የአፍሪካ አገሮች የገበያ ክልከላን በማስወገድ የጋራ የሆነ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ሊመሠርቱ ነው፡፡
የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በይፋ የሚመሠረተው፣ ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ነው፡፡
የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በክልከላ የተተበተበ በመሆኑ፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች አፍሪካ ውስጥ እንደልባቸው መሥራት ተስኗቸው እንደቆየ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የአፍሪካ አገሮች ለአፍሪካ አየር መንገዶች የበረራ ፈቃድ ለመስጠት ሲያንገራግሩ ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት የአፍሪካ አገሮች በአየር ትራንስፖርት ያላቸው ትስስር ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡፡
የአፍሪካ አገሮች የአፍሪካን ሰማይ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ክፍት ለማድረግ የያማሱኩሮ ውሳኔ የተባለውን ስምምነት እ.ኤ.አ. 1999 ያፀደቁ ቢሆንም፣ እስካሁን ተግባራዊ ሳያደርጉ ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ኅብረት ከአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበርና ከአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ጋር በመተባበር፣ የያማሱክሮ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
እ.ኤ.አ. በጥር 2015 አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ አገሮች የያማሱኩሮ ውሳኔን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በፊርማ ያፀደቁ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ወደ 22 አድጓል፡፡ በመጪው እሑድ በሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በይፋ መመሥረቱን ያበስራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህን አስመልክቶ የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ማክሰኞ ጥር 15 ቀን በሰጡትት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታ የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ ሲሰጥ እንደቆየ ገልጸዋል፡፡ የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታ የአፍሪካ ኅብረት 2063 የልማት አጀንዳ አንዱ አካል መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ፣ የጋራ ገበያ መመሥረት የአፍሪካ አየር መንገዶች አፍሪካ ውስጥ ያለገደብ ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ እንደሚያሳድግ፣ የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ትስስር እንደሚያጠናክር፣ የንግድ ልውውጥና ቱሪዝም እንደሚስፋፋና ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የተናገሩት አቶ አህመድ፣ 300,000 ቀጥተኛ የሆነና ሁለት ሚሊዮን ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ላይ የሚሠራ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ እንዳቋቋመ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ጥር 20 ቀን የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታ በይፋ የሚታወጅበት ታሪካዊ ዕለት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ 15 በመቶ፣ የአውሮፓ አገሮች የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ 60 በመቶ መሆኑን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ የአየር ትራንስፖርት ንግድና ቱሪዝምን በማሳደግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ ውስጥ ባለው የገበያ ክልከላ ምክንያት የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ወደኋላ መቅረቱን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ አፍሪካውያን ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ለመጓዝ አውሮፓ ደርሶ ለመመለስ ሲገደዱ እንደቆዩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ ምን ያህል የአየር ትራንስፖርት ትስስሩ የላላ እንደሆነ ያሳያል፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የአፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ ባለመመሥረቻው ባለው የገበያ ክልከላ ምክንያት የአፍሪካን የአየር ትራንስፖርት ገበያ የውጭ አየር መንገዶች እንደተቆጣጠሩት ገልጸዋል፡፡
‹‹በአፍሪካና በሌሎች አኅጉሮች መካከል ከሚመላለሰው መንገደኛ ፍሰት 80 በመቶውን የሚያጓጉዙት የውጭ አየር መንገዶች ሲሆኑ፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች የገበያ ድርሻ 20 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ፍትሐዊ ያልሆነውን የገበያ ሥርዓት መለወጥ አለብን፡፡ በገዛ አኅጉራችን የበይ ተመልካች መሆን የለብንም፤›› ብለዋል፡፡
እሑድ ጥር 20 ቀን በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ 32 አገሮች የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታን ያፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