Monday, March 4, 2024

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የግብፅ ጉብኝት ፋይዳ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ገጽታዎች እንደነበራት ታሪክ ያስረዳል፡፡ ሁለቱ አገሮች ጥንት የጦር መሣሪያ የተማዘዙት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም. የህዳሴ ግድቡን የመሠረት ድንጋይ ከጣለችበት ጊዜ ጀምሮ፣ ግብፅ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ስትከተልና የተለያዩ ሐሳቦችን ስታራምድ መቆየቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በፊት የነበሩት መሐመድ ሙርሲ መሪዎች ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ እንድታቆም ከማስፈራራት ባሻገር፣ ግብፅ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድርም ሆነ ድጋፍ እንዳያደርጉ ስትወተውት ቆይታለች፡፡ አብዱልፈታህ አልሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህም ቢሆን የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የተለያዩ አወዛጋቢ አስተያየቶችን ሲሰጡ ተደምጧል፡፡ ‹‹የናይል ወንዝ ለግብፃውያን የሞትና ሽረት ጉዳይ ነው፤›› ከማለት ባሻገር፣ ‹‹በግብፅ የውኃ ሀብት ላይ ማንም ጣልቃ እንዲገባ አልፈቅድም፤›› ሲሉ መደመጣቸው አይዘነጋም፡፡

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖና የግድቡን አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ተቋም ቀጥረው ለማስጠናት ቢስማሙም፣ ተቋሙ በሚሠራበት የመነሻ ሐሳብ ላይ የጋራ ስምምነት መድረስ አልቻሉም፡፡ በተለይ ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር ያደረገችው የውኃ ስምምነት የመነሻ ሐሳቡ አካል ይሁን የሚል ጥያቄ ማንሳቷና ኢትዮጵያ ጥያቄውን አለመቀበሏ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት አጣብቂኝ እንደከተተው እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡   

የውይይቱ አካል የሆነችው ሱዳን እንድትወጣና በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለውን ውዝግብ የዓለም ባንክ እንዲያሸማግላቸው ግብፅ ጥያቄ ብታቀርብም፣ ኢትዮጵያ ውድቅ አድርጋዋለች፡፡ እነዚህና ሌሎች ውጥረቶች ባሉበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት ወደ ግብፅ ካይሮ አቅንተው፣ ከግብፅ አቻቸው አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የግብፅ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ከአገር ውስጥ ሚዲያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች በተለይም በግብፅ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሌለው ለፕሬዚዳንት አልሲሲ እንዳብራሩላቸውና ፕሬዚዳንት አልሲሲም ሐሳባቸውን እንደተቀበሏቸው ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡

አገሮቹ በሚኒስትሮች ደረጃ የነበረውን የጋራ ኮሚሽን ስብሰባም በመሪዎች ደረጃ ከፍ ለማድረግ መስማማታቸውንና በንግድ፣ በቱሪዝምና በሌሎች መስኮች ግንኙነታቸውን ለማሳደግ መወሰናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፣ ግብፅን በፕሬዚዳንትነት መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲዳብር ሲሠሩ መቆየታቸውን እንደተናገሩ አህራም ኦንላይን የተሰኘው የግብፅ ሚዲያ ዘግቧል፡፡ የዓባይ ውኃ ኢትዮጵያና ግብፅን ያስተሳሰረ ነው እንዳሉ የጠቆመው የመረጃ መረቡ፣ ሁለቱም አገሮች ተጎጂ በማይሆኑበት መንገድ ችግሩ መፈታት እንዳለበት መግለጻቸውን ጠቁሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ካይሮ ሄደው በሁለቱ አገሮች ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ብዙም ትርጉም የሚሰጥ እንዳልሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራ (ሕወሓት) ነገር አባልና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ገብሩ አሥራት በዚህ ጉዳይ ይስማማሉ፡፡ ውይይቱ የግብፅን አቋም ለማለዘብ የተደረገ እንጂ፣ ሁለቱን አገሮች በዋናነት በሚያገናኛቸውና የልዩነታቸው መንስዔ በሆነው የዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ በዝርዝር ተወያይተው ዘላቂ መፍትሔ እንዳላመጡ ተናግረዋል፡፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የዓባይን ወንዝ ማንም ሳይነካው የመጠቀም ፍላጎት ያካተተ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ገብሩ፣ በቀይ ባህር በኩል ያላቸውን ተፅዕኖ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡ ግብፅ በቀይ ባህር አካባቢ እያሳደረችው ስለመጣችው ጉዳይ በጥልቀት እንዳልተወያዩና ለዘላቂ መፍትሔ የሚበጅ ነገር እንደሌለ ጠቁመው፣ ይህ ዓይነቱ ውይይትና ስምምነት ደግሞ ረዥም መንገድ ሊያስጉዝ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህርና የፖለቲካ ተንታኙ ንጋት አስፋው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ውይይት አዲስ ነገር ይዞ እንደማይመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ ከዚህ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ልታገኝ የምትችለው ትርፍ እንደማይኖርም ዶ/ር ንጋት አክለው ጠቁመዋል፡፡

ግብፅ በቀይ ባህር ያለው የጂኦ ፖለቲካ ውጥረት እንዲጦዝና ለኤርትራ ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ውስጣዊ አቋም እንዲዳከም እየሠራች መሆኑን፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

ግብፅ ለኤርትራ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ከማድረጓም በላይ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እንደምትደግፍና እንደምታስታጥቅ በየጊዜው እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ግን የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት ከሚያውኩ ኃይሎች ጋር ግብፅ እንደማታብር ተናግረዋል፡፡

አቶ ገብሩ በፕሬዚዳንቱ ንግግር አይስማሙም፡፡ ‹‹በዲፕሎማሲ ዙሪያ ከአጭር ጊዜ አኳያ የአገሮቹን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ወይም ካለው ልዩነት አንፃር የዚህ ዓይነት አስተያየት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን ግብፅ በወንዙ ላይ የመጠቀም መብት አላት ብሎ የማመን ጉዳይ እስካልመጣ ድረስ እንደ ትክክለኛ ዲፕሎማሲ ፍጆታ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ለማዘናጋት ካልሆነ በስተቀር ምንም ፋይዳ የለውም፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ገብሩ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ የግብፅ ዋነኛ ፖሊሲ የዓባይ ውኃ በኢትዮጵያ ለማንኛውም ፍጆታ ተብሎ መነካት የለበትም የሚል እንደሆነና ይህን ፖሊሲያቸውን ደግሞ መቼም ይቀይሩታል ተብሎ እንደማይታሰብ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት በበኩላቸው፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት ይህን መሰል አስተያየት መስጠታቸው ጊዜ ወስደው ራሳቸውን ለማጠናከርና የኢትዮጵያን አቋም ለማለዘብ ካልሆነ በስተቀር፣ ትርጉም ሊኖረው እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያን የማስፈራርያ ምልክቶች እንደሆኑ ነው ዶ/ር ንጋት የሚረዱት፡፡ ‹‹የግብፅ ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ነው፤›› ሲሉም አይቀበሉትም፡፡

