Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአፍሪካ መሪዎች በአምስት ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ ይመክራሉ

የአፍሪካ መሪዎች በአምስት ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ ይመክራሉ

ቀን:

  • የመንግሥት ተቋማት ትብብር ተጠይቋል

ከጥር 14 እስከ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ በሚካሄደው 30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአምስት ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ውይይት እንደሚያካሄድ፣ ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስከብርባቸው ውይይቶች እንደሚደረጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት ወደ ሥልጣን ከመጡ ለመጀመርያ ጊዜ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ነው፡፡

በአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የአኅጉሪቱን የተለያዩ ችግሮች ከመፍታት አንፃር ጠቃሚ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ገልጸው፣ መሪዎቹም በዋነኝነት በአምስት ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡

መሪዎቹ ከሚወያዩባቸው ቁልፍ አጀንዳዎች መካከል በሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ አማካይነት በመከናወን ላይ ያለውን የኅብረቱን አሠራር የማሻሻል ጉዳይ ዋነኛው ነው፡፡

ስለሆነም ኅብረቱን ከማሻሻል አንፃር በተከናወኑ ሥራዎች ላይ የሚደረገው ውይይት በዋነኛነት በአምስት ዓበይት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ አምስት ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የመጀመርያው የኅብረቱ ስብሰባዎች በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ ወሳኝ በሆኑ የአኅጉሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለሚዳስሱ ጥቂት ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት አቅሙን እንዲያጠናክርና አመራር እንዲሰጥ ማድረግ የሚለው ነው፡፡

ሁለተኛው ኅብረቱን የማሻሻል ጉዳይ ደግሞ የተቋሙን አደረጃጀት የተመለከተ ነው፡፡ ኅብረቱ ግዙፍ ተቋም እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በኅብረቱ የተደራጁ አካላት አንዱ ከአንዱ ጋር ሳይጣረስና አንዱ የሚሠራውን ሌላኛው ሳይሻማ በተቀናጀና በተቀላጠፈ ሁኔታ ኅብረቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣና የአፍሪካውያንን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያከናውነውን ሥራ በማጠናከር እንዴት ወደፊት እንደሚያራምድ ውይይት የሚካሄድበት ነው፡፡

ሦስተኛው ደግሞ የአፍሪካውንያ ዜጎች በኅብረቱ የመወከል ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ምንም እንኳን የአፍሪካ ኅብረት የአገሮች ስብሰባ ቢሆንም ከቢሊዮን በላይ አፍሪካውያን ዜጎች የተሰባሰቡበት፣ የሚወከሉበትና ጥላ የሆነ ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ ዜጎችን ማሳተፍ ተገቢ ነው የሚል አቋም ተይዟል፤›› በማለት ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በአፍሪካ ኅብረት ጉዳዮች ላይ አገሮችን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካውያንን እንዴት ይሳተፉ የሚለው ላይ ውይይት ይካሄዳል፡፡

አራተኛው ኅብረቱን ከማሻሻል አንፃር ለውይይት የሚቀርበው ጉዳይ ደግሞ፣ በኅብረቱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊነትና አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችንና ጉድለቶችን ማስተካከል በተመለከተ ነው፡፡

አምስተኛው ደግሞ የኅብረቱን የገንዘብ አቅም የማጎልበት ሲሆን፣ የተቋሙን በጀት አፍሪካውያን ራሳቸው እንዲሸፍኑ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ለማሰባሰብ የተጠኑትን ጥናቶች መሠረት አድርጎ ኅብረቱ በገንዘብ ኃይል እንዴት ራሱን መቻል እንደሚኖርበት መሪዎቹ እንደሚወያዩ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ በሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ አማካይነት ከሚቀርቡ ኅብረቱን የማሻሻል አጀንዳዎች በተጨማሪ፣ መሪዎቹ በአፍሪካውያን መካከል ስለሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የአኅጉሪቱን የእርሻ ዕድገት፣ የአፍሪካውያንን አየር ክልል ለአፍሪካውያን ነፃ ማድረግ፣ እንዲሁም በአኅጉሪቱ የሰላም ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

በዘንድሮው 30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ከ40 በላይ የአፍሪካ መሪዎች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ከመሪዎቹ በተጨማሪ የተባበሩትት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዬ ጉቴሬዝን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና ኃላፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የመስተንግዶ ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ለእንግዶቹ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የባህል ቱሪዝም፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የመብራት ኃይል እንዲሁም የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...