Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልእውንነት አስመሳዩ ጥበብ

እውንነት አስመሳዩ ጥበብ

ቀን:

በጎተ ኢንስቲትዩት አዳራሽ ውስጥ በተሽከርካሪ ወንበር የተቀመጡ ወጣቶች ይታያሉ፡፡ ሁሉም ጆሯቸው ላይ ሔድፎን፣ ዓይናቸው ላይ የቨርችዋል ሪያሊቲ መነፅር አድርገዋል፡፡ በመነፅሩ የሚመለከቱት ፊልም የፈጠረባቸውን ስሜት ከሰውነታቸው እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል፡፡ በፊልሙ አስጨናቂ ነገር ሲያዩ በእውን የሆነ ያህል ስለሚሰማቸው መነፅሩን ለማውለቅ ይቃጣቸዋል፡፡ በፊልሙ አስገራሚ ትዕይንት ሲመለከቱ፣ የሚያዩትን ለማጣጣም ወንበሩን በተለያየ አቅጣጫ ያሽከረክራሉ፡፡

‹‹ቨርችዋል ሪያሊቲ›› (እውንነት አስመሳይ ጥበብ) በቪዲዮ የሚታዩ ትዕይንቶች በእውን እየተፈጠሩ ያሉ ስለሚያስመስል የተመልካቾችን ቀልብ ይገዛል፡፡ በጎተ ኢንስቲትዩት ከነበሩት ተመልካቾች አንዷ፣ ትመለከት የነበረው ፊልም አካል የሆነች ያህል ተሰምቷት ግራ በመጋባት መነፅሩን አውልቃ አካባቢዋን ትቃኝ ነበር፡፡ መነፅሩን አድርጋ ለጥቂት ደቂቃዎች ትመለከትና በድጋሚ መነፅሩን አውልቃ በቨርችዋል ሪያሊቲና በአካባቢዋ ያለው እውናዊ ዓለም መካከል ባለው መመሳሰል ትገረማለች፡፡ በአዳራሹ እንደነበሩት አብዛኞቹ ተመልካቾች ሁሉ ቨርችዋል ሪያሊቲ ስትመለከት የመጀመሪያዋ ነበር፡፡

ቨርችዋል ሪያሊቲ ዓለም ከደረሰባቸው የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ለቨርችዋል ሪያሊቲ የተዘጋጁ ሔድሴቶች በመጠቀም ቪዲዮ መመልከት ይቻላል፡፡ ተመልካቾች በቪዲዮው የሚያዩትን ትዕይንት ከተለያየ አቅጣጫ ለመመልከት፣ በአራቱም አቅጣጫ መንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ ቪዲዮው በስክሪን ላይ እንደሚታየው ሳይሆን ትዕይንቱ በተከናወነበት ቦታ ያሉ እንዲመስላቸው ቴክኖሎጂው ያስችላል፡፡ የቨርችዋል ሪያሊቲ ሔድሴት ዓይን ስለሚሸፍንና ጆሮ ላይ የሚደረገው ሔድፎን በእውን ዓለም ያለውን ድምፅ ስለሚያግድ ተመልካቾች በቪዲዮው ሙሉ በሙሉ ይሳባሉ፡፡

- Advertisement -

በቨርችዋል ሪያሊቲ ያሉ ምስሎችና ድምፆች የሚዘጋጁት ተመልካቾች በእውነታው ዓለም በስሜት ሕዋሶቻቸው በመታገዝ የሚያዩትና የሚያደምጡትን በማስመሰል ነው፡፡ ስለዚህም በቪዲዮው ያለውን ምስልና ድምፅ የሚከታተል ሰው በእውን እየተከናወኑ ሊመስለው ይችላል፡፡ በቪዲዮው የሚታዩ ሰዎችን በቅርበት መመልከትና አካባቢያቸውን እነሱ በሚያዩበት ቅርበት መቃኘት አስደሳች ስሜት ይፈጥራል፡፡

ቴክኖሎጂው ከዚህም በላይ ተራቆ ተመልካቾች በቪዲዮ የሚሳተፉበት የቨርችዋል ራያሊቲ መሣሪያም ተፈጥሯል፡፡ ተመልካቾች ቪዲዮ ማየት ብቻ ሳይሆን በቪዲዮ የሚያዩት ትዕይንት አካል ሆነው ዕቃ ማንሳት አልያም ሌላም እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላሉ፡፡

በጎተ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው ‹‹ኒው ዳይሜንሽንስ፤ ቨርችዋል ሪያሊቲ አፍሪካ›› ዐውደ ርዕይ ከኬንያ፣ ሴኔጋልና ጋና የተውጣጡ አራት ፊልሞች የታዩበት ነበር፡፡ ዐውደ ርዕዩ ጥር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. የተከፈተ ሲሆን፣ ለሦስት ቀናት በጎተ ኢንስቲትዩት ታይቶ ከጥር 17 ቀን ጀምሮ ለአራት ቀናት (ቦሌ አካባቢ) ይቀርባል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1950ዎቹ ጀምሮ እያደገ የመጣው የቨርችዋል ሪያሊቲ ቴክኖሎጂ በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ በሕክምና ዘርፍ ለቀዶ ጥገናና የሥነ ልቦና ምርመራ ይውላል፡፡ በሳይንስ ነክ ትምህርቶች፣ በወታደራዊ ሥልጠና፣ በምህንድስና፣ በታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና በሌሎችም ዘርፎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ቨርችዋል ሪያሊቲ በጥበባዊ ሥራዎችም አሻራውን እያሳረፈ ሲሆን፣ በፊልም፣ በሥነ ጥበብና በሙዚቃ ያለው አስተዋፅኦ ይጠቀሳል፡፡

