር እንዲጣጣም ያደረገ፣ በአሁኑ ወቅት ከማሽከርከር ብቃት ማነስና በሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት እየደረሰ ያለውን የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን ገልጿል።

 በስተመጨረሻ በረቂቁ ላይ ድምፅ እንዲሰጥ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ካሳሰቡ በኋላ ኢሕአዴግና አጋሮቹ በተቆጣጠሩት ፓርላማ ታሪክ ያልታየ ክስተት ተስተውሏል። ረቂቅ የሕግ ሰነዱ እንዳይፀድቅ 67 የፓርላማ አባላት የተቃውሞ ድምፅ ሲሰጡ፣ ሌሎች 30 የምክር ቤቱ አባላት ደግሞ የተአቅቦ ድምፅ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ረቂቁ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ህወሓት ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ፈቃዱ ታገደ

-የቦርድ ትእዛዝ አክብሮ ካልተገኘ ከሶስት ወር በኋላ እንደሚሰረዝ ተገልጿል የምስረታ...

የአየር መንገዱን አሠራር ጥሰዋል በተባሉ የአዲስ አበባ ሽያጭ ቢሮ ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

- የሕግ ክፍሉ ክስ መመሥረት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች እየተመለከተ ነው...

የጋዛ ውዝግብ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የደቀነው ሥጋት

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማችና የቀድሞ የመካከለኛው ምሥራቅ የፖሊሲ...