Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንገድን ማወቅ የመሰለ ነገር የለም!አ።ሃራለን።xi ነን

ትዕግሥት በተፈታተነ የረጅም ሰዓት ጥበቃ አንዲት ታክሲ ዞራ መጣች። እነሆ ከካዛንቺስ አራት ኪሎ ልንጓዝ መሆኑ ነው። ዛሬም እንደ ትናንቱ፣ እንደ ሳምንቱ፣ እንደ አምናው ለመጓዝ። የሕይወት ዋናው ቀመር በእንቅስቃሴ የተነደፈ መሆኑን ማንም ሳያስረዳን የተረዳነው የኑሮ ፊዚክስ ነው። በእንቅስቃሴ ውስጥ ትግል፣ በትግል ውስጥ ለውጥ በሚል ርዕስ መጻሕፍት ሳይጻፉ በፊት ይህን እውነት የሁሉም ሰው ነፍስ ደረሰችበት። እናም ያለ አስገዳጅ እየተጓዘች፣ እየሮጠች፣ እየታገለች ነፍሳችን በሥጋ አድራ ትኖረዋለች። ኑሮ የዕለት ጉርስን ለማግኘት በመላወስ ውስጥ አቻና ተቀናቃኝ ዓላማ ሳይኖረው ዘልቋል።

የሰው ልጅ ከእምነቱ፣ ከፍልስፍናው፣ ከፍላጎቱና ከምኞቱ ላፍታ አቅሉን ሲስት የሚታየው ሲጓዝ ብቻ ነው። ሒደት ዋና የለውጥ መካኒክ ነውና። ታክሲዋ በሚተራመሰውና በሚጋፋው ሰው እየተወዛወዘች የቻለችውን ያህል አስገብታን ስታበቃ ሞላች። “ይኼው ነው እኮ! ቦታ እስኪይዙና እስኪረጋጉ ትግል ግድ ነው፤” አለና አንድ ጎልማሳ ተሳፋሪ ወዲያው መልሶ ደግሞ፣ “ሕይወትን ማለቴ ነው ጎበዝ። ስውር ፖለቲካ የለውም አደራችሁን። ኑሮ እግር ተሰቅሎ አይሆንም ለማለት ነው፤” እያለ አጠገቡ ላለው ወጣት ያብራራ ጀመር። ውስጡ ሌላ ስምና ቅጥያ እንደፈራ ንግግሩ ይመሰክራል። ወያላው ገብቶ በሩን እየዘጋ “ሳበው” ይለዋል ሾፌሩን። ሁላችንም ሳይታወቀን ከቦታ ቦታ እንጎተታለን!

ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ ያዙኝ ልቁኝ እያለ ነው። “ውይ! ኧረ አገር ስጡኝ ተው?! የት ሄጄ ልፈንዳ በመድኃኔዓለም?” ይወራጫል። “ኧረ ቀስ! በተረጋጋ ቀጣና ውስጥ ምንድነው እንደዚህ ማተራመስ?” ወይዘሮዋ ናት። “ምንድነው የሚለው? የት አለና ነው እንቆቅልሹ አገር ስጡኝ የሚለን?” ከኋላዬ ከተደረደሩት አንዲት የቀይ ዳማ። “አይ! እንቆቅልሹንስ ተይው። እንግዲያውስ ለእንቆቅልሾቻችን የሚበቃ አገር አለ እንዴ?” ሥጋ ባዳው አጉል ሰብቶበት፣ በከፊል ደመናማ የአየር ፀባይ ላብ የሚያጠምቀው ህያው ገጸ ባህሪ ከጎኗ ያሽሟጥጣል። ‹‹‘ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ’ ተብሏል። ምን እንቆቅልሾቻችን ቢበዙ በመልካም አስተዳደር ችግር ተጠቃለው ዕውቅና ተሰጧቸው ተቀምጠናል። ከዚህ በላይ ምን ይምጣ?” ሲል ጋቢና መሀል ላይ የተቀመጠ ወጣት ዞሮ ታክሲያችን በምትሃት ወደ ክብ ጠረጴዛነት የተቀየረች መሰለች።

