Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል ባንኮች ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ በማበደር ግማሽ ዓመቱን አጠናቀዋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ አትርፈዋል

በአገሪቱ በተፈጠረው የፖሊቲካና የፀጥታ ችግር ሳቢያ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸው ብቻም ሳይሆን፣ የብድር አሰጣጥ ገደብ መጣሉ የባንኮችን እንቅስቃሴ ክፉኛ እንደፈተነው ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ ይባል እንጂ የአገሪቱ ባንኮች እንደወትሯቸው ውጤታሜ እንቅስቃሴ ከማድረግ ባሻገር በአትራፊነታቸው እንደቀጠሉና ለተበዳሪዎች የሰጡት የገንዘብ መጠንም ጭማሪ ማሳየቱ ታውቋል፡፡

በተለይ በ2010 ዓ.ም. የግል ባንኮች የብድር አሰጣጥ እንደ የኢኮኖሚ ዘርፉ ተጠንቶና ድርሻው ተሰልቶ እንዲቀርብለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስተላለፈው መመርያ የባንኮቹን ውጤታማ እንቅስቃሴ ሊያውክ ይችላል የሚል ሥጋት ሲቀርብበት ሰንብቷል፡፡ ሆኖም እንደተፈራው ሳይሆን፣ የተገላቢጦሹ መታየቱን  የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

የ2010 ዓ.ም. ስድስት ወራት የግል ባንኮች የሒሳብ ሪፖርት ይፋ ተደርጓል፡፡ የዚህ ዓመት ስድስት ወራት አፈጻጸም ከ2009 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ባንኮቹ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡበትና ለብድር ያዋሉት የገንዘብ መጠንም ብልጫ የታየበት እንደነበር አስፍሯል፡፡

የሒሳብ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ በ2010 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ውስጥ 16ቱ የግል ባንኮች የሰጡት የብድር መጠን ከ161.7 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ በግማሽ በጀት ዓመት ውስጥ የተሰጠው የብድር መጠን ከ2009 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ከ55 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ያመላክታል፡፡

ይህ ንጽጽራዊ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ባንኮች ለኢንዱስትሪና ለወጪ ንግድ ዘርፎች ያለገደብ ብድር እንዲሰጡ፣ ለሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች የሚሰጡትን የብድር ገንዘብም በመቶኛ አስልተው ድርሻው ምን ያህል እንደሆነ ተንትነው እንዲያቀርቡ በማሳሰብ የላከላቸው መመርያ፣ እንቅስቃሴያቸው ላይ የተፈራውን ተፅዕኖ እንዳላመጣ በማሳያነት እየቀረበ ነው፡፡

ባንኮቹ ምንም እንኳ የብድር መጠናቸው ማደጉና አሁንም ትልቅ ትርፍ እያስመዘገቡ መቀጠላቸው ቢገለጸም፣ የብድር ገደቡ ግን ተፅዕኖ አላሳረፈባቸውም ማለት እንዳማይቻል የባንክ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አብዛኞቹ ባንኮች ትልቅ ትርፍ ያስመዘግቡበት ለነበረው የቢዝነስ ዘርፍ የሚውለው የብድር መጠን ላይ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ ገደብ የተጣለበት በመሆኑ፣ ለዚህ ዘርፍ ይውል የነበረው ብድር እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ይህ በመሆኑም ባንኮቹ ከዚህ ቀደም ያገኙት የነበረውን ያህል ትርፍ እንዳያገኙ አድርጓል በማለት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ባለሙያዎች አብራርተዋል፡፡ የመመርያው ተፅዕኖ ጎልቶ ሊታይ የሚችለው ከሁለተኛው ግማሽ ዓመት በኋላ ሊሆን እንደሚችልም እነኚሁ ባለሙያዎች አብራርተዋል፡፡  

ይህ ይባል እንጂ የግል ባንኮች እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሁሉ በሥራ አፈጻጸማቸው ዕድገትና ለውጥ በማሳየት በዚህ ዓመትም መቀጠላቸውን የሚያስረዳው  ሌላኛው ነጥብ፣ በግማሽ ዓመቱ ያገኙት የትርፍ መጠን ነው፡፡ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ብልጫ ያለው ትርፍ ማስመዝገባቸውን መረጃው አስፍሯል፡፡ የግማሽ ዓመቱ የሒሳብ ሪፖርት እንዳሰፈረው፣ 16ቱ የግል ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት በጠቅላላው ከ4.7 ቢሊዮን ብር  በላይ ትርፍ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠንም ከ2009 ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ሲታይ፣ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ የታየበት ነው፡፡

በ2009 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ የግል ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት ያገኙት ትርፍ 3.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በግማሽ ዓመቱ ከታክስና ከተቀናሽ ወጪዎች በፊት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በማትረፍ አዋሽ ባንክ በቀዳሚነት ተጠቅሷል፡፡ ዳሸንና አቢሲኒያም ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገባቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

የግል ባንኮቹ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ትልቅ ለውጥ የታየበት ሆኗል፡፡ ከ161.7 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ አሰባስበዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የወጡ መረጃዎች እንደሚየሳዩት፣ በ2008 በጀት ዓመት የመጀመርያው ስድስት ወራት ውስጥ አስመዝግበውት የነበረው ትርፍ ከ3.4 ቢሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡ ይህ የትርፍ መጠን በ2007 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ካተረፉት 2.92 ቢሊዮን ብር አኳያ ሲነፃፀር፣ የ500 ሚሊዮን ብር ገደማ ብልጫ ነበረው፡፡

በ2010 ዓ.ም. የተገኘው የትርፍ መጠን ግን ከ2009 ግማሽ ዓመት አኳያ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው በመሆኑ ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ የትርፍ ዕድገት ታይቶበታል፡፡ የግል ባንኮች የተቀማጭ ገንዘባቸውን የተመለከተው መረጃም በ2010 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት መጨረሻ ላይ የተመዘገበው አኃዝ 231.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያሳያል፡፡

አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈትም የግል ባንኮች በ2010 ዓ.ም. ትልቅ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ ቅርንጫፎቻቸውን ወደ 2,910 ማድረስ ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የ2009 ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ባንኮቹ 956 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈታቸው የአገሪቱ ባንኮችና ቅርንጫፎቻቸው ቁጥር 4,257 ሊደርስ ችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 33 በመቶው በአዲስ አበባ እንደሚገኙ የሚጠቁመው ይኸው መረጃ፣ ዓምና ከተከፈቱት 958 አዳዲስ ቅርንጫፎች ውስጥ 798ቱ በግል ባንኮች እንደተከፈቱ አስፍሯል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 160 ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ከግል ባንኮች በ2009 ዓ.ም. በርካታ ቅርንጫፎችን የከፈተው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ነው፡፡ ባንኩ በ2009 ዓ.ም. ብቻ 103 ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ አዋሽ ባንክ 94፣ ብርሃን 89፣ ዳሸን 83 እንዲሁም አቢሲኒያ 77 ቅርንጫፎችን መክፈታቸው ታውቋል፡፡

በመሆኑም የአገሪቱ ባንኮች ከደረሱበት የቅርንጫፎች ብዛት አኳያ ሲታይ፣ የግል ባንኮች በቅርንጫፎች ብዛት 66.6 በመቶውን እንደያዙም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች