ሰላም! ሰላም! ‹ሁዳዴ ከመግባቱ በፊት…› እያለ አንዳንዱ ይኼን ቁርጥ ሲቆርጥ ሳይ ቅበላ እየመሰለኝ ተቸግሬያለሁ። ዳሩ ካላንደር ሳይ ገና ብዙ ቀናት ይቀራሉ። ታዲያ ምንድነው እንዲህ በፆም አሳቦ መፈሰክ እያልኩ ግራ እየገባኝ ነው። አቤት ሆድና ሰው ተባለ። ‹ከውስጥ የሚወጣ እንጂ ወደ ውስጥ የሚገባ ሰውን አያረክሰውም› እንዳላለን ቃሉ ብሎ ብሎ ትዝብትም ወደ ሆድ ገባ። ሰውና አፉ የማይገባበት የለም አትሉም? መቼስ እንደ ዘንድሮ አልተዛዘብንም። ለነገሩ ሁሌም እንደተዛዘብን ነው። ጥሎብን በየዓመቱ ትዝብታችን ከኑሮ ውድነት እኩል ሽቅብ ይነዳል እንጂ። በነገራችን ላይ ‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል› ሆኖ እንጂ የኑሮ ውድነት አልበረደም እሺ። ላስታውሳችሁ ብዬ እኮ ነው። አስታዋሽም ታዋሽም ጠፍቷላ። ሆድ ሆዴን ካለ ድሮስ ማን ማንን ሊያስታውስልህ ኖሯል?›› የሚሉኝ ባሻዬ ናቸው። የሰሞኑን የሥጋ ነገር ዓይተው።
“ሰው ከአምላኩ ዘንድ በሚወጣ ቃል ጭምር እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብለው ቃል ሲጠቅሱ፣ እኔ ደግሞ በእንጀራና በማባያው መሀል ሰፊ ልዩነት እንዳለ መተንተን ጀመርኩ። እንዲያው ለጨዋታ እንጂ ጠበቃ መቆሜ አልነበረም። ባሻዬ ግን ገላመጡኝ። በበኩሌ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ማዕቀብ ሥጋ ላይ ለመጣል ገና ከአሁኑ ይኼን ያህል ጭንቅ ማየቴ ደንቆኛል። ‹ወድቄ ነበር ከእሳት ላይ፣ ሥጋ ሥጋዬን ሳይ› ያሉት መነኩሴ ወደው አይደለም ስል ነበር። ከሁሉ ከሁሉ ድንቅ ድንቅንቅ ያለኝ ይኼን ያህል ሰው የሥጋ ፍቅር ካለው ምቀኝነት፣ ትዕቢት፣ ፀብና ጥላቻ ለምን ተበራከቱ የሚለው ጥያቄ? የጥያቄና የጠያቂ ትንሽ የለውም የሚሉት ባሻዬ እንዲህ ስል ሰምተው፣ “አይ አንበርብር ሞኙ ፍቅር እኮ ከነፍስ ናት። ሥጋ ግን የሥጋ ነው። ዘንድሮ መንፈሱን በመንፈስ የሚመግብ ሰው ቁጥር አንሷል። ሥጋ ሥጋውን ሲመግብ እያየህ ከዚህ በላይ ጉድ አለመታዘብህም ፈጣሪ በዙፋኑ ላይ ቢኖር ነው?” ብለው አበረዱኝ። ባሻዬ እኮ ነፍስ ነገር ናቸው!
