Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ ላይ ተጨማሪ ነጥቦች

በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጫ ላይ ተጨማሪ ነጥቦች

ቀን:

በመርሐጽድቅ መኮንን ዓባይነህ

በዚህ መጣጥፍ የመጀመሪያ ክፍል የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከአታካች ግምገማ በኋላ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ተፈጥሮ ነበር ያለውን የእርስ በርስ ጥርጣሬና አለመተማመን አስወግዶ፣ ከፍተኛ መግባባትና የሐሳብ አንድነት ላይ እንደ ደረሰ ድምፁን ከፍ አድርጎ በማሰማት በቅርቡ ያወጣውን የአቋም መግለጫ ተንተርሼ አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳቴ ይታወሳል፡፡ በዚያ ክፍል ግንባሩ ግምገማውን ያካሄደበትን አመክንዮ፣ የመግለጫውን አወቃቀርና አንዳንድ ወገኖች በድጋፍም ሆነ በነቀፌታ መልክ የሚያሰሙትን አስተያየት በማጣቀስ ለጊዜው በመረጥኳቸው ጉዳዮች ላይ አተኩሬ የራሴን ትንታኔ ካቀረብኩ በኋላ፣ በማጠቃለያው ላይ በልዩ ትኩረት ተይዘው በኮሚቴው ውሳኔ ተላልፎባቸዋል የተባሉትን ስምንት ዋና ዋና ነጥቦች በይደር አቆይቻቸው ነበር፡፡ እነሆ በቃሌ መሠረት እንካችሁ ለማለት ዛሬ ተመልሻለሁ፡፡

ሕግና ሥርዓትን ስለማስከበርና የሕዝብን ደኅንነት ስለማስጠበቅ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እምነት የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅስቃሴዎችን በማጠናከር የሕዝቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ከሁሉ አስቀድሞ በአገሪቱ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተገቢ ነው፡፡ ግንባሩ ይህንን ያሰመረበት ከሰላም ውጪ የሚካሄድ ልማትም ሆነ የሚዘመር ዴሞክራሲ አለመኖሩን ለማጠየቅ ይመስላል፡፡ ስለሆነም ከፍተኛ አጽንኦት ሰጥቶ ውሳኔ ያሳለፈበት የመጀመሪያው ጉዳይ፣ እርሱ የሚመራው መንግሥት አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያጋጠማትን ሰው ሠራሽ አደጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቀለብስና ሕዝቡን ወደ ተረጋጋ ኑሮው እንዲመልስ የሚለው ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የኅብረተሰቡን ሰላማዊ ኑሮ ክፉኛ የሚያውኩ ማናቸውንም ዓይነት ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት ሲል ነግሮናል፡፡

በመሠረቱ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ላፍታም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የሚታዩትን የሕግ ጥሰቶች መንግሥቱ ተግቶ እንዲቆጣጠርና ሰላምና ደኅንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስፈን እንደሚገባው ተጠናክሮ መገለጹ፣ ‘ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ’ ከሚባል በስተቀር የሚነቀፍበት ምክንያት የለውም፡፡ በእኔ በኩል ይህ ውሳኔ ራሱን በራሱ የሚገልጽና ፈረንጆቹ (ሠልፍ ኤክስፕላናቶሪ) የሚሉት ዓይነት ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ በመንግሥት ስም የተደራጀ ተቋም ይህንን ካላከናወነ የማንን ጎፈሬ ሊያበጥር ኖሯል?

ከዚህ አንፃር ግንባሩ እንደሚለው በየአካባቢው የሕዝብ መገልገያዎች በሆኑ ተቋማት ላይ የተነጣጠረ ሁከትና ግርግር የሚፈጥሩ ወገኖችን ለይቶ በመከታተልና በመቆጣጠር፣ የኅብረተሰቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል መቀጠሉን ለማረጋገጥ ያመች ዘንድ፣ አውራና መጋቢ መንገዶችን በመዝጋት የዜጎችን ከሥፍራ ሥፍራ የመዘዋወር መብት ያላግባብ የሚያግዱ ሕገወጥ የተናጠልና የቡድን እንቅስቃሴዎች መገታት እንዳለባቸው ለመግባባት አያዳግትም፡፡ ሆኖም ይህ በወጉ ሊፈጸም የሚችለው በመንግሥት ብርቱ ፍላጎት ብቻ እንዳልሆነ ከወዲሁ መታወቅ አለበት፡፡ ቀድሞ ነገር በሁከት ፈጣሪነት የሚከሰሱት ግለሰቦችና ቡድኖች ያልተገባ መደበቂያ ዋሻ የሚያደርጉት ሰፊውን ሕዝብ ስለሆነ፣ ዕርምጃው ቢወሰድ ፍሬ የሚኖረው የሰላሙ ተጠቃሚ የሆነውን ምልዓተ ሕዝብ ከጎን ማሠለፍ የተቻለ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