በፊልም ዘርፍ የአንድ አካባቢን ሙሉ ገጽታ (360 ዲግሪ) የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ገበያውን እየተቆጣጠሩት ነው፡፡ የሙዚቃ ቪዲዮዎችና ኮንሰርቶችን በቨርችዋል ሪያሊቱ ማቅረብም በሙዚቃ ኢንዱስትሪው እየገነነ መጥቷል፡፡ ቴክኖሎጂው በሥነ ጥበብም እየተዘወተረ ስለሄደ፣ የቨርችዋል ሪያሊቲ የሥነ ጥበብ ውጤት የሚታዩባቸው ፌስቲቫሎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡

‹‹ኒው ዳይሜንሽንስ›› (አዳዲስ አቅጣጫዎች) የሚል ስያሜ የተሰጠው የቨርችዋል ሪያሊቲ ዐውደ ርዕይ፣ አፍሪካውያን ፊልም ሠሪዎች በዘርፉ እያደረጉት ያሉትን እንቅስቃሴ ለማሳየት ያለመ መሆኑን አዘጋጆቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ጎተ ኢንስቲቲዩት በሚገኝባቸው አገሮች በቨርችዋል ሪያሊቲ የተዘጋጁት ፊልሞች መታየት የጀመሩት ከወራት በፊት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ በፊት በደቡብ አፍሪካ ፊልሞቹ ታይተዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎች አገሮች ይቀርባሉ፡፡

በዐውደ ርዕዩ የተካተቱት ፊልሞች ከኬንያ ‹‹ናይሮቢ ቤሪስ›› እና ‹‹ሌት ዚስ ቢ ኤ ዋርኒንግ››፣ ከጋና ‹‹ስፒሪት ሮቦት›› እና ከሴኔጋል ‹‹ዘ አዘር ዳካር›› ናቸው፡፡ አዘጋጆቹ እንደገለጹት፣ አጫጭር ፊልሞቹ ልቦለዳዊና ዘጋቢ ሲሆኑ፣ ተመልካቾችን እንዲሁም ፊልም ሠሪዎችንም ለቨርችዋል ሪያሊቲ ፊልሞች ቅርብ ለማድረግ ያለሙ ናቸው፡፡

‹‹ስፒሪት ሮቦት›› በጋና፣ አክራ ያለውን የጎዳና ላይ ጥበባዊ ንቅናቄ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ አዘጋጁ ጋናዊው ጆናታን ዶስቴ ሲሆን፣ ሥነ ጥበብ፣ ሙዚቃና ዳንስን ማኅበረሰቡ ሊከታተል በሚችልባቸው ጎዳናዎች የማቅረብ ሒደትን በፊልሙ ዳሷል፡፡ ተመልካቾች ወደ አክራ የተጓዙ እስከሚመስላቸው በከተማዋ የተካሄዱ ዐውደ ርዕዮችንና የሙዚቃ ትርኢቶችን በቨርችዋል ሪያሊቲ መነፅር ይቃኛሉ፡፡

የኬንያውያን አርቲስቶች ስብስብ በሆነው ዘ ኔስት ኮሌክቲቭ የተሠራው ‹‹ሌት ዚስ ቢ ኤ ዋርኒንግ›› የሰባት ደቂቃ ፊልም ነው፡፡ ከምድር ውጪ ካለ ፕላኔት ስለመጣ ወራሪ የሚያወሳ ሲሆን፣ ተመልካቾች በፊልሙ ተዋንያን መካከል ሆነው እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ይመለከታሉ፡፡

‹‹ዘ አዘር ዳካር›› በሴኔጋላዊቷ ሴሊ ራብ ኬን የተሠራ ዘጋቢ ፊልም ሲሆን፣ አንዲት ታዳጊ በሴኔጋል፣ ዳካር መልዕክት አዘል ጽሑፍ ይዛ ስትዘዋወር የምታየውን የአገሪቱን ገጽታ ያስቃኛል፡፡ በኬንያዊቷ የኔጌንዶ ሙኪ ፊልም ‹‹ናይቦቢ ቤሪስ›› ይሰኛል፡፡  በፊልሙ በሁለት ሴትና አንድ ወንድ ገፀ ባህሪ፣ ናይሮቢ በምሳሌያዊ መንገድ ተወክላ ቀርባለች፡፡

በቨርችዋል ሪያሊቲ በመታገዝ ፊልሞቹን መመልከት ልዩ ስሜት የፈጠረባቸው ተመልካቾች በጎተ ኢንስቲተዩት አስተውለናል፡፡ ከሌሎች አገሮች አንፃር በኢትዮጵያ ያለው እንቅስቃሴ ደካማ ቢሆንም፣ ብዙዎች ስለቴክኖሎጂው ግንዛቤ እያዳበሩ መጥተዋል፡፡

 አዘጋጆቹ እንደገለጹት፣ ዐውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተደረገው አሁን ካሉት የበለጠ ተመልካቾችን ለመሳብ ነው፡፡ ቨርችዋል ሪያሊቲ ለተመልካቾች ተጨማሪ እይታ የሚያክል ቴክኖሎጂ በመሆኑ ተመራጭ መንገድ እየሆነ መጥቷል፡፡ ፊልም ሠሪዎች በቴክኖሎጂው የታገዙ ቪዲዮዎችን ወደ ማዘጋጀት እያዘነበሉ ሲሆን፣ ተመልካቾችም በቨርችዋል ሪያሊቲ ፊልሞችን መመልከት ይመርጣሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