“ዓይኔ ነው ጆሮዬ?” ትላለች ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠችው ደግሞ ተደናግራ። “ምን የሆነው?” ጎልማሳው መወራጨቱን ቀነስ አድርጎ ሲጠይቃት፣ “በአንዴ እንቆቅልሹን በፖለቲካ ፈቶ ያሳየኝ ወይ ያሰማኝ ነዋ?” ስትለው ጆከኛው ጎልማሳ፣ “የለም! የለም! የአላዲንና የፋኖሱ ነገር ነው። ሳናስበው ‘ዴሞክራት’ ስናስበው ደግሞ ‘አውቶክራት’ና ‘ታይራንት’ የሚያደርገን፣ የአላዲንና የፋኖሱ ጂኒ ነው፤” ይላታል። ‹‹‘ዳዲ’ ጂኒ ምንድነው?›› ሲል ደግሞ ብላቴናው በከረሜላ ጥርሶቹን መጨረስ በሚገባው ዕድሜ ‘ጌሙ’ ላይ እንዳፈጠጠ ዓይኑን ከስልኩ ባትሪ እኩል እያዳከመ ይጠይቃል። ወጋ፣ ወጋ፣ ጠቅ ጠቁ፣ ጂኒ ቁልቋል ወሬ ቢመስልም ሰውን ግን ያስተነፍሰዋል። ታክሲ ሳንባን የመተካት አቅም እንዳለው ሳይንስ ደርሶበት ይሆን?

ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠው ወጣት “አይዞህ ገብቶናል። ምን ይህን ያህል አጨናነቀህ?” ብሎ ሊያረጋጋው እየሞከረ ጠየቀው። “ወዳጄ ሥልጣን ለማግኘት ብቃት ሳይሆን አቋራጭ እንደ አማራጭ በሚያዝበት አገር እንዲያ ብዬ መናገር እንዴት አያደናብረኝ?” አለው ቀስ ብሎ አሁንም ሌላው ሰው እንዳይሰማው። “አገራችን እኮ የዴሞክራሲ ባህል እንደ ልቡ የሚንሸራሸርበትን መስመር እየዘረጋች ነው?” ሲለው ወጣቱ ጎልማሳው ሳቅ እያለ “እ? . . . ምነው ግድቡን ረሳኸው?” አለው። ተግባቡና ተሳሳቁ። ከሳቃቸው ኋላ የምሬት ወዮታ ስንሰማ ጆሯችን እዚያ ተሰደደ። “በሞቀበት መሰደድ ግን በደም ነው እንዴ የወረስነው?” ስትለኝ አጠገቤ የተቀመጠችው ልጅ ቁንጅናዋን አስተዋልኩ። “ቆንጆ አለማየት ከብዶን፣ ኑሮ ከብዶን እንዴት ይሆን የምንኖረው?” ይላል ሌላው እያንሾካሾከ። የሚሊኒየሙ ዓብይ ጥያቄ አትሉም? “ውይ! ውይ! ውይ! ኧረ ምን አባታችን ይሻለን ይሆን?” ወደሚለው አውቆ አበድ መሳይ ወጣት እንደ ዞርን ነን።

ለራሱ በፈጠረው ነፃነት ውስጥ ሌላ የሚያይም የሚሰማም አይመስልም። “ምነው?” አሉት አንዳንድ አጠገቡ የተቀመጡ ተሳፋሪዎች። “ታክሲ ነዋ። እዚህ ቆሜ ስጠብቅ ሰዓቱ አልፎኛል። ብደርስም አልገባም እኮ፤” አለ ጨንቆትና ከፍቶት። “የት ነው የማትገባው?” አሉት አንድ አዛውንት። “ክፍል ነዋ። አስተማሪው ከጀመረ በቃ አያስገባም. . .” ብሎ ሳይጨርስ፣ “አይዞህ ማርፈድ ራሱ አንዱ የትምህርቱ አካል ነው። ጎበዝ! ስም ጠሪ የለብንም እንጂ እኮ ለአንዳንዶቻችን ውሏችን ትምህርትና ፈተና ሆኗል፤” ብለው አዛውንቱ ፈገግ አሰኙን። ‘ተጨዋች ሽማግሌ አንቱ ሳይባል ያረጃል’ ማለት እሳቸው መስለው ነበር፡፡