ግብፆች በቀይ ባህርና በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን የቆየ የበላይነት ፍላጎት ለማስቀጠል አሁንም እየሠሩ መሆናቸውን ተንታኞች ጠቁመዋል፡፡ ግብፅና ኤርትራ በአሰብ ወደብ የጋራ የጦር ቀጣና እንዲመሠረትና ይህ ደግሞ የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነትን ምን ያህል ሊያሻክረው እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ግብፅ አሁንም ኢትጵያን ለማጥቃት ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር እንደማታብር ብትገልጽም፣ ከኤርትራ ጋር የውክልና ጦርነት ውስጥ በመግባት ፍላጎቷን የማሳካት ዕቅድ ሊኖራት እንደሚችል የተለያዩ ጉዳዮች አመላካከቶች መሆናቸውን አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡ ግብፃውያን በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ሊገጥሙ እንደማይችሉ የጠቆሙት አቶ ገብሩ፣ በኤርትራ በኩል ግን የውክልና ጦርነት ሊያካሂዱ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያን በእነዚህና በሌሎች መንገዶች ሊያዳክሙ እንደሚችሉ፣ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጦርነት ትገባለች ብለው እንደማያስቡ ግን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በሁለንተናዊ ጉዳዮች ተባብራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ፕሬዚዳንት አልሲሲ መናገራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ ይህን በተመለከተ አቶ ገብሩ ሲናገሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ግብፅን በተመለከተ የምትከተለው የየዋህነት ፖሊሲ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ አድርገው የሚያቀርቡት ደግሞ ግብፅ በተጨባጭ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከሌሎች አገሮች ጋር የጋራ አቋም እንደያዘችና በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት (ተመድ) ማዕቀብ ከተጣለባት ኤርትራ ጋር እንኳ ወዳጅ መሆኗን ሳይቀር ይጠቅሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ራሷ ይህን ጉዳይ እያወቀች ከግብፅ ጋር ግንኙነቴን አጠናክራለሁ ማለቷ ራሱ የውጭ ፖሊሲው ክፍተት አንዱ ማሳያ ተድርጎ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ግብፅ የዓባይን ውኃ እንዳትነኩት እያለች እንደምታንገራግር፣ ኤርትራ ከዓረብ አገሮች ጋር አባሪ መሆኗ እየታወቀ፣ በኢትዮጵያ ላይ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ለመፍጠር ስትሞክር እየታየ ነገሩን በዝምታ የመመልከት ጉዳይ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ገብሩ የኢትዮጵያና የግብፅ መሪዎች ያደረጉት ውይይት በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንዳልሆነ፣ ግብፅ በቀይ ባህር ቀጣናና በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፍላጎት ለማስጠበቅና ኤርትራም ከዚህ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያደርግ እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኤርትራና ግብፅ የሚነጋገሩት ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ገብሩ፣ ግብፅና ኤርትራ ኢትዮጵያን ስለማወክ፣ የህዳሴ ግድቡ እንዳይጣናቀቅ ተፅዕኖ ስለመፍጠርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል፡፡ ግብፅና ኢትዮጵያ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ትርጉም የለውም ሲሉ አክለዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት በበኩላቸው የግብፅና የኢትዮጵያ፣ እንዲሁም የግብፅና የኤርትራ መሪዎች በተገናኙባቸው ጊዜያት የተነጋገሩባቸውና ሊነጋገሩባቸው የሚችሉ ጉዳዮች የተለያየ ክብደትና ቅለት እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡ ግብፅና ኤርትራ የጋራ ጥቅማቸውን በሚያስከብሩ እውነተኛ ጉዳዮች ላይ ሊወያዩ እንደሚችሉ፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ግን ሁለቱ አገሮች አሁን ያለባቸውን የሕዝብ ጫና ለመቀነስ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊኖረው እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡

ግብፅ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የዓለም ባንክ ያደራድረን ጥያቄ ማንሳቷና ኢትዮጵያ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጓ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እዚህ ግባ ሊባል እንደማይችል ተንታኞች አስረድተዋል፡፡ አቶ ገብሩ ሁለቱ አገሮች በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸው የተጠቃሚነት ጥያቄ ዘላቂ መፍትሔ እስካልተሰጠው ድረስ፣ በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሄዳቸው ትርጉሙ አይገባኝም ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ የጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ አሸናፊ ሆና ለመውጣት መንግሥት በዋናነት ውስጣዊ ችግሯን መፍታት እንዳለበትና በዚች አገር ያገባኛል ከሚሉ ወገኖች ጋር መሥራት እንዳለባት አቶ ገብሩ ጠቁመዋል፡፡ ሁለተኛው መፍትሔ ብለው ያነሱት ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲዋን እንደገና መፈተሽ እንደሚጠበቅባት ነው፡፡

ዶ/ር ንጋት ደግሞ አገሪቱ ውስጣዊ አንድነቷንና ጥንካሬዋን በማስጠበቅ፣ የሕዝቡን ጥያቄ በተገቢው መንገድ በመመለስ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተገባውን ቃል ተግባራዊ በማድረግና የውስጥ አቅምን በማጎልበት ለውጭ ተጋላጭ  ያልሆነ አገር መገንባት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነትን በተመለከተ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች የተለያዩ ሐሳቦችን ሲሰነዝሩ ተደምጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የግብፅ ቆይታቸው ጥሩ እንደነበር፣ ከዚህ በፊት የነበሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሁለቱ አገሮች ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በተመለከተ ተቋርጦ የነበረውን ድርድር ለማስጀመርና በቀጣይነት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ከፍ ለማድረግ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የግብፅ የዓለም ባንክ ያደራድረን ጥያቄ ማቅረብ፣ ኢትዮጵያ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጓ ደግሞ አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ እንደሚጠቁም ባለሙያዎቹ አብራርተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጉብኝት የግብፅን አቋም በማስቀየር ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች? ወይስ አትቀጥልም? የሚለው ጥያቄ ወደፊት ምላሹ እንደሚታይ ተንታኞቹ ጠቁመዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -