Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሙስናን በጥበብ መዋጋት

ሙስናን በጥበብ መዋጋት

ቀን:

ፒላቶ በሚል የመድረክ ስሙ የሚታወቀው ዛምቢያዊው አቀንቃኝ ፉምባ ቻማ የዛምቢያውን ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉና የፖለቲካ ፓርቲያቸውን የሚተች ‹‹ኮስዌ ሙምፓቶ›› የተሰኘ ዘፈን የለቀቀው በቅርቡ ነበር፡፡ ‹‹በማሰሮ ውስጥ ያለ አይጥ›› የሚል ትርጓሜ ያለው ዘፈኑ እንደተለቀቀ በመላው አገሪቱ ይደመጥ ጀመር፡፡

በዘፈኑ፣ የአገሪቱ ፖለቲከኞች እንደ አይጥ ምግብ ብቻ ሳይሆን የማይጠቅሙ ነገሮችንም ከሕዝቡ እየሰረቁ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ዘፈኑ በሬዲዮና ቴሌቭዥን ከመቅረቡ ባሻገር ፒላቶ በተለያዩ መድረኮች እንዲያቀነቅነው ተጠይቋል፡፡ ነገሩ ያልተዋጠላቸው የአገሪቱ አመራሮች ዘፈኑ በመገናኛ ብዙኃን እንዳይሰራጭና ፒላቶም ኮንሰርቶቹን እንዲሰርዝ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡

ሙዚቀኛና የመብት ተሟጋቹ ፒላቶ፣ ዘፈኑን ከለቀቀ በኋላ በርካታ ማስፈራሪያዎች ደርሰውታል፡፡ ዘፈኑ በአገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማንፀባረቁ ዛምቢያውያን ቢደሰቱም ፖለቲከኞቹ የዘፈኑን መልዕክት ለማዳፈን ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ፒላቶ ከአመራሮቹ የሚደርሰው ማስፈራሪያ እየተባባሰ ሲሄድ አገሩን ጥሎ መሰደድ ግድ ሆነበት፡፡ በአሁን ወቅትም በስደት ላይ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለጻቸው ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ የገጠማቸው አርቲስቶች ብዙ ናቸው፡፡ ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍና ፎቶግራፍ ማኅበረሰባዊ መልዕክት ከሚተላለፍባቸው የጥበብ መንገዶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስላሉ ችግሮች ግንዛቤ ለመፍጠርና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከትም ጥበብን የሚገለገሉ አርቲስቶች በርካታ ሲሆኑ፣ በሥራዎቻቸው አማካይነት ለውጥ ለመምጣት ይተጋሉ፡፡

አርቲስቶች መልዕክት አዘል የጥበብ ውጤት ሲያቀርቡ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኙም ሥራቸው አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም፡፡ በተለያዩ አገሮች ሥራዎቻቸው የታገዱባቸው እንዲሁም ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉ አርቲስቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ሆኖም ስለ ነጻነት፣ ፍትሕና እኩልነት የሚሰብኩ ሥራዎቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡

አርቲስቶች ለማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ የሚያመላክቱ ሥራዎች በማበርከት እንዲገፉበት የሚያበረታታው አፍሪካን አርቲስት ፒስ ኢንሽየቲቭ (ኤኤፒአይ) የተመሠረተው ከአምስት ዓመት በፊት ነው፡፡ አርቲስቶችና የመብት ተሟጋቾች በጥምረት የሚሠሩበት ሲሆን፣ ሠዓሊዎች፣ ዲዛይነሮች፣ ገጣሚዎች፣ ተዋናዮች፣ ዘፋኞች፣ ጸሐፊዎችና ከጥበቡ ውጪ ባሉ ሙያዎች የተሰማሩ የሐሳቡ ተጋሪዎች ስብስብ ነው፡፡

ኤኤፒአይ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ቅርንጫፍ ያለው ሲሆን፣ ጥበብና መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም በአፍሪካ ሰላም እንዲሰፍን እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በ45 አገሮች እንቅስቃሴውን ከማስፋፋቱ ጎን ለጎን፣ አፍሪካ ውስጥና ውጪም የሚኖሩ 15,000 አባላት አፍርቷል፡፡ 90 ታዋቂ አርቲስቶችም ‹‹የሰላም አምባሳደር›› በሚል የንቅናቄው ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ድርጅቱ አራተኛውን የአፍሪካ አርቲስቶች የሰላም ፎረም በአዲስ አበባ ማካሄድ የጀመረው ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በሞሞና ሆቴል ነበር፡፡ ‹‹ቢውልዲንግ ኦን አክሽን ፋክተሪ ፎር አንቲ ኮራፕሽን ኢን አፍሪካ›› በሚል ለአምስት ቀናት ዘልቋል፡፡ የዘንድሮው መወያያ አጀንዳ ሙስናን በመዋጋት ዙሪያ እየተደረገ ያለውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ አጀንዳ ትኩረት በመከተል መሆኑን አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የዘንድሮው መወያያ ‹‹ዊኒንግ ዘ ፋይት አጌንስት ኮራፕሽን፤ ኤ ሰስቴነብል ፓዝ ፎር አፍሪካስ ትራንስፎርሜሽን›› የሚል መሆኑ ይታወቃል፡፡

በፎረሙ ከዑጋንዳ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጋምቢያና ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ የፈጠራ ሥራዎችን በመጠቀም ሙስናን እንዴት መዋጋት ይቻላል? በሚለው ርዕሰ ጉዳይም ተወያይተዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ ጸሐፊዎች፣ ሙዚቀኞችና ሌሎችም ጠቢባን፣ ሙስናን ጨምሮ የአንድ አገር ዕድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመዋጋት ጥበባዊ ሥራዎች የላቀ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች ውስጥ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥበባዊ ሥራዎች የሠሩ ይገኙታል፡፡ በየአገራቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ጥበብን መልዕክት ለማስተላለፊያነት የሚገለገሉ አርቲስቶችን አሰባስበው ማኅበር የመሠረቱም ይገኙበታል፡፡ ተሳታፊዎቹ ስለየመጡበት አገርና ስለሥራቸው ንግግር ሲያደርጉ፣ ሙስና የአፍሪካውያን ራስ ምታት ከሆኑ ችግሮች በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል፡፡ የየአገራቸውን ተሞክሮ በመመርኮዝም ጥበብ ችግሩን ለመቅረፍ ያለውን ሚና ተናግረዋል፡፡

በስብሰባ፣ በኮንፈረንስና መሰል የውይይት መድረኮች ሙስና እያሳደረ ስላለው ተፅዕኖ ይነገራል፡፡ መደበኛ ውይይቶች ችግሩን ለመቅረፍ አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም፣ ጥበባዊ ሥራዎች ለሰው ልጅ ስሜት ቅርብ እንደመሆናቸው የሚያስተላልፉት መልዕክት የበለጠ ተደማጭነት ያገኛል፡፡ በመደበኛ ውይይት ከሚተላለፈው መልዕከት የጥቂት ደቂቃዎች ዘፈን፣ አጭር ፊልም ወይም ፎቶግራፍ የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝም ይችላል፡፡

ስለዚህም ጥበባዊ ሥራዎች የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያመላክቱና ንቃተ ሕሊናን የሚያጎለብቱ መሆን እንዳለባቸው በፎረሙ ተገልጿል፡፡ ተሳታፊዎቹ  በየተሰማሩበት ሙያ ዘርፍ ለችግሩ መፍትሔ ስለሚሰጥበት መንገድ ተናግረዋል፡፡ ገጣሚዎቹ ችግሩ ይቀረፋል ብለው የሚያምኑባቸውን ነጥቦች በስንኝ ሲያስቀምጡ፣ ሙዚቀኞቹ ኖታ ቀምረዋል፡፡ የፈጠራ ሰዎች መልዕክት አዘል ሥራዎችን ለማኅበረሰቡ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተመልክቷል፡፡

የኤኤፒአይ ዋና ዳይሬክተር ኢብራሒም ሴሰይ እንደሚናገረው፣ በአፍሪካ ውስጥ ላሉ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ሒደት ውስጥ የአፍሪካ አርቲስቶች የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹አፍሪካን አርቲስት አጌነስት ክላይሜት ቼንጅ›› በሚል አፍሪካውያን አርቲስቶች የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከቱ ጥበባዊ ሥራዎች እንዲያቀርቡ ቅስቀሳ መደረጉን ያስታውሳል፡፡ በአህጉሪቷ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍንም የተለያዩ ጥበባዊ ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል፡፡

‹‹ጥበብ ለማኅበረሰባዊ መልዕክቶች ጉልበት ይሰጣል፡፡ ኅብረተሰቡ ለመልዕክቶቹ ትኩረት እንዲቸርም ያግዛል፤›› በማለት ኢብራሂም ያስረዳል፡፡ መገናኛ ብዙኃንና ጥበባዊ ሥራዎች በጋራ ለለውጥ እንደሚያነሳሱም ያክላል፡፡ ተቋሙ ከአፍሪካ ኅብረት የወጣቶች ክፍል ከተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እና ሌሎችም ሐሳቡን የሚደገፉ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ይሠራል፡፡

ኢብራሂም እንደሚለው፣ ‹‹የሰላም አምባሳደር›› በሚል የተመረጡ ታዋቂ አርቲስቶች የሚያበረክቱት አስተዋፅኦም ቀላል አይደለም፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ተደማጭነት ስላላቸው፣ የአንድን አገር ችግር ለመፍታት ሥራዎቻቸውን እንደ መሣሪያ መጠቀም ይችላሉ፡፡ ከኤኤፒአይ አምባሳደሮች መካከል ፀደኒያ ገብረማርቆስ፣ ሲድኒ ሰሎሞን፣ ክሪቲካል (ከኬንያ)፣ የቭስ ካሚክዌ (ከብሩንዲ) እና ጊላድ ሚሎ (ከኬንያ) ሥራዎቻቸውን በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ አስደምጠዋል፡፡

በዘንድሮው ፎረም ‹‹ሲኒማ ፎር ፒስ›› (ሲኒማ ለሰላም) በሚል ‹‹93 ደይስ›› (ከናይጄሪያ)፣ ‹‹አይ ሻት ቢ ኪዲዴ›› (ከታንዛኒያና እንግሊዝ) እና ‹‹ዌልካም ቱ ዘ ስማይሊንግ ኮስት›› (ከጋምቢያ) ይታያሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የፎረሙ ተሳታፊዎች ማኅበራዊ መልዕክት ያላቸው ግጥሞችና ሙዚቃም ፎረሙ በተካሄደበት አዳራሽ አስደምጠዋል፡፡ ይኼም በፎረሙ ለውይይት የቀረበው ጉዳይ በእውን በጥበብ የተገለጸበት ነበር፡፡

በፎረሙ የየአገራቸውን ተሞክሮ በማቅረብ፣ ጥበብ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ቦታ ካሳዩ መካከል የአይቮሪኮስት ተወካይ ይጠቀሳል፡፡ በተጨማሪም ከጋምቢያ፣ ከዩጋንዳ፣ ከሞዛምቢክና ከዛምቢያ የተውጣጡ የኤኤፒአይ ተወካዮች ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡ ብዙኃኑ ጥበብ የለውጥ መሣሪያ ስለመሆኑ በመስማማት፣ በተለይም ወጣት አርቲስቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

በተሳታፊዎቹ ከተነሱ ነጥቦች መካከል አፍሪካ ውስጥ ጥበብን ለማኅበረሰባዊ ለውጥ መጠቀም በፈተና የተከበበ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ መንግሥታት ለጥበብና ባህል ዘርፍ በቂ ድጋፍ ካለማድረጋቸውም በላይ መልዕክት አዘል ሥራዎች አይበረታቱም፡፡ የአርቲስቶች የመናገር መብት ከመገደቡ ባሻገር አርቲስቶቹ በሥራዎቻቸው ጫና ይደርስባቸዋል፡፡ ማነቆውን ከግምት በማስገባት፣ ‹‹ውጣ ውረድ ቢኖርም ያመናችሁበትን ከማድረግ ወደ ኋላ አትበሉ፤›› የምትለው ደስታ መግሆ (ዶ/ር) ናት፡፡

ዶ/ር ደስታ ሠዓሊዎችን፣ ሙዚቀኞችን በማማከርና በመወከል ሥራዋ ከምትደሰትባቸው ነገሮች፣ ጥበብ ለማኅበረሰባዊ ጉዳይ ሲውል መመልከት መሆኑን ትናገራለች፡፡ ‹‹ሥነ ግጥም፣ ሥነ ጥበብና ሙዚቃ ጉልበት አላቸው፤›› ትላለች፡፡ ሙዚቃን ለፍትሕና ነፃነት መልዕክት ለማስተላለፊያነት ከተጠቀሙ መካከል የምትጠቅሰው ቦብ ማርሌን ነው፡፡ ሙዚቃዎቹ በድንበር ሳይገደቡ የመላው ዓለም ሕዝብን ስለእኩልነት በመስበክ ዘመናት ተሻግረዋል፡፡

‹‹ሰዎች ለጥበብ ቶሎ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ከአንድ ንግግር ይልቅ መድረከ ላይ የቆመ ገጣሚና ሥራዎቹን የሚያሳይ ሠዓሊ ተቀባይነት አላቸው፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡ ጥበባዊ ሥራዎች ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ የማድረግ ኃይል እንዳላቸውም ታክላለች፡፡ የተለያዩ አጀንዳዎችን ወደ መድረክ በማምጣት፣ የውይይት መነሻ በማድረግ ጥበብ የተሻለ አማራጭ እንደሆነም ታስረግጣለች፡፡

በውይይቱ ተሳታፊዎች ከተነሱ ነጥቦች መካከል ‹‹ጥበብ ሰዎች ማኅበረሰቡን መምራት አለባቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡ ጥበብና የመብት አቀንቃኞች ጎን ለጎን መራመድ እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡ ‹‹ጥበበኞች የሚያስተላልፉት መልዕክት፣ ማኅበረሰቡን የሚቀሰቅስና ለለውጥ የሚያነሳሳ መሆን ይገባዋል፤›› ሲሉ አስተያየት የሰነዘሩም ነበሩ፡፡

‹‹ጥበበኞች ቀና መልዕክትን ለመጪው ትውልድ የማሻገር ኃላፊነት አለባቸው፤›› ያሉም ተደምጠዋል፡፡ በተለይም ወጣት አርቲስቶች የለውጥ ኃይል በመሆን፣ መንግሥትና ኅብረተሰቡንም መሞገት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣትና የመፍትሔ አቅጣጫ መጠቆምም ከግዴታዎቻቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡  

የኤኤፒአይ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሌንሳ ቢየና እንደምትናገረው፣ በፎረሙ በየዓመቱ በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄዱ ውይይቶችን ተመርኩዞ ርዕሰ ጉዳይ ይመረጣል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ የጥበብ ሰዎችን የሚወክል አካል ባለመኖሩ ሐሳባቸውን ለማስተጋባት ፎረሙን ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ዓመቱን የፀረ ሙስና ዓመት ብሎታል፡፡ በኤኤፒአይ የሚካሄደው ውይይትም ሙስናን በጥበብ ስለመዋጋት ያወሳል፡፡

ሌንሳ እንዳለችው፣ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ያልፀደቁ ባህል ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎች በምን መንገድ መጽደቅ እንዳለባቸው ውይይት አድርገው ለአፍሪካ ኅብረት ግብዓት ይሰጣሉ፡፡  በተጨማሪም አርቲስቶች ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ጥበባዊ ሥራዎች እንዲያበረክቱ ቅስቀሳ ያከናውናሉ፡፡

‹‹ፊልም ሠሪዎች፣ ሙዚቀኞችና ሌሎችም ባለሙያዎች በማኅበራዊ ጉዳዮች የሚያተኩሩ ሥራዎች እንዴት እንደሚያቀርቡ የሚያመለክቱ ውይይቶች ይካሄዳሉ፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የውይይት መነሻ የሚሆኑ አጀንዳዎች ከመሪዎች በዘለለ ወደ ሰፊው ሕዝብ ሲወርዱ አይስተዋልም፡፡ ለሕዝብ ልብ ቅርብ በሆኑ ጥበባዊ ሥራዎች ይኼንን ክፍተት መሙላት እንደሚቻል ታምናለች፡፡

ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት ፎረሞች የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ትኩረት የነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች የፎረሙ አባላትም መወያያ ሆነዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊ አርቲስቶች ጥበባዊ ሥራዎቻቸውን ከርዕሰ ጉዳዮቹ ጋር አስተሳስረዋል፡፡ በየአገራቸው ያሉ አርቲስቶች ለውጥ ተኮር ሥራዎችን እንዲያቀርቡም አነሳስተዋል፡፡ ‹‹አርቲስቶች ለሕዝብ ቅርብ በሆኑ ሥራዎቻቸው ማኅበራዊ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር የሚያስተሳስሩ ድልድዮች ናቸው፤›› ስትል ታስረዳለች፡፡ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ለአምባሳደርነት የሚመረጡ አርቲስቶች በሥራዎቻቸው ማኅበራዊ ችግሮችን በመዳሰስ መፍትሔ እንደሚያመላክቱም ታክላለች፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ተስፋ የተጣለባቸው የንግድ ማዕከላት

ፆም ሲገባ ዋጋቸው ከሚጨምሩ የምግብ ፍጆታዎች ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ ...

የወጣቶችን ፈጠራ የሚያስቃኘው የስታርት አፕ ዓውደ ርዕይ

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ...

በግጭት ለተጎዱ ልጆች 80 ሺሕ መጻሕፍት ማሠራጨት መጀመሩን ኢትዮጵያ ሪድስ አስታወቀ

በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት ከትምህርት ቤት ለተስተጓጐሉ፣ በሥነ ልቦናና በሌሎች...

የም እና መስህቦቿ

በቱባ ሀገሬ የም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ በ239...