በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የቢጂአይ ምርት በሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ላይ የተጀመረው የቢራ ዋጋ ጭማሪ፣ ከትናንት ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሌሎች የቢራ ፋብሪካ ምርቶች ላይ መተግበር ጀምሯል፡፡
ከሰኞ ታኅሳስ 14 ቀን 2010 ዓ.መ. ጀምሮ የአንድ ሳጥን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ የማከፋፈያ ዋጋ ከ214 ብር ወደ 251 ብር ከፍ ብሎ መሸጥ መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የሐይኒከን ምርቶች በተመሳሳይ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸው መሸጥ ጀምረዋል፡፡ የምርቶቹ አከፋፋዮች እንደገለጹት፣ አንዱን ሳጥን ቢራ በ251 ብር ተረክበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ አንድ ሳጥን ዋልያ ቢራ ይከፋፈል የነበረው በ214 ብር ነበር፡፡
በቢጂአይ ምርቶችና በሐይኒከን ምርቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ተመሳሳይ ነው፡፡
ከሶስት ወራት በፊት የቢራ ፋብሪካዎች በአንድ ላይ አድርገውት የነበረው የዋጋ ጭማሪ፣ በፌዴራል የሸማቾች ጥበቃና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን አግባብነት የለውም ተብሎ ተግባራዊ እንዳይደረግ በተላለፈ ውሳኔ ጭማሪው ሳይደረግ ቀርቷል፡፡
የቢራ ፋብሪካዎች አሁን እያደረጉት ያለው የዋጋ ጭማሪ ከሶስት ወራት በፊት ተደርጎ በነበረው የብር የምንዛሪ ተመን ምክንያት፣ ከውጭ የሚያስመጧቸው የምርት ግብዓቶች ዋጋ በመጨራቸው ሳቢያ እንደሆነ ታውቋል፡፡