Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ2.1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር በሸገር አውቶብሶች

2.1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር በሸገር አውቶብሶች

ቀን:

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል አንዱ የትራንስፖርት እጥረት ነው፡፡ ያለውን የትራንስፖርት ችግር የሚያማርሩ ነዋሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያን መጎብኘት ያቻሉ የሌላ አገር ዜጎችም ናቸው፡፡ ተማሪዎች በሰዓታቸው በትምህርት ገበታቸው እንዳይገኙ፣ ሠራተኞች በጊዜ ወደ ቢሯቸው እንዳይገቡ፣ ሰዎች በተቀጣጠሩበት ቦታ ሰዓታቸውን ጠብቀው እንዳይገናኙ የትራንስፖርት ችግር እንቅፋት መሆኑ የተለመደ ነው፡፡

15 ደቂቃ የማይፈጅ ጉዞ በትራንስፖርት ችግር ሰዓታት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ለሰዓታት ቆመው ታክሲ መጠበቁ አሰልችቶት ኪሎ ሜትሮችን በእግር ለመሄድ ተገደው፣ ታክሲ ለመያዝ ሲጋፉ በግርግር ሞባይሎ አሊያም ገንዘብዎ ተሰርቆ፣ ግፊያውን መቋቋም አቅቶት ወድቀው፣ ባለው የትራንስፖርት ችግር ምክንያት ሌሎችም ያልታሰቡ ችግሮች አጋጥሞት ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህ የትራንስፖርት ችግር በአዲስ አበባ ለመኖር የሚከፈል ዋጋ ይመስል ነዋሪዎቹን እየፈተነ ይገኛል፡፡

ሦስት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች መኖሪያ የሆነችው ከተማዋ ካሉባት መሠረታዊ ችግሮች መካከል የሆነውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፣ እየተደረጉም ይገኛሉ፡፡ ለትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ የሚውሉ ታክሲዎችና ሚኒባሶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይታያል፡፡ ያለውን የትራንስፖርት ችግር በመጠኑም ቢሆን እንዲያረጋጉ ባለፈው ዓመት ብቻ 1,163 ሜትር ታክሲዎች ከቀረጥ ነፃ ገብተዋል፡፡ ቀላል የመንገደኞች ባቡርም ሥራ ጀምሯል፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባ በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት፣ አሁን አሁን ደግሞ በሥራ ሰዓትም የሚታየው የትራንስፖርት እጥረት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን የመጨመር ሥራው ቢቀጥልም ጉልህ ለውጥ አለመታየቱን ያሳያል፡፡

- Advertisement -

የከተማዋን የትራንስፖርት ሥርዓት በማሳለጡ ረገድ በግል ከተሠማሩ ግለሰቦች ባሻገር አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶችም የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ረገድ ፈር ቀዳጅ የሆነውን አንበሳ የከተማ አውቶብስን ማንሳት ይቻላል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለብዙኃኑ ሲያቀርብ ዓመታትን ያስቆጠረው አንበሳ የከተማ አውቶብስ በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞችን ያጓጉዛል፡፡ ተደራራቢ አውቶብሶችንም ለአገሪቱ አስተዋውቋል፡፡

በ2008 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ሥራ የጀመረው ሸገር የብዙኋን ትራንስፖርት አገልግሎትም ሌላው በዘርፉ የተሠማራ የመንግሥት ድርጅት ነው፡፡ ሸገር በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ከሁለት ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረው ድርጅቱ በአንድ ጊዜ 70 ሰዎችን የመጫን አቅም ያላቸውን አሥር አውቶቢሶች ይዞ ነበር ሥራ የጀመረው፡፡

ሸገር የአውቶብሶቹን ቁጥር ወደ 209 ከፍ ማድረጉን በዚህኛው ሳምንት መግቢያ ላይ ያወጣው የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በእነዚህ ስድስት ወራት 21 ሚሊዮን ደንበኞቹን ማጓጓዝ ችሏል፡፡ በድርጅቱ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያው አቶ አለልኝ በለጠ፣ አውቶቢሶቹ እንደ ጀሞ፣ የካ አባዱ፣ አያት ኮንዶሚኒየም ባሉ የማስፋፊያ መስመሮች ላይ በስፋት እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡

ከንጋት 12 ሰዓት እስከ ምሽት 3 ሰዓት ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት የሸገር አውቶብሶች በ44 የሥምሪት መስመሮች ተሠማርተው፣ 2.1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር የከተማዋን ጎዳናዎች መሸፈን ችለዋል፡፡ ‹‹ከአንድ ብር ከ50 ሳንቲም ጀምሮ እስከ አምስት ብር ነው የምናስከፍለው፡፡ አንድ መንገደኛ ከመገናኛ እስከ ቱሉ ዲምቱ ድረስ ሲጓዝ የሚከፍለው 5 ብር ብቻ ነው፤›› ያሉት አቶ አለልኝ፣ ድርጅቱ በ2017 ዓ.ም ተመራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ የመሆን ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የድርጅቱ የ2010 ዓም. የ6 ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ ጥቅል ገቢው ከ13 ሚሊዮን ወደ 53 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለት ችሏል፡፡ የሥምሪት መስመሮቹም ከ24 ወደ 44 እንዲሁም የአውቶቡስ ቁጥሩም ከ89 ወደ 209 ከፍ ብሏል፡፡ ድርጅቱ በዚህኛው ዓመት መጀመርያ ላይ እጀምራለሁ ያለውን የተማሪዎች አውቶቡስ አገልግሎትም ከሰሞኑ መስጠት ጀምሯል፡፡

የተማሪዎች መጓጓዣ አውቶብሶችና ተደራራቢ የሕዝብ ትራንስፖርት አውቶብሶችን አገልግሎት ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ናቸው፡፡ በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ተገጣጥመው ከተመረቁት 80 አውቶብሶች ውስጥ 50ዎቹ የሕዝብ አውቶብሶች ሲሆኑ፣ 30ዎቹ የተማሪዎች አውቶብሶች ናቸው፡፡ በወቅቱ የተመረቁትን ጨምሮ ሸገር አውቶብስ ከቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ ጋር የገዛቸው አውቶብሶች ዋጋ 3.4 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ናቸው ተብሏል፡፡

ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙ 300 የከተማና 30 የተማሪ አውቶብሶች ባለቤት ነው፡፡ በርክክብ ላይ የሚገኙት 25 ተደራራቢ አውቶብሶችም በተያዘው ጥር ወር ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ ከአንድ ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...