ውሳኔው ከዚህ ላቅ ባለ ድምፀት በአንዳንድ አጎራባች ክልሎች ውስጥ በወሰን ይገባኛልም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ተደጋግሞ እያጋጠመ ያለው የንፁኃን ዜጎች ሞትና የሕዝብ መፈናቀል በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት ያሳስባል፡፡ ይልቁንም በቅርቡ በኦሮሚያናሶማሌ ክልሎች መካከል ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች ባጋጠሙ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ግጭቶች ሳቢያ የተፈጠረው የሰላማዊ ወገኖች ሞትና እንግልት፣ እንዲሁም የመቶ ሺዎች መፈናቀል እልባት አግኝቶ በግጭቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙት ዜጎች እንደገና የሚቋቋሙበትና መደበኛ ሕይወታቸውን በተረጋጋ መንገድ የሚመሩበት ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲመቻችላቸው ያዝዛል፡፡ ወደ ቀድሞው ቤት ንብረታቸው ሊመለሱ ይችሉ እንደሆነ ግን ውሳኔው አንዳች ፍንጭ አይሰጥም፡፡

በመጨረሻም እነዚሁ ክልሎች ለገቡበት የእርስ በርስ ግጭት መንስዔዎች ናቸው የተባሉት ሕገወጥንግድ እንቅስቃሴዎች ሳይቀር በአስቸኳይ ቆመው፣ አርሶና አርብቶ አደሮች የተሰማሩበት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለበለጠ አደጋ እንዳይጋለጥ አስፈላጊው ጥበቃና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ቃል ተገብቷል፡፡ ይሁን እንጂ የኮንትሮባንድ ንግዱ ከአባባሽነት አልፎ የደም አፋሳሽ ግጭቱ ዓይነተኛ መንስዔ ነው ለማለት በበኩሌ አልደፍርም፡፡ ዜጎች በብሔራዊ ማንነታቸውና በሚናገሩት የአፍ መፍቻ ቋንቋ እየተለዩ በጠራራ ፀሐይ መጠቃታቸው፣ መሳደዳቸውና በኃይል መፈናቀላቸው እየታየ የዚህ መንስዔ የኮንትሮባንድ ንግድ ነው ብሎ ማስተሀቀሩ አጥብቀን የምንመኘውን መፍትሔ በብዙ ማይሎች የራቀና የተወሳሰበ እንዳያደርገው እሠጋለሁ፡፡

የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ያሳለፈበት ሁለተኛው ነጥብ የአባል ድርጅቶቹን ውስጣዊ ዴሞክራሲ ይመለከታል፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ የተላለፈው ውሳኔ በአጭሩ በግንባር ደረጃ ሲካሄድ የቆየውን መሠረታዊ ግምገማ መነሻ በማድረግና የአገሪቱን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ በውጤታማነት ለማስፈጸም ይቻል ዘንድ፣ እያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚታይበትን ድክመት በጥልቀት ከመረመረ በኋላ በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ የእርምትና የማስተካከያርምጃ በሚወስድበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ድግግሞሽ ቢታይበትም እስካሁን ከምናውቀውና ከተለመደው የድርጅቱ ባህል እምብዛም የተለየ አሠራር ባለመሆኑ በዚህ ላይ አቃቂር ለማውጣት አልፈለግኩም፡፡

የልማት አቅርቦት ሚዛናዊነት

በክልሎች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ የልማት ደረጃ ልዩነት እየተፈጠረ መጥቷል የሚለውን ስሞታ እኔም አልፎ አልፎ እሰማለሁ፡፡ የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሦስተኛ ውሳኔው የተመለከተው ይህንኑ ነጥብ መሆኑ ታዲያ ስሞታው ሥነ ልቦናዊ ብቻ እንዳልሆነ አረጋግጦልኛል፡፡

