Monday, July 15, 2024

ጽንፈኝነት ለማንም አይበጅም!

ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አገር ናት፡፡ ከብሔር ማንነት ጀምሮ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና የመሳሰሉ በርካታ መገለጫዎች ባሉባት በዚህች ታሪካዊ አገር ውስጥ የአንድ ጎራ ኃያልነት ወይም የበላይነት ከቶውንም ሊኖር አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ዘመናት በተነሱ ገዥዎች ሥር ቢተዳደርም፣ ደጉንና ክፉን ጊዜ ያሳለፈው ግን ተሳስቦና ተደጋግፎ መሆኑን ፈጽሞ መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ አገሩን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች በአንድነት ሲጠብቅ ዘመናትን ያሳለፈው