መሰንበቻውን የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ከሳቡ በዓላት አንዱ ዓመታዊው የጥምቀት በዓል ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአደባባይ ከሚከበሩት በአውራነትም ይጠቀሳል፡፡ ሃይማኖት ከባህል ጋር የነበረውና ያለው የሚኖረው ቁርኝት አሳይነቱም ይጎላል፡፡ ድንበርን አልፎ ባሕርን ተሻግሮ ባዕዶችን ጭምር የማረከ መሆኑም ሌላው ገጽታው ነው፡፡
የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን መሠረት አድርጎ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣው የጥምቀት ክብረ በዓል ማኅበራዊ አንድነትን፣ መስተጋብርንና ብዝኃነትን በመላ አገሪቱ ያስተሳሰረ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ይህም ገጽታው ነው በመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ክንፍ ዩኔስኮ በማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስና ወካይ መዝገብ ውስጥ የመግባት ዕድሉ ከፍተኛ ነው የሚያሰኘው፡፡
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ጉባዔ በ1996 ዓ.ም. የፀደቀውን የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ ስምምነትን በየካቲት 1998 ዓ.ም. ከፈረመች በኋላ ነው ለዘርፉ ትኩረት መስጠት የጀመረው፡፡ በዩኔስኮ መዝገብ በሚዳሰሱ ቅርሶች ብቻ ትታወቅ ከነበረችበት አልፋ የማይዳሰሰውን ባህላዊ ቅርስ ለማስመዝገብ የቻለችው ስምምነቱን በፈረመች በስምንት ዓመቷ የመስቀል በዓልን በዓለም ወካይ ቅርስ መዝገብ ውስጥ ማስገባቷ ነው፡፡
በተከታታይ ዓመታትም የፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓት በመመዝገባቸው ቁጥሩን ወደ ሦስት አድርሶታል፡፡
በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል ‹‹የአፍሪካ ኤጲፋንያ›› (The African Epiphany) እየተባለ የሚሞካሸው፣ ከአገሬው ባለፈ የውጭ ቱሪስቶች እየመጡ የሚያደንቁት፣ አንዳንዶችም ‹‹በዓለም ወካይ ቅርስ ውስጥ ጥምቀትን ለምን በቅርስነት አላስመዘገባችሁትም?›› እየተባለ የተጠየቀለት በዓለ ጥምቀት እስካሁን ለዩኔስኮ ‹‹ወግ ማዕረግ›› ለመብቃት አልታደለም፡፡
በዓሉ በ2006 ዓ.ም. በተለይ በአዲስ አበባና በጎንደር ሲከበር የቤተክህነትም ሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ ሹማምንት ‹‹ክብረ በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሠራን ነው›› ሲሉ በቴሌቪዥን መስኮት፣ በሬዲዮ ሞገድ መደመጣቸው ይታወሳል፡፡ ከዜና ፍጆታ ባለፈ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ግን ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የመንፈቀ ዓመቱን አፈጻጸም ሪፖርቱን ባለፈው ታኅሣሥ ለፓርላማው ባቀረበበት ወቅት፣ በጥምቀት ክብረ በዓል ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ 70 ከመቶ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወቃል፡፡
ይህም ሆኖ የፎክሎርም ሆነ የአንትሮፖሎጂ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የጥምቀት በዓል እንደ መስቀል በዓል ሁሉ በዩኔስኮ ወካይ ቅርስ መዝገብ ውስጥ ለመስፈር የሚያዳግተው አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ለዩኔስኮ የሚቀርበው ሰነድ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጥናት መደረግ እንዳለበት ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡ እዚህ ላይ ለዕውቀት ክፍተት ማሳያነት በዩኔስኮ የመስቀል ክብረ በዓል አመዘጋገብ ላይ የተከሰተው ይነሳል፡፡
በዩኔስኮ የመስቀል በዓል ቀን ተብሎ የተመዘገበው የቱ ነው?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የመስቀል በዓል በየዓመቱ የሚከበረው መስከረም 17 ቀን (በግብፅ ኮፕቲክ ካሌንደር ቲቶ 17 ቀን) እንደ ጎርጎርዮሳዊ ዘመን አቆጣጠር ደግሞ ሴብቴምበር 27 ቀን ነው፡፡
ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ በውጭ ባሉም መዝገቦች ይታወቃል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ትውፊት የመስቀል በዓል ዋዜማው ደመራ ይባላል፡፡ መሠረቱ ይህ ሆኖ ሳለ ግን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ክብረ በዓሉን በ2006 ዓ.ም. በዩኔስኮ ውሳኔ ሲያስመዘግብ በዋናነት የተጠቀሰው ቀን ‹‹ሴብቴምበር 26›› ተብሎ መስፈሩ ነው ስህተቱ፡፡ በዩኔስኮ ድረ ገጽ የተመለከተው ‹‹The Festival of Maskel is Celebrated across Ethiopia on the 26th of September to commemorate the unearthing of Truth Holy Cross of Christ›› በማለት ነበር፡፡
በግርድፉ ሲተረጎም የመስቀል ክብረ በዓል በመላ ኢትዮጵያ ሴብቴምበር 26 ቀን [ማለትም መስከረም 16 ቀን] ይከበራል ይሆናል፡፡
የመስቀል ዋዜማው መስከረም 16 ቀን አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች ምሽት ላይ ደመራ የሚለኮስበት እንጂ የመስቀሉ በዓል መስከረም 17 ቀን ነው፡፡ በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብና ሰሜን ምሥራቅ አካባቢዎች ደግሞ የመስቀል ደመራው የሚለኮሰው በዕለቱ (17) ንጋትና ረፋድ ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በባሕረ ሐሳቧ መሠረት ሁለት ዓይነት አቆጣጠር አላት፡፡ አንደኛው ፀሐያዊ ቀን (Solar day) ሲሆን፣ ሁለተኛው ሊጡሪጊያዊ ቀን (Liturgical day) ከጨረቃ ጋር የሚያያዘው ነው፡፡ በሊጡሪያጊያዊ ቀን ዕለቱ የሚጀመረው በዋዜማው ከ12 ሰዓት ምሽት በኋላ ነው፡፡ ኦሪቱ እንደሚለው ‹‹ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ አንደኛ ቀን›› ሲል፣ የመስከረም 17 መነሻው መስከረም 16 ማታ ሆኖ ከመስከረም 17 እስከ ማታ 24 ሰዓቱ ይሞላል፡፡ በሊጡሪጊያዊ ቀን ስሌት መሠረት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመስቀል ደመራው የሚለኮሰው ‹‹መስከረም 17 ቀን›› ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ መስከረም 16 ቀን ማታ ሲለኮስ ‹‹በመስከረም 17›› የመጀመርያ ክፍል የሌሊቱ ሰዓት ላይ ሲሆን፣ በጎንደር መስከረም 17 ቀን ረፋድ ላይ የሚለኮሰው ‹‹በመስከረም 17›› ሁለተኛው ክፍል የመዓልቱ (የቀኑ) ብርሃን ላይ ነው፡፡
ይህ በቅጡ ባለመታወቁ፣ የማስመዝገቢያው ሰነድ ሲዘጋጅ ባሕረ ሐሳቡን ማዕከል ባለመድረጉና በዕውቀት ላይ ባለመመሥረቱ በዓሉ ‹‹ሴብቴምበር 26 ቀን በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል›› ተባለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፍተት በጥምቀት በዓል ምዝገባ ላይ እንዳይፈጠር ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
የጥምቀት ክብረ በዓል
በየዓመቱ ጥር 11 ቀን (ጃንዋሪ 19 ቀን) የሚከበረው የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ዋዜማውን ከተራ ጥር 10 ቀን፣ ማግስቱን ጥር 12 እና 13 ቀን አማክሎ የያዘ መሆኑ ሊቃውንት ይገልጻሉ፣ መጻሕፍት ያመለክታሉ፡፡
በዓሉ ‹‹Commemoration of Jesus Christ’s baptism in river Jordan›› (የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት መታሰቢያ በዓል) ከሚባለው በተጨማሪ ‹‹Ethiopian Orthodox Celebration of Epiphany›› የአስተርእዮ፣ የመገለጥ በዓል በመባልም ይታወቃል፡፡የሁለቱ ስያሜዎች ምንነትና ይዘት በቅጡ መገለጽ አለበት፡፡ ዕለተ ጥምቀት ጥር 11 ቀን ሆኖ ኤጲፋንያ (አስተርእዮ) ከበዓለ ጥምቀቱ እስከ ጸመ ነነዌ መያዣ ዋዜማ ድረስ የሚያጠቃልል እንደሆነ ይገለጻል፡፡ የምር ምሁራንን ማነጋገር ከሰሞነኛም መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
አንዱ ማሳያ ባለሥልጣኑ በአማራ ክልል በሠራው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ የታየው ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ በሰሜን ወሎ ዞን በላስታ ላሊበላና አካባቢ ስላለው የጥምቀት በዓል አከባበር በ2009 ዓ.ም. ያሳተመው መድበል ላይ የሚታይ ክፍተት አለ፡፡ ስለ ቅርሱ ምንነት ማብራሪያ ሲሰጥ ‹‹የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ጥምቀት የሚለው ቃል በግእዝ አስተርእዮ፣ በአማርኛ መጠመቅ፣ መገለጥ (መታየት) እንደማለት ነው፤›› ይላል፡፡
ስለሆነም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሙያተኞች ከስያሜ፣ ከይዘትና ከበዓሉ ዕለታት ጋር በተያያዘ ክፍተትም ሆነ ስህተት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያን የጥምቀት በዓል አከባበር ልዩ ገጽታ ከላሊበላ እስከ ጎንደር፣ ከአክሱም እስከ ዝዋይ ተነቅሶ በሰነዱ ውስጥ ማካተት አስፈላጊነት አለው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ከ1979 ዓመታት በፊት የተጠመቀበት ዕለትና ዓመት ልዩ በሆነው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) መሠረት መቼ እንደሆነ መገለጽ አለበት፡፡ ይህም ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (2010-31=1979)፣ 5531 ዓመተ ዓለም (በስድስተኛው ሺሕ) መሆኑን፣ እግረ መንገዱንም የዘመን ቀመሩን ማሳየት ያሻል፡፡
የዘንድሮ በዓል በተለይ በአዲስ አበባ፣ በጎንደርና በመቐለ ሲከበር በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን አግኝቷል፡፡ ከጎንደር ሲተላለፍ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቅ በዓሉ ‹‹1980ኛ ዓመት›› መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህን የሰማ የኢቢሲ ጋዜጠኛ ስለ በዓሉ ሲዘግብ ‹‹በጎንደር ለ1980ኛ ጊዜ›› መከበሩን አስተላልፎ ነበር፡፡ የጥምቀትን አከባበር ለመሰነድ ወደ ጎንደር ያቀናው የባለሙያዎች ቡድን ለዚህ ስህተት ጆሮ እንደማይሰጥ ይታመናል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የገዳ ሥርዓትን በዩኔስኮ ለማሰመዝገብ ሰነዶቹን ከመላኩ በፊት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዕውቀት ተኮር ምክክር እንዳደረገው ሁሉ፣ ስለ ጥምቀት ክብረ በዓል የተሰነዱት ጓዞች ወደ ዩኔስኮ ከመላካቸው በፊት ለምክክር መድረክ እንደሚያቀርበው ይጠበቃል፡፡