Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሁለቱ የረዥም ርቀት ባለታሪኮች በለንደን ማራቶን ሊገናኙ ነው

ሁለቱ የረዥም ርቀት ባለታሪኮች በለንደን ማራቶን ሊገናኙ ነው

ቀን:

  •  መሠረት ለመጀመርያ ጊዜ በቶኪዮ ማራቶን ትሮጣለች

በረዥም ርቀት በማይታመን ብቃትና ፍጥነት በአሸናፊነቱ የሚታወቀው ቀነኒሳ በቀለ ሚያዝያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚካሄደው ለንደን ማራቶን ከእንግሊዛዊው ሞ ፋራህና ከኬንያዊው ኤሉዱ ኪብቾጌ ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ለበርካታ ጊዜያት ከአትሌቲክሱ መድረክ ርቃ የከረመችው መሠረት ደፋር የመጀመርያዋን የማራቶን ሩጫ በቶኪዮ እንደምታደርግ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ዘገባ አመልክቷል፡፡

የዓለም አቀፉ ማኅበር በወርቅ ደረጃ ከሚያስቀምጣቸው ዓመታዊ ማራቶኖች አንዱ በሆነው ለንደን ማራቶን፣ በወንዶች ሦስቱን ጠንካራ አትሌቶች በአንድ መድረክ ማገናኘቱ ፉክክሩን ከወዲሁ እንዲጠበቅ ማድረጉ ዘገባዎች እያመለከቱ ይገኛል፡፡

በረዥም ርቀት የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ ፊቱን ወደ ጎዳና ሩጫ ካዞረ ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ በርቀቱ የቀድሞ ስምና ዝናውን ማስጠበቅ እየቻለ አይደለም፡፡ ለዚህም ዓምና በዚሁ በለንደን ማራቶን ተወዳድሮ ለአሸናፊነት ሲጠበቅ፣ በኬንያዊ ዳንኤል ዋንጅሩ ተቀድሞ ሁለተኛ መውጣቱ አይዘነጋም፡፡ አሸናፊው ዋንጅሩ 2፡05.48 ሲያጠናቅቅ ቀነኒሳ ደግሞ 2፡05.57 ያስመዘገበው ሰዓት ይጠቀሳል፡፡

የዘንድሮውን ካለፉት ዓመታት ለየት የሚያደርገው በትውልድ ሶማሌያዊ በዜግነት እንግሊዛዊው ሞ ፋራህና ኬንያዊው ኤሉድ ኬብቾጌ በአትሌቲክስ ካላቸው ስምና ዝና በመነሳት ለማሸነፍ በሚያደርጉት ትንቅንቅ ውድድሩን ተጠባቂ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

ወደ ቀድሞ ስምና ብቃቱ ለመመለስ ባጋጠመው ተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት ከውድድር ርቆ የቆየው ቀነኒሳ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብቅ እያለ በተሳተፈባቸው የሩጫ መድረኮች ደግሞ ወደ አሸናፊነት መመለስ ጀምሯል፡፡ ለዚህም በቅርቡ በህንድ ካልካታ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ማሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም ሚያዚያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሞ ፋራህ ጋር የሚወዳደርበት የለንደኑ ማራቶን ግን ለቀነኒሳ ብቻም ሳይሆን፣ ለአትሌቲክሱ ልዩ መድረክ እንደሚሆን ጭምር ሙያተኞች ያምናሉ፡፡

በሌላ በኩል ለበርካታ ጊዜያት ከተለያዩ የሩጫ መድረኮች ርቃ የቆየችው መሠረት ደፋር፣ የካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው ማራቶን ለመጀመርያ ጊዜ እንደምትሮጥ ታውቋል፡፡ በወንዶች ተስፋዬ አበራና ፀጋዬ ከበደ ካለፈው ዓመት አሸናፊ ዊልሰን ኪፕሰንግ ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡

በወሊድና በጉዳት ምክንያት ከሩጫ ርቃ የከረመችው መሠረት፣ ሙሉ ማራቶን ስትሮጥ የመጀመርያ ጊዜዋ ቢሆንም ከሚጠበቁት ተወዳዳሪዎች አንዷ ለመሆኗ የዓለም መገናኛ ብዙኃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በ5,000 ሜትር የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናዋ መሠረት፣ በ3,000 ሜትር ተደጋጋሚ ድሎችን በማስመዝገብ ከታላላቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንዷ በመሆን ትጠቀሳለች፡፡

በመጪው የካቲት በሚደረገው ቶኪዮ ማራቶን፣ ኬንያውያቱ እንስቶች ችሪዮቲች ሪዮኖሪፓና ሒላህ ኪፕሮፕ እንዲሁም ኢትዮጵያውያኑ ሩቲ አጋ፣ ሹሬ ደምሴና ብርሃኔ ዲባባ በርቀቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከምትሳተፈው መሠረት ደፋር ጋር የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡ በወንዶች ደግሞ በርቀቱ ያለፈው ዓመት አሸናፊ ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሰንግ፣ ዲክሰን ቹምባ፣ ቪሴንት ኪፕሩቶ፣ ጌዲዮን ኪፕኬተርና አምሶ ኪፕሩቶ ሲጠቀሱ፣ ከኢትዮጵያውያኑ ተስፋዬ አበራ፣ ፀጋዬ መኰንንና ፈይሳ ሌሊሳ ተጠባቂ ሆነዋል፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በተለያዩ አገሮች በተደረጉ የማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አሸናፊ በመሆን ያጠናቀቁበት ሳምንት ሆኗል፡፡ እሑድ ጥር 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በህንድ ሞምባይ በተከናወነው ማራቶን በወንዶች ሰለሞን ዲስኪክሳ ርቀቱን 2፡09.34 በማጠናቀቅ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ሹመቴ አካልነው 2፡10.01 ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ አይቸው ባንቴ፣ ሁሴን መሐመዳሚንና አብርሃም ግርማ አምስተኛ፣ ስድስተኛና ስምንተኛ በመውጣት አጠናቀዋል፡፡

በሴቶች አማን ጎበና 2፡25.50 በማጠናቀቅ አንደኛ ስትሆን፣ ሹኮ ገነሞና ብርቄ ደበሌ 2፡29.42 እና 2፡29.45 በማጠናቀቅ ሦስተኛና አራተኛ በመሆን ያጠናቀቁ ናቸው፡፡

በቻይና ሆንግ ኮንግ በተደረገው የማራቶን ውድድርም በወንዶች፣ ቦንሳ ዲዳ ሲያሸንፍ ርቀቱንም 2፡13.42 አጠናቋል፡፡ በሴቶች ጉልሜ ቶሎሳ 2፡29.36 በማጠናቀቅ አንደኛ ስትወጣ፣ መስከረም አሰፋና ፋንቱ ኢቴቻ 2፡29.41 እና 2፡30.11 በማጠናቀቅ ሁለተኛና ሦስተኛ ወጥተዋል፡፡ ቤተልሔም ሞገስ፣ መሠረት ረጋሳ፣ አስካለ ዓለማየሁ፣ አበበች አፈወርቅና አበሩ መኩሪያ ተከታትለው በመግባት እስከ ዘጠነኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...