Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከንፋስ አመጣሽ ታክስና ከልማት ድርጅቶች ሽያጭ የሚገኝ 14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት...

ከንፋስ አመጣሽ ታክስና ከልማት ድርጅቶች ሽያጭ የሚገኝ 14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ሆኖ ቀረበ

ቀን:

የብር ምንዛሪ ተመን እንዲቀንስ በመደረጉ የአገሪቱ ባንኮች ከነበራቸው ተቀማጭ የዶላር ክምችት ካገኙት ድንገተኛ ትርፍ ላይ መንግሥት በንፋስ አመጣሽ ታክስ ከሚያገኘው ገቢ፣ እንዲሁም ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሽያጭ እንደሚገኝ የታሰበ 14 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት በጀት እንዲሆን ተጠየቀ፡፡

ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤተ ያፀደቀው ይህ የተጨማሪ በጀት፣ ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ፓርላማው እንዲያፀድቀው ቀርቧል፡፡

ተጨማሪ በጀቱን ለማፀደቅ የቀረበው ረቂቅ ማፅደቂያ ሰነድ አባሪ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. በ15 በመቶ እንዲቀንስ በተደረገበት ወቅት ባንኮች በወቅቱ በነበራቸው ተቀማጭ የውጭ ገንዘብ ላይ ከፍተኛ ትርፍ አግኝተዋል፡፡

በዚህ መሰሉ የመንግሥት ውሳኔ የንግድ ተቋማት ያለምንም ዓይነት ወጪና ልፋት በሚያገኙት ትርፍ ላይ ንፋስ አመጣሽ ታክስ ከስድስት ዓመት በፊት መጣሉ ይታወሳል፡፡ በዚህ የታክስ ድንጋጌ መሠረት ተቋማት በድንገት ከሚያገኙት ትርፍ 75 በመቶውን በታክስ መልክ ለመንግሥት የማስረከብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት በጥቅምት ወር የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ እንዲቀንስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲወስን የአገሪቱ ባንኮች ካገኙት ንፋስ አመጣሽ (ድንገተኛ) ትርፍ ላይ መንግሥት 4.3 ቢሊዮን ብር እንደሚያገኝ ታሳቢ መደረጉን አባሪ ሰነዱ ያብራራል፡፡

ከእነዚህ ገቢዎች የሚገኘው 14 ቢሊዮን ብር በዋናነት ማለትም አምስት ቢሊዮን ብር የሚሆነው በቀጣዮቹ ወራት በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍና ለማቋቋም እንዲውል የታሰበ ሲሆን፣ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ደግሞ አንድ ቢሊዮን ብር ለመልቀቅ ታስቦ የቀረበ ነው፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ 11 ዩኒቨርሲቲዎች በ2011 ዓ.ም. የሚኖራቸውን የቅበላ አቅም ከ1,500 ወደ 2,500 ለማሳደግ 500 ሚሊዮን ብር፣ ለዲጂታል ቴሌቪዥን ሥርዓት የመሣሪያ ግዥ ቀሪ ክፍያዎች 300 ሚሊዮን ብር ለመክፈል እንደሚውል በረቂቅ ሰነዱ ተብራርቷል፡፡ ቀሪው ደግሞ ለሌሎች ድንገተኛ ወጪዎች በመጠባበቂያነት ተደግፏል፡፡ ተጨማሪ በጀቱ እንዲፀድቅ በመንግሥት የተጠየቀ ቢሆንም፣ ፓርላማው ግን ለዝርዝር ዕይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...