ጨዋታ እንደ አጨዋወቱ አይደል? ያው አላድለን ብሎ የእኛ ሻምፒዮንስ ሊግ ወሬ ነው። ወሬም አያልቅብን እኛም አይደክመን ይኼው ይዘነዋል። እና ዛሬ የማጫውታችሁ በሆድ ዙርያ ይሆናል። ተረቱ ‹ሆድ ካገር ይሰፋል› ይላል። ዛሬ ላይ ቆማችሁ ልትተረጉሙት ካሰባችሁ ማበዳችሁ ነው። ምክንያቱም ቻይነትና ታጋሽነት፣ ለመስማት መፍጠን፣ ለመናገር መዘግየት ደብዛቸው ጠፍቷል። ባንመዘገብም እያንዳንዳችን የወሬ ጣቢያ አለን። የወሬ ስላችሁ ይገባችኋል ብዬ ነው። እና እኔ የተነቋቋሪውን ብዛት፣ የአጥፍቶ ጠፊውን ቁጥር ቁጭ ብዬ ሳሰላ መቼ ይሆን የሚሰለቸን ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር አወራዋለሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ለዛው ሳይሟጠጥ ይቀጥልልኛል። ‹‹መቼ ይሆን የምንጠግበው አትልም? ሆድ ካገር ይሰፋል የሚለው ተረት እኮ ሲተረት መብልን ማዕከል አድርጎ ሳይሆን ወሬንም ነው፤›› አለኝ። ደርሶ ግራ ሲያጋባኝ ፊቴ ሲጠይም ደስ ይለው የለ? ምንድነው የምታወራው?›› ስለው፣ ‹‹በዚህ በኖርከው ዕድሜ ቢያንስ እንዴት ይኼ አልተገለጠልህም?” ብሎ አሁንም ወደኔ አፈጠጠ።
ይኼ ሰው እንዴት ነው ነገሩ? ስላፈጠጡና ስላጉረጠረጡ ብቻ እንደመጣለን ብለው ከሚያስቡት ወገኖች ዘንድ መዋል ጀመረ እንዴ? እያልኩ፣ ‹‹በላ ግለጥልኝ…›› ስለው “የዘመኑን ፈሊጥ ታውቃለህ? ዋናው ድፍረት ይሰኛል። ድፍረት ምንድነው ብትል፣ ድፍረት በዘመኑ መዝገበ ቃል አፈታት ማንበልብል መቻል ማለት ነው። ስለዚህ መማር ድሮ ቀረ። እውቀት አፈር ቃመ። ዋናው ድፍረት ነው። ድፍረት ያበላል ሲሉህ በአጭሩ ወሬ መቻል ማለት ነው። ልብ አድርግ ማንበልብልና አንደበተ ርዕቱነት የትናየት ናቸው። ስለዚህ ተረቱ ሲተረት ይኼን ዘመን ዓይቶ ነው በሚለው መስማማት አለብህ። በዚህ ከተስማማህ ብዙ አገር ሻጭ፣ ብዙ ክብር ሻጭ፣ ብዙ እምነት ሻጭ ስታይ የሆድ ነገር በሆድ ብቻ እንደማይፈታ ሳታልመው ሊፈታልህ ይገባል። ስለዚህ…›› ብሎ ምን ብሎ ቢቋጨው ጥሩ ነው፣ ‹‹ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በወሬም እንጂ!” ሲለኝ ወይ አገርና ሆድ አያ!
ዛሬ እንዲህ ስለሥራ ውጣ ውረድ በየመሀሉ ጣልቃ ሳላስገባ የባጥ የቆጡን የምቀደው ለካ ምን ሆኜ እንደ ሰነበትኩ አልነገርኳችሁም? የእኔ ነገር! የሚያዝል፣ የሚያዞር፣ ካልጋ ከወረዱ የሚጥል ወረርሽኝ (ደግሞ ይኼንንም በዓለም አንደኛና ብቸኛ ካላስባለን እንዳንል እንጂ) ጉንፋን አሞሃል ተብዬ የሰነበትኩት አልጋዬ ላይ ነው። ያው ስልኩ ስላለ አንዳንዴ ሲሻለኝ በስልክ የምሸቅለው እንዳለ ነው። ታዲያ ልምከራችሁ? ምንም ቢሆን በዚህ ጊዜ መያዝ የለባችሁም። እኔ በፖሊስ አላልኩም በበሽታ ነው! ኧረ እባካችሁ እያጣራችሁ ስሙ። ምርጫ በማጣራት የዛሉት አንሷቸው ወሬ አጣሩልን ብለን የአውሮፓ ኅብረትን ማስቸገር እኮ ነው የቀረን። ታዲያላችሁ አንድ ወዳጄ ደውሎ፣ “ያንን ቤት ላሳይልህ ሰዎች አግኝቻለሁ፤” አለኝ። ባለሁለት ፎቅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ነው። “ጥሩ አሳያቸውና መልሰህ ደውል፤” ብዬው እኔ በቴሌቪዥን የአሜሪካንን ጉድ እኮመኩማለሁ።
ለካ እዚያም መንግሥት ሥራ ያቆማል። ያውም ሁለት ሳምንት። ደግሞም የሚወዱትም የማይወዱትም አሉ። እነሱም ወግ ደረሳቸውና ይኼው መከፋፈልን እየቀመሷት ነው። እሰይ ባይባልም መቼስ አንዳንዱን ነገር ካላዩት አይረዱትምና ሰሞኑን ያለቅጥ የትራምፕ ደጋፊ ሆኛለሁ። በሁለት አፍ ማውራትና የቋንቋ መደበላለቅ በእነ አሜሪካ እልፍኝ ተቀጣጥሎ ሳይ የአፍሪካ አምላክ እላለሁ። ለካ የእነሱም ዴሞክራሲ የጭንቅ ቀን ለገላጋይ ይከብዳል? እነዚህ ሰዎች በመረጡት ፕሬዚዳንት ያውም ገና በዓመታቸው እንዲህ ከሆኑ ውኃ ቢሄድባቸው፣ ሙስና ቢደቁሳቸው፣ በየሄዱበት ቢሮ ስብሰባ ላይ ናቸው ቢባሉ አሜሪካ የምትባል አገር ከዓለም ካርታ ላይ ልትጠፋ እንደምትችል አሰብኩ። “አወይ ሥልጣኔ! እውነት የምር የሠለጠነችው ሥልጣኔ፣ ከግጭትና ሁከት በላይ ክንፍ አውጥቶ የበረረ ሕዝብ ያዘለችው ሥልጣኔ መገኛዋ የት ይሆን?” ስል ማንጠግቦሽ ሰምታኝ፣ “አርፈህ ጉንፋንህን አታስታምም? በሰው ክርክር ምን ጥልቅ አደረገህ?” ብላ ተቆጣችኝ። ስልኬ አልጠራም። ወዲያው ጭልጥ አድርጎ እንቅልፍ ወሰደኝ። ማንጠግቦሽ ‘አያገባህም’ ብላ ዝም ብታስብለኝም፣ በህልሜ ጭራሽ ‘ቪዛ’ ተመቶልኝ ትራምፕ ኤርፖርት ጠብቀው አትገባም ሲሉኝ አየሁ። ያኔ ስነቃ ኢትዮጵያ ነኝ። “ዌል ካም ቱ ሪያሊቲ” አትሉም!
በሉ እንሰነባበት። ሰሞነኛው ወሬ በዝቶብኝ ግራ ገብቶኛል። በተለይ የሐይቲና የአፍሪካ የትራምፕ ሽሙጥ ከጉንፋኔ ጋር ተዳብሎ ሲያሳስበኝም ሰንብቷል። ከደጋፊነት ወደ ተቀናቃኝነት የወሰደኝ ጉዳይ ሆኗል። ታዲያ አመፃዬን በአልኮል ካልሆነ በምን እገልጻለሁ ብዬ ጉንፋኔ እስኪሻለኝ ጠበቅኩ። ታዲያ አንድ ወዳጄ፣ ‹‹የዘንድሮ ጉንፋን እኮ እንደ ድሮው በማርና በነጭ ሽንኩርት አይለቅህም፤›› አለኝ። ‹‹ታዲያ በምንድነው?›› ስለው፣ ‹‹በአልኮል ብቻ ነው የሚለቀው›› አይለኝ መሰላችሁ? ልሞክረው ብዬ ሞክሬው ሲሠራ ሳይ ደነገጥኩና በዚህ ዓይነት ነገራችን ሁሉ አልኮል አልኮል እየሸተተ፣ ቤንዚን ቤንዚን እየሸተተ እንዴት ልንሆን ነው ብዬ ሳስብ ክው አልኩ። “ከላይ እሳት ከታች እሳት ሆኖብን ምን ልንሆን ነው?” የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ይኼን ስነግረው፣ “ከውስጥም እሳት ከውጭም እሳት ሆነ በለኛ፤” አለኝ። ባሻዬ ደግሞ በበኩላቸው፣ “እንግዲህ ዘመኑ ቀርቧል። በልዩ ልዩ ሥፍራ የመሬት መናወጥ ይሆናል ይላል ቃሉ። አርፋችሁ በጊዜ ንስሐ ግቡ፤” ይሉናል ይኼን የሰሞኑን እሳተ ጎሞራ እያዩ።
ማንጠግቦሽ በፈንታዋ፣ “እሱ ካመጣው ምን ልታደርግ ነው? እሳት እንደ ውኃ አይገደብ?” ትለኛል። በየአቅጣጫው አስተያየቱ ሲበዛብኝ ብቻዬን ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ እጓዝና እቆዝማለሁ። እዚያም አመሻሽቶ ሰው ሞቅ ሲለው የሚያወራው ስለዚሁ ነው። አንዱ እንዲህ ይላል፣ “እኔ በጣም የማዝነው ግን ይኼን የመሰለ ታላቅ ክስተት እየተከናወነ፣ እኛ ግን ልባችን ያለው የማድሪድ ቀጣይ አሠልጣኝ ማን ይሆናል የሚለው ላይ ነው፤” ይላል። ሌላው ቀጠል አድርጎ፣ “ታዲያ ከዚህ በላይ ምን እንድናስብ ፈለግክ? በሰው አገር ቡድን፣ በሰው አገር መሪ ምርጫ ላይ ልባችንን በማሳረፋችን መሰለኝ ይችን ታህል የሰነበትነው?” ይለዋል። የኤርታሌው ጎሞራ ሲገርመኝ ደግሞ በዚህ በኩል ሌላ የነገር ጎሞራ ሲፈነዳብኝ ሒሳቤን ከፍዬ ውልቅ። በአልኮል ላይ አልኮል ስንደባልቅ አንዱ ክብሪት ቢለኩስ ምን ልንሆን ነው? መሸሽ ነው እንዳትሉኝ ብቻ፡፡ ለመሸሽም እኮ የተከፈተ በር ያስፈልገናል፡፡ ማን ነበር በሩ ሲዘጋ መስኮት በር ይሆናል ያለው? መልካም ሰንበት!