አገር ዓቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአንድ ዓመት ያህል ከኢሕአዴግ ጋር እያደረጉት ካለው ድርድር የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ራሱን እንዳገለለ አስታወቀ፡፡ ኢራፓ ይህንን ያስታወቀው ዛሬ ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ፓርቲዎቹ በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ ለመወያየት በተሰበሰቡበት ወቅት ነው፡፡
‹‹እስካሁን ባደረግነው አጠቃላይ የድርድር ሒደት የምናቀርበው ሐሳብ ተቀባይነት እያገኘ ባለመምጣቱ ኢራፓ እየተካሄደ ካለው የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ራሱን አግልሏል፤›› ያሉት የፓርቲው ተወካይ፣ ከዛሬ በኋላ በድርድሩ ላይ አንገኝም በማለት ከመሰብሰቢያ አዳራሹ ወጥተዋል፡፡
ኢራፓ ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ ውይይት እየተደረገበት ያለውን የፀረ ሽብር ሕግ ሙሉ በሙሉ እንዲቀር አቋሙ እንደሆነ ገልጾ ነው ከድርድሩ ራሱን ያገለለው፡፡