በአገሪቱ የተተከለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሕዝቦች መካከል እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አስቀድሞ እንደ መለሰ ግንባሩ ያምናል፡፡ ያም ሆኖ ታዲያ እርሱ እንደሚገልጸው ከአፈጻጸም ድክመት ጋር በተያያዘ ከቦታ ቦታ የሚታዩ የልማት አቅርቦት ውጣ ውረዶች እንደሚታዩ ባካሄደው ግምገማ ሳይቀር አረጋግጦ መውጣቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በቅድሚያ እንደ ቆዳ ስፋታቸው ሁሉ ክልሎቻችን በተፈጥሮ ፀጋቸውም ሆነ በሰው ኃይል ሀብታቸው አንደኛው ከሌላው ጋር ሊለያዩ የመቻላቸውን እውነታ አምኖ መቀበል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ በፖሊሲ ደረጃ የተደገፈ እስኪመስል ድረስ አንደኛው ክልል በጥሬ የእርሻ ምርት አቅራቢነት ተወስኖ ሲንከላወስ፣ ሌላኛው ክልል በዘመናዊ ኢንዱስትሪ ውጤቶች አቀነባባሪነት እንዲሠለጥን ሲደረግ በሚታይበት ጊዜ ግን ፉክክሩ የተዛባና ፍትሐዊነት የጎደለው ይሆናል፡፡

የአቋም መግለጫው እንደሚለው በሥርዓቱ ውስጥ ያለው ወሳኝ የልማት አቅም በራሳቸው በክልሎች ውስጥ የሚገኘው ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ክልሎችን የሚያስተዳድሩ ብሔራዊ ድርጅቶች ይህንኑ የየክልሎቻቸውን የልማት አቅም አሟጠው የሚጠቀሙበትን ሥልት መቀየስ እንደሚገባቸው ኮሚቴው አስምሮበታል፡፡ በእርግጥ በዚህ ብቻ አልተወሰነም፡፡ በፌዴራል መንግሥቱ ደረጃም ቢሆን ይህንን ዓይነቱን የልማት ደረጃ ልዩነት ቀስ በቀስ የማጥበብና አገራዊ አንድነትን ይበልጥ የማጠናከር ፋይዳ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ እየታቀዱ መከናወን እንደሚገባቸው ተገቢውን አቅጣጫ እንደሰጠ አስተውያለሁ፡፡ እንግዲህ ገቢራዊነቱን በቅርብ እየተከታተሉ ወደፊት መወቃቀስ ሳይሻል አይቀርም፡፡

የማሻሻያ ፕሮግራሞች ክለሳና አተገባበር

በእኔ አስተያየት ኢሕአዴግ ነጋ ጠባ የሚወተውተውን ያህል ተሳክቶለት የማያውቀው የመንግሥታዊ ብቃትና ውጤታማነት ጉዳይ ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ሰፊውን ጊዜ የሚያባክነውና መላ ጉልበቱን የሚያፈሰው በማሻሻያ ፕሮግራሞች ቀረፃና ክለሳ ስም ገደብ የለሽና አንዳንዴም አስቀድመው ያልታቀዱ አታካች ስብሰባዎችን በማካሄድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ቀርቶ የፖለቲካ ድርጅቱ ስብሰባዎች እንኳ የሚካሄዱት በመንግሥት ወጪና የሥራ ሰዓት እንደሆነ እንታዘባለን፡፡

ከዚህ አንፃር ይህ ደካማና ከአገልግሎት ሰጪነት ይልቅ በስብሰባ አዳኝነት ተጠምዶ የምናየው መንግሥታዊ ቢሮክራሲ ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽመስጠት አቅምና ቁመና እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው፡፡

የተጀመሩትን የሪፎርም ፕሮግራሞች ውጤታማ ለማድረግና መስተካከል ያለባቸው አቅጣጫዎች ቢኖሩ ከሕዝቡና ከፈጻሚ አካላት ጋር በመተባበር እንደገና ተከልሰው ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገቡ ይደረጋል መባሉስ በተጨባጭ ምን ይጨምርልን ይሆን?

