Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰባት ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰባት ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

ቀን:

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ተማሪዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት፣ ሰባት ተማሪዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አዳነ ኃይሌ (ዶ/ር) ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በተፈጠረው ግጭት በሰባት ተማሪዎች ላይ ጉዳት በመድረሱ ወደ ሆስፒታል ተልከዋል፡፡

ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ሦስት ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው  እንደነበር፣ አሁን ግን ሁሉም ተማሪዎች የሕክምና ዕርዳታ ተደርጎላቸው ከሆስፒታል መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ከነበሩ ሦስት ተማሪዎች መካከል አንደኛው ከኦሮሚያ ክልል የመጣ እንደሆነና ሁለቱ ደግሞ የአማራ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተማሪዎች መካከል ለተፈጠረው ግጭት መንስዔው በሁለት የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች ተወላጆች ተማሪዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው፣ ግጭቱን ወደ ብሔር በመቀየር ከአንድ ሺሕ በላይ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች ከግቢ ለመውጣት መውጫ በር አካባቢ ደርሰው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በተፈጠረው ግጭት ሦስት ተማሪዎች ከፍተኛ የሚባል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ በሁለት ተማሪዎች መካከል የነበረውን አለመግባባት የብሔር መልክ እንዲይዝና ግጭቱ እንዲስፋፋ ያደርጉ የነበሩ ተማሪዎች፣ ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆነባቸውና ጉዳዩ ፖለቲካዊ ሆኖ እንዲወጣ የሚፈልጉ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት መገምገሙንም አስረድተዋል፡፡

ግጭቱን በፈጠሩ ተማሪዎች ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ ተወሰደባቸው የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ በፊት በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ከግምት በማስገባት እስካሁን ዕርምጃ እንዳልተወሰደ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የዚህን ችግር መንስዔና ወደፊት መወሰድ ስለሚገባው ዕርምጃ በተመለከተ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ ግጭቱን የፈጠሩና እንዲባባስ ሲያደርጉ የነበሩ ተማሪዎች የመለየት፣ እንዲሁም ችግሩን ሲያባብሱ የነበሩ ተማሪዎች የትምህርት ደረጃቸው ምን እንደሚመስል ሌሎች ዝርዝር ሥራዎችን እንዲያከናውን ተልዕኮ ተሰጥቶት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ለመውጣት መውጫ በር ድረስ ሄደው ከነበሩና አንድ ሺሕ ከሚጠጉ ተማሪዎች ጋር የዩኒቨርሲቲውና የዞኑ አመራር ውይይት እንዳደረገ፣ ተማሪዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን ምላሽ እንደሰጠ አክለው ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልል በሐዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በ2001 ዓ.ም. ግንባታው ተጀምሮ በ2004 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ በ230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከ18 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት በስድስት ኮሌጆች ያስተምራል፡፡

ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ብሔር ተኮር ግጭት ተቀስቅሶ የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ግጭቱ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በመዛመት የአራት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉንና አሥራ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማር ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አቋርጠው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...