Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምከሦስት ቀናት መስተጓጎል በኋላ ለ17 ቀናት የተለቀቀው የአሜሪካ በጀት

ከሦስት ቀናት መስተጓጎል በኋላ ለ17 ቀናት የተለቀቀው የአሜሪካ በጀት

ቀን:

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ወቅትና ከዚያም በኋላ ለሕዝባቸው ቃል የገቧቸውን አጀንዳዎች ለመፈጸም ሁኔታዎች እምብዛም አልፈቀዱላቸውም፡፡ በተለይ አሜሪካን በማስቀደም ለስደተኞች ያላቸው አሉታዊ አቋም ከማስተቸትም አልፎ፣ የአሜሪካን የመንግሥት በጀት እስከማስተጓጎል ደርሶ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች በከፊል ለሦስት ቀናት ያህል ቤታቸው እንዲቀመጡም ምክንያት ሆኗል፡፡

‹‹በእኔ የሥልጣን ዘመን የበጀት መዘጋት አይኖርም፤›› ሲሉ ከዚህ ቀደም የተናገሩት ትራምፕ፣ ሥልጣን በያዙ በዓመታቸው የመንግሥት በጀት ለሦስት ቀናት ተዘግቷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን እንዲሁ የአሜሪካ በጀት ለ16 ቀናት ያህል ተዘግቶ፣ ከ800 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ከፊል የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ተስተጓጉለው የነበረ ቢሆንም፣ ትራምፕ በሥራ ላይ እያሉ መስተጓጎሉ የተለየና በዴሞክራቶቹና በሪፐብሊካኑ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ያሳየ ነው አስብሏል፡፡ በኦባማ ዘመን በጀት የተዘጋው በሽግግር ላይ ሳሉ እንደነበር ሲኤንኤን አስታውሷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለሦስት ቀናት ከ800 ሺሕ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራቸው እንዲስተጓጎሉ ምክንያት የሆነው የመንግሥት በጀት መዘጋት፣ ዴሞክራቶቹና ሪፐብሊካኑ ባደረጉት ድርድር ከማክሰኞ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 17 ቀናት የተለቀቀ ሲሆን፣ ሁለቱ ፓርቲዎች በደረሱት ስምምነት መሠረት በስደተኞች ጉዳይ ላይ ይወያያሉ፡፡  ትራምፕና ተቃዋሚዎቻቸው በስደተኞች ጉዳይ ላይ መቀራረብ ካልፈጠሩ ደግሞ፣ አሁን የተለቀቀው በጀት ከ17 ቀናት በኋላ ዳግም ሊዘጋ የሚችልበት ሁኔታም ክፍት ነው፡፡

ከሦስት ቀናት መስተጓጎል በኋላ ለ17 ቀናት የተለቀቀው የአሜሪካ በጀት

 

ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪዎች በበጀቱ መለቀቅ ላይ የተስማሙት ሪፐብሊካኖቹ በወጣት ስደተኞች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወያየት ቃል ከገቡ በኋላ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕም ሰኞ ምሽት የበጀት ሰነዱን ፈርመዋል፡፡ ሆኖም ለአጭር ቀናት የተለቀቀው በጀት የአሜሪካን የመንግሥት ሠራተኞች ለ17 ቀናት ዕፎይታ የሚሰጥ ቢሆንም፣ በቀጣይ የረዥም ጊዜ በጀት በሚለቀቅበት ላይ ኮንግረሱ ከስምምነት ካልደረሰ የመንግሥት ሠራተኞች ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ተብሏል፡፡

ፈቃድ ያለ ክፍያ እንዲወስዱ የተደረጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራተኞችም ጊዜያዊ ቢሆንም ዕፎይ ብለዋል፡፡ ሮይተርስ የአሜሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ድርጅት ሳይንቲስት ቶም ቻፔልን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ የበጀት መለቀቁን መስማታቸው ወሳኝ ነው፡፡

ሪፐብሊካኖች ምን አሉ?

      የሪፐብሊካኑ ሴኔት መሪ ሚች ማክኮኔል ፓርቲያቸው ዴሞክራቶች በሚያነሱት በወጣት ስደተኞች ጉዳይ ላይ ለመወያየት ከስምምነት ደርሷል፡፡ ዴሞክራቶች ከ700 ሺሕ በላይ ለሚሆኑና በሕፃንነታቸው አሜሪካ ለገቡ የአሁን ወጣቶች መንግሥት ከለላ እንዲያደርግ ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም ሪፐብሊካኖቹ መንግሥት ለስደተኞች የሚሰጠውን አገልግሎት በዘጋበት ሁኔታ ለስደተኞቹ ጥበቃ መስጠትም አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ለመወያየትና ለ17 ቀናት ብቻ የተለቀቀውን የመንግሥት በጀት ለረዥም ጊዜ እንዲለቀቅ ለማስቻል ከስምምነት ተደርሷል፡፡

ምንም እንኳን ከስምምነት ቢደረስም፣ ትራምፕ በሰጡት መግለጫ ‹‹በኮንግረሱ ያሉ ዴሞክራቶች ወደ ራሳቸው በመመለሳቸው ደስተኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በስደተኞች ጉዳይ ላይም የረዥም ጊዜ ስምምነት የምንደርሰው ስደተኞች ለአገራችን ጥሩ እስከሆኑ ድረስ ብቻ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ዴሞክራቶች ከአሜሪካ መከላከያ በጀት ይልቅ ለስደተኞች ቅድሚያ መስጠትን መምረጣቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከሦስት ቀናት መስተጓጎል በኋላ ለ17 ቀናት የተለቀቀው የአሜሪካ በጀት

 

የዴሞክራቶች ቁጭት

ምንም እንኳን ሪፐብሊካኖች በስደተኞች ጥበቃ ጉዳይ ከዴሞክራቶች ጋር ለመወያየትና ከስምምነት ለመድረስ ቃል ቢገቡም፣ ዴሞክራቶች ጥርጣሬ ገብቷቸዋል፡፡ ‹‹ማክኮኔል ቃሉን ይጠብቃል?›› የሚለውም ያጠራጥራቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በበጀቱ መለቀቅና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መከፈት ተናደዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2020 ለሚደረገው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዎች ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የሴኔቱ አባላት ኤልዛቤት ዋረን፣ ክርስቲን ጊልብራንድ፣ ኮሪ ቦከር፣ በርኒ ሳንደርስና ካማላ ሃሪስ በጀቱ መለቀቅ የለበትም ብለው የተቃውሞ ፊርማቸውን ያሰፈሩ ናቸው፡፡

ሴናተር ሃሪስም ማክኮኔል የስደተኞቹን አጀንዳ በቀጣዮቹ ሳምንታት ለድርድር ያመጧቸዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ብዙዎቹም በበጀት መለቀቁ ላይ ደስተኞች አይደሉም፡፡

ማን አሸናፊ ሆነ?

የመንግሥት በጀት ባለመፈቀዱ ሪፐብሊካኖችም ሆኑ ዴሞክራቶች እንደ መንግሥት ሠራተኛው አይጎዱም፡፡ ሲኤንኤን እንደሚለው፣ ሁሌም ተጎጂውና የሚያጣው ወይም በበጀቱ መለቀቅ የሚያሸንፈው የመንግሥት ሠራተኛው ነው፡፡ ሆኖም በጀቱ ለሁለት ሳምንታት ያህል ቢለቀቅም፣ የስደተኞችና የበጀት አጀንዳ የዴሞክራቶችና የሪፐብሊካኖች ቀጣይ መፋለሚያ ናቸው፡፡

ይህም ከዚህ ቀደም በበጀት አለመፅደቅ ምክንያት ለሁለት ሳምንታት ያህል ቤት መቀመጥን ላዩት የመንግሥት ሠራተኞች፣ ከሳምንት በኋላ የሚኖረው ድርድር ውጤት የተለየ ችግር ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ግምትንም አሳድሯል፡፡

ከሦስት ቀናት መስተጓጎል በኋላ ለ17 ቀናት የተለቀቀው የአሜሪካ በጀት

 

የመንግሥት ተቋማት በከፊል የመዘጋት አንድምታ

በአሜሪካ ከ800 ሺሕ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች በጀት በመዘጋቱ ምክንያት ለሦስት ቀናት ያህል ሥራ አልገቡም ነበር፡፡ መቋረጥ በሌለባቸው የመንግሥት የአገልግሎት ተቋማት የሚሠሩት ደግሞ በነፃ ለመሥራት ተገደዋል፡፡ ያለክፍያ የሥራ ፈቃድ እንዲወጡ የተደረጉም አሉ፡፡

በበጀት አለመፅደቅ ሳቢያ ተዘግተው ከነበሩ የመንግሥት ተቋማት መካከል ብሔራዊ ፓርኮች ይገኙበታል፡፡ በአሜሪካ የሚገኙ ፓርኮች በቀን 750 ሺሕ ጎብኚዎች ቢኖራቸውም፣ በመዘጋታቸው ምክንያት በፓርኮች ከሚሰጥ አገልግሎት ሊገኝ የሚችልን 500 ሚሊዮን ዶላር አሳጥተዋል፡፡ ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑት መካነ አራዊት፣ የኮንግረስ ቤተ መጻሕፍትና ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ከተዘጉት ይገኙበታል፡፡

የገቢ መሥሪያ ቤቱም 90 በመቶ ያህል ሠራተኞቹ ሥራ እንዳይገቡ በማድረጉ አራት ቢሊዮን ዶላር ያህል የታክስ ተመላሽ ዘግይቷል፡፡ የፓስፖርት አሰጣጥ ላይ የቀን መጓተት የገጠመ ሲሆን፣ የፖስታ አገልግሎት፣ የመከላከያ የመጓጓዧ አገልግሎት ዘርፍ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ የማኅበራዊ ዋስትና ቢሮዎችና የምግብ ተቆጣጣሪው ቢሮ ሥራቸውን ካላቋረጡት መካከል ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...