በዚህ አጋጣሚ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ተዋቅሮ የምናገኘው ሲቪል ሰርቪስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሶ የሕዝቡን አንገብጋቢ ጥያቄዎች በወቅቱ ለመመለስ ተግቶ እንዲረባረብ በመግለጫው አማካይነት ጥሪ ቀርቦለታል፡፡

የሕዝብን አመኔታ መልሶ ማግኘትና ቅሬታዎቹ የሚደመጡበትን ዕድል ማስፋት

ኢሕአዴግ በዚህኛው ውሳኔው እመራዋለሁ ከሚለው ሕዝብ ጋር የተካረረ ግጭት ውስጥ እንደገባና ታማኝነቱ ክፉኛ እየተሸረሸረ እንደመጣ የተቀበለው ይመስላል፡፡ እንዲያውም ከአሁን በኋላ ሕዝቡ ለሚያነሳቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መጣር እንደሚገባው መረዳቱን በአደባባይ ሲያውጅ ተሰምቷል፡፡ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ይመስላል ሕዝብ በየደረጃው የሚደመጥበትንና ወሳኝነቱ በሚገባ የሚረጋገጥበትን ዕድል ይበልጥ ለማስፋት፣ በተለይም የየአካባቢው ወጣቶች አዘውትረው የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስና በልማትም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ረገድ ሊኖራቸው የሚገባውን ንቁ ተሳትፎ በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እንዲከናወኑ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በእርግጥ በአንድ ወቅት የታጣን የሕዝብ አመኔታ ቀድሞ በነበረበት ሁኔታ መልሶ መቀዳጀቱ የተመኙትን ያህል ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ያም ሆኖ የፈሰሰ ውኃን ከማፈስ እንደማይከብድ አውቀው መግለጫው በተሰማበት ሰሞን በመጠኑም ቢሆን ልባቸውን ከፍተው ያዳመጡትና ቃል ኪዳኑን ከተስፋ ጋር የተቀበሉት ወገኖች አልታጡም፡፡ ስለሆነም ግንባሩ ‘ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ፀሎት’ እንዳይሆንበት ውሳኔውን ዕውን ለማድረግ እንደ ወትሮው የምልዓተ ሕዝቡን ልብ ለመማረክ ከፈለገ፣ በየጊዜው ሱባዔ መግባቱን ቀነስ አድርጎ በፀፀቱ ልክ ተጨባጭና ተከታታይ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ከቃላት በላይ የሚናገረው ተግባር ነውና፡፡

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ

የኢትዮጵያ ፌዴራል ዴሞክራሲ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ለፖለቲካ ብዝኃነትና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተገቢውን ዕውቅና ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ በዚህ ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ በግርድፉ ሲዳሰስ ያን ያህል አበረታች አልነበረም፣ አይደለምም፡፡ አሉ የሚባሉት ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች አማራጭ ፕሮግራሞቻቸውን ለሕዝብ እያቀረቡ እንዲያው ለወጉ ያህል በምርጫ የመሳተፍና ለመመረጥ የመወዳደር መብት ባይነፈጋቸውም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ለአምስት ተከታታይ ዙሮች በተካሄዱት አገር አቀፍ ምርጫዎች በሰፊ ርቀት እያሸነፈ መንግሥታዊ ሥልጣኑን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ ከቆየው ግንባር ጋር ያላቸው ግንኙነት ፍፁም የሻከረና ሰላማዊ ድባብ የማይታይበት ነው፡፡ ስለሆነም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከረዥም ጊዜ በኋላ ይህንኑ ሀቅ አምኖ በመቀበል፣ ከሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ከሕዝቡ ጋር ተባብሮ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ የሚታዩትን ህፀፆች ለማረም መወሰኑ አበጀህና ግፋበት የሚያሰኘው ነው እላለሁ፡፡

ከዚህ አልፎ ምሁራንና የሲቪክ ማኅበረሰቡ አባላት የዴሞክራሲውን ምኅዳር ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ተገቢ ሚናቸውን ለመጫወት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ተግቶ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት እስከ መግለጽ ደርሷል፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ የፖለቲካ ሜዳውን ለፖለቲካ ሥልጣን ተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ በአገራችን ጉዳይ እኛንም ያገባናል ለሚሉ ወገኖች ሁሉ ሳይሰስቱ ክፍትና ተደራሽ በማድረግ የተለያዩ አስተያየቶችን ያለአድልዎ ማስተናገድ መሆኑ ነው፡፡ የሀቀኛ ዴሞክራሲ ትሩፋቱም ከዚህ ውጪ የሚታሰብ አይሆንም፡፡

የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከበሬታ

የዜጎችና የሕዝቦች መሠረታዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ተፈጥሯዊነትና አይገሰሴነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 10 ሥር ተረጋግጧል፡፡ ዝርዝራቸው በምዕራፍ ሦስት ሥር የሠፈረው እነዚህ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ለሕዝብ ጥቅምና ለአገራዊ ደኅንነት ሲባል ራሱ ሕገ መንግሥቱ አስቀድሞ ከሚደነግገውና ይህንኑ ገቢራዊ ለማድረግ የወጣ፣ ወይም ወደፊት የሚወጣ ሕግ በግልጽ ከሚፈቅደው ሥነ ሥርዓት ውጭ በሆነ ማናቸውም ዓይነት ዕርምጃ ሊገደቡ አይችሉም፡፡

የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያወጣው የአቋም መግለጫ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጠሁት የሚለው ውሳኔ ግልጽነት የጎደለውና አሻሚነት የሚታይበት ነው፡፡ ለመሆኑ በአገሪቱ ውስጥ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ረገድ የሚታዩትን አዝማሚያዎችና ተግባራት እመክታለሁ ወይም እከላከላለሁ ማለት በተጨባጭ ምን ማለት ነው?

በእርግጥ የሕዝቡን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአስተማማኝ ደረጃ ለማስከበር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ተጨማሪርምጃዎች እንደሚወሰዱ በውሳኔው ላይ ተጠቅሷል፡፡ ለእኔ ግን ይህ ሁሉ ከቃላት ጨዋታ የዘለለ አይደለም፡፡ ልባዊ ቁርጠኝነትንም ያመለክታል ብዬ አላምንም፡፡ እንዲያውም ኮሚቴው ያለው ሊባል ከሚገባው በእጅጉ ያነሰ መስሎ ይሰማኛል፡፡

ለወደፊቱ የሚያጋጥሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ግንባሩ እንደሚለው አጥብቆ መመከት ወይም መከላከል ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ ይበልጥ የሚታመነው ግን በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ ይታያሉ ያላቸው ጥሰቶች በወጉ እንዲመረመሩና ተጠያቂዎች ሆነው የተገኙት ወገኖች ለፍርድ እንዲቀርቡ ቢያደርግ እንደሆነ ለመምከር እወዳለሁ፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ሚና

ይህኛውን የውሳኔ ነጥብ አስመልክቶ በክፍል አንድ ላይ ብዙ ሳላወራ የቀረሁ አይመስለኝምና በዚህ ክፍል ላይ ትንሽ እቆጠባለሁ፡፡

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የመጨረሻ ባደረገው በዚህ ነጥብ ሁለንተናዊ ልማትን በማበረታታትና አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ዙሪያ ተግተው መሥራት ሲገባቸው፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በሚያራርቅ አሉታዊ ተግባር ተጠምደው ይታያሉ ያላቸው አንዳንድ የግልና የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት ይህንኑ የተሳሳተ ቅኝታቸውን የሚያስተካክሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ አስታውቋል፡፡ ኮሚቴው በአንክሮ እንደገለጸው ከሆነ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት ከሕጋዊ አሠራር ባፈነገጠ አካሄድ የሁከትና የግርግር መልዕክቶች ይሠራጫሉ፣ ይሰበካሉ፡፡ ስለሆነም ይህንን አፍራሽ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የሚያስችሉና የተቀናጁ ዕርምጃዎች በመንግሥት እንደሚወሰዱ ከወዲሁ አስጠንቅቋል፡፡

በግልም ይተዳደሩ በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተልዕኮና የሥምሪት መስክ ቀድሞ ነገር የሚወሰነው በየተቋቋሙበት ቻርተርና በየተቀረፀላቸው ዝርዝር የኤዲቶሪያል ፖሊሲ አማካይነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተለየ ድርጅታዊ መግለጫ አማካይነት ከፍላጎታቸው ውጪ የስምሪት መስካቸውን እንዲያስተካክሉ ማስገደዱ እምብዛም አያዋጣም፡፡

ከመካከላቸው የሚዲያ ሕግ በግልጽ የሚከለክለውን የፈጸሙ መኖራቸው ከተረጋገጠ ደግሞ ጉዳዩን በተናጠል አጣርቶ ተገቢውን የዕርምት ዕርምጃ መውሰድ የአባት ነው፡፡ ከዚህ አልፎ በዘገባችሁ ውስጥ ያኛውን ትታችሁ በዚህኛው ላይ አተኩሩ እያሉ አጠቃላይነት ባለው አነጋገር ገና ብቅ ብቅ በማለት ላይ የሚገኙትን ለጋ ተቋማት እስከ ማስፈራራት መዝለቁ ግን፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ (3)ሀ ሥር በበር የከለከለውን ቅድመ ምርመራ በጓሮ መመለስ እንዳይመስል ብርቱ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...