- 379 ቤቶች በፍርድ ቤት ዕግድ ምክንያት አልተነሱም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 78 ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ አምስት ነባር መንደሮችን ለማፍረስ፣ ከተነሺዎች ጋር ውይይት ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ፣ ቀደም ብለው ከተካሄዱ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች በተሻለ የተነሺዎችን መብት እንደሚያስከብር አስታውቋል፡፡
የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው ሙሉ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ከተነሺዎች ጋር ውይይት ማድረግ ይጀምራል፡፡
በ2010 ዓ.ም. ሁለተኛው ግማሽ ዓመት ይፈርሳሉ የተባሉት በአራዳ ክፍለ ከተማ አሜሪካ ግቢ ቁጥር ሁለትና ገዳም ሠፈር፣ በየካ ክፍለ ከተማ ከሾላ እስከ መገናኛ ድረስ፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ጌጃ ሠፈር፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንቺስ ቁጥር ሦስት ቶታል ነዳጅ ማደያ አካባቢ ያሉ መንደሮች ናቸው፡፡
አቶ ሚሊዮን እንደሚሉት፣ በልማት ምክንያት ከቦታቸው የሚነሱ ተነሺዎች የካሳ መጠን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ተመጣጣኝ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተነሺዎች አቅሙ ካላቸውና ቦታቸው በማስተር ፕላኑ ለሌላ አገልግሎት የማይፈልግ ከሆነ፣ እዚያው በአካባቢያቸው መልሰው እንዲያለሙ ዕድል ይሰጣል ብለዋል፡፡
ኤጀንሲው እንደ አዲስ በቅርቡ ከሚጀምረው የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት በተጨማሪ፣ ቀደም ብለው የተጀመሩ ነገር ግን ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ቅሬታ በማንሳታቸው ለጊዜው እንዲቋረጡ የተወሰነባቸውን ቦታዎች ባለፉት ስድስት ወራት በድጋሚ ከሰው ንክኪ ነፃ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
እነዚህ ቦታዎች የሚገኙት በአራዳ ክፍለ ከተማ ባሻ ወልዴ ቁጥር ሁለት፣ አሮጌው ቄራ ቁጥር አንድና ሁለት፣ ፓርላማ አካባቢና ደጃች ውቤ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አፍሪካ ኅብረት ቁጥር ሁለት፣ ካዛንቺስ ቁጥር ሁለትና ፈለገ ዮርዳኖስ፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ዙርያ፣ ሰንጋ ተራ ቁጥር ሦስት፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አሜሪካ ግቢ ቁጥር አንድ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ የእነዚህ ቦታዎች ስፋት 214 ሔክታር ሲሆን፣ ባለፉት ስድስት ወራት 186 ሔክታር ላይ ካረፉ 12,085 ቤቶች ውስጥ 11,673 የሚሆኑት መነሳታቸውን በኤጀንሲው ሪፖርት ቀርቧል፡፡
ነገር ግን 379 ቤቶች በይገባኛልና በፍርድ ቤት ዕግድ ምክንያት በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ሊነሳ እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡
አቶ ሚሊዮን እንደገለጹት፣ በይገባኛልና በፍርድ ቤት ዕግድ ምክንያት ሊነሱ ያልቻሉ ቤቶች መልሶ ማልማቱን በተያዘለት ጊዜ ገደብ ለማካሄድ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ስለሆነም የፍትሕ ሒደቱን የተፋጠነ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ አማካይነት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራዎች ተጀምረዋል ብለዋል፡፡