የኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን የሚገኘውንና የፌዴራል መንግሥት ተቋም የሆነውን የቂንጢቻ ታንታለም ማዕድን ማምረቻ መዝጋቱ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት መካከል ውዝግብ ፈጠረ፡፡
የማዕድን ማምረቻው እንዲዘጋ የተወሰነው በአካባቢውና በማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው በሚል ምክንያት ቢሆንም፣ ዋና ምክንያቱ ግን የማዕድን ይዞታውን ለአካባቢው ወጣቶች ተሰጥቷቸው ራሳቸው አምርተው በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታስቦ መሆኑን ከሁለቱም ወገኖች ሪፖርተር ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን ላለፋት 28 ዓመታት ማዕድኑን በማምረት ለውጭ ገበያ ሲቀርብ የነበረ ሲሆን፣ ማዕድኑን እዚሁ በማቀነባበርና እሴት በመጨመር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝ የፌዴራል መንግሥት መወሰኑ ይታወቃል። በውሳኔው መሠረትም ኮርፖሬሽኑን የሚቆጣጠረው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የቂንጢቻ ታንታለም ማምረቻን በከፊል ለመሸጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም በክልሉና በኮርፖሬሽኑ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ይህ ጨረታ በወጣበት ወቅት ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚመድብ ያቀረበው የአማራጭ ሐሳብም በዞኑ አስተዳደር ተቀባይነት አላገኘም። ይህንን አጣብቂኝ ሁኔታ ለመፍታትና የቂንጢቻ ታንታለም ማዕድን ማምረቻን ለውጭ አልሚዎች በከፊል ለማዘዋወር የወጣው ጨረታና የተጀመረው ጥረት እንዳይስተጓጎል ለማድረግ የኮርፖሬሽኑ ተቆጣጣሪ የሆነው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር አቶ ግርማ አመንቴ የሚመራ ኮሚቴ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ለማነጋገር መወሰኑን ያገኘናቸው መረጃዎች አመልክተዋል።