“ወይ ዘንድሮ! ለመሆኑ አሠሪዎቻችን፣ አስተማሪዎቻችን በታክሲ ጥበቃ የምናጠፋውን ጊዜ እያሰቡ የማርክና የደመወዝ ጭማሪ ቢያደርጉልን ምን አለበት?” አለ የማይሰማ መስሎት አንድ ወጣት እየተንሾካሾከ። “ታክሲ የምንሠለፍበትንና የምንጠበቅበት ይታሰብልን ማለትህ ነው?” ይለዋል ጓደኛው። “ታዲያስ! እንዲህ ተሰባብረን እንዳንሆን ሆነን እየሠራንና እየተማርን የማርፈድ ቅጣት፣ በ‘አቴንዳንስ’ ሰበብ ‘ኤፍ’ ሰለቸን አቦ!” እያለ ምሬቱን ከቀልድ ወደ ምር ሲያሸጋግረው “እርፍ ይኼ ነበር የቀረን። መቼ ይሆን ሰበብ እየፈለግን ከዚህች ደሃ አገር ጉሮሮ ቀምቶ ለመጉረስ ማሰብ የምናቆመው?” ትላለች አጠገቤ የተቀመጠችው ቆንጆ።

“አሄሄ አንተ ጉርሻውን ትላለህ የደላህ። ምናለበት መዋጮው ባበቃ አትልም?” አሉ አዛውንቱ። ሁሉም ከራሱ ሕመም እየተነሳ አስተያየቱን ሲዘነዝር ቆየና ድንገት፣ “ለመሆኑ አገራችን በየዓመቱ በስንት አኃዝ ነበር እያደገች ነው የተባለው?” ብሎ ጎልማሳው ሲጠይቅ ‘በሁለት’ ብለው ሁለት ወጣቶች እኩል መለሱለት። “እሺ! እኛና ኑሯችን በስንት አኃዝ ነበር ቁልቁል የምንወርደው?” ሲል ግን እንኳን የሚመልስ የሚተነፍስ ጠፋ። ‘ምርጥ ምርጡን ለመንግሥት አለ ገዥው ፓርቲ!’ የምትል ደፋር ጥቅስ ታክሲያችን ውስጥ ተለጥፎ ብናይ ያየነውን ማመን አቃተን። ቆይ የሚታመን እንዲህ ይጥፋ?

ታክሲያችን አሁንም ትንሽ ከመንደርደሯ መልሳ ቀዝቀዝ አለች። ይኼኔ ወራጅ ልታወርድ ወይም ተሳፋሪ ልትጭን አልነበረም። ከፊታችን ያሉ የሠርግ ሥነ ሥርዓት አድማቂ ‘መርሰዲሶች’ መንገዱን ስለዘጉት እንጂ። “ተመልከት የሰውን ልጅ መጨረሻ፤” አለ ወያላው ለመጀመሪያ ጊዜ ሳቅ እያለ። “መጀመሪያ ማለትህ ነው?” አለው ሾፌሩ ዞር እንደ ማለት ብሎ። “የለም መጨረሻ ነው ያልኩህ። በቃ እኮ ከዚህ በኋላ ስለሕይወት የምታስበው ነገር አከተመ። ለምን? ተከርቸም ነዋ ትዳር። ሰው ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይጋባል፣ ይሞታል ሲባል አልሰማህም?” እያለ ይቀልዳል። “ኧረ እይልኝ ሙሽሮቹን?” ከሾፌሩ ኋላ ያለው ወጣት ነው። ሙሽሮቹ ከመኪናቸው ወርደው መኪና ሲገፉ በካሜራ እየተቀረፁ ነው።

“እርፍ! ደግሞ ከየት የታየ ‘ስታይል’ ይሆን ይኼ?” ይላል ወያላው። ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠው ጎልማሳ በበኩሉ፣ “ተዋቸው ይለማመዱት። ጉድና ጅራት ከበስተኋላ አይደል? ዛሬ እየሳቁ ነገ ደግሞ እያለቀሱ የትዳርን መከራ መግፋታቸው የት ይቀራል?” ብሎ ከማለቱ አጠገቤ የተቀመጠች ረዘም የምትል ሴት፣ “ሟርተኛ ሁሉ!” ስትል ሰማኋት። እንደ ሰማኋት አውቃለች መሰለኝ ፊቷን ወደ እኔ አዙራ፣ “አይገርምህም? ምናለበት ደህና ነገር ማሰብ ብንወድ? ቀና አስተሳሰብ በቃ እዚህ አገር ሕልም ሆኖ ሊቀር ነው? ዛሬ ተደራጁ ሲባል ነገ ይፈርሳሉ፣ ዛሬ ተፋቀሩ ሲባል ነገ ይጣላሉ፣ ዛሬ ወጠኑ ሲባል ነገ ይከሽፋሉ የማይልህ ሰው ጠፋ እኮ!” ስትለኝ ትከሻዬን ሰብቄ ‘ምን ይደረግ?’ አልኳት። ሁሉን አጣመን እያሰብን ሁሉ ሲጣመምብን ለምን እንደማንነቃ እንጃ!   

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወዲያ፣ “እኮ የዓለም መንግሥታት ምን እያሰቡ ይመስላችኋል?” ብሎ ጥያቄ ያነሳል። “ምንስ ቢያስቡ ምን አገባን? እዚህ የጓዳችንን  ችግር አንድ ነገር ሳናደርግ ምን ‘ኬላ’ ያሻግረናል?” ትላለች ከወዲህ። “እንዴ ዘመኑ እኮ የግሎባላይዜሽን ነው ኬላ አይደለም ህዋም ያሻግራል ጊዜው፤” ይላል ሌላው። “የፍሳሽ ቦይ ተደፍኖ ያቆረውን ውኃ መሻገር ያቃተንን አትርሱን ፕሊስ?” ትላለች ከወደ ጋቢና። ‘አሽሟጣጭ ሰውና ጋሬጣ አንድ ናቸው የሚያልፈውን ሁሉ በመቦጨቃቸው’ ይላል ከወደ ስፒከሩ ከተማ መኮንን። “እኛን ያስቸገረን እኮ ታዲያ የሚያልፈው አይደለም። እኔም አላልፍም እናንተም አታልፉም ብሎ መንገዱን የዘጋው ነው፤” ራሰ በራው ይቀጥላል። “በስንቱ ይሆን ይኼ መንገድ የሚዘጋው?” ትላለች ከአጠገቡ። ‘የዛሬ ጓደኛ ዋንጫ አገናኛው፣ መለኪያ አገናኛው፣ ሸርተት ሸርተት ይላል መከራ ሲያገኘው’ ከተማ ቀጥሏል። “እውነት ነው! ይኼው የመከራ ለትማ አለሁ ባዩ ሁሉ ቤቱን ዘግቶ ተቀመጠ፤” ወይዘሮዋ አጉል ነገር ጠመዘዘች። “የምን መከራ ነው የምታወሩት?” ከወደ መጨረሻ ይጠየቃል።

“ኧረ ባትሰማ ይሻልሃል። እኛስ ሰምተን ምን ፈየድን? ወይዘሮዋ ቀጥላለች። “እስካሁን መደመር አልተማርንም እንዴ?” ነገር ያልገባው ነገር ሊያቦካ ድንጉር ይላል። “እንጃ! እስካሁን መቀነስ ላይ ነበር። መሸፋፈን ላይ ነበርን። አሁን ግን ይኼው እንደምራለን፤” ይላል መሀል መቀመጫ ላይ ያለው። “ብቻ እነዚህ ‘አይሲስ’ የሚባሉትን አንድ ነገር ካላደረግናቸው እንጃልን?” ትላለች ደግሞ ከጎኔ። “እኛ ስንት ሆነን ነው እነሱን አንድ የምናደርጋቸው?” ብለው አዛውንቱ ጣልቃ ሲገቡ፣ “እንዴት?” የሚል ጥያቄ ተከተላቸው። “ምን እንዴት አለው? ይኼው እንደ ባቢሎን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላልቋል እኮ። አንዱ የሚናገረውን ሌላው አይሰማም። ወዲያ የፈለገውን ሲል ወዲህ የፈለገውን ይቀጥላል። ችግሮቻችን ውስብስብ። ነገራችን ውስብስብ . . .” ብለው ሳይጨርሱ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ ማስወረድ ጀመረ። “ኧረ መላ መላ . . .” የከተማ መኮንን ቀጥሏል፡፡ እኛም መንገዳችንን ይዘናል፡፡ መንገድን ማወቅ የመሰለ ነገር የለም፡፡ መልካም ጉዞ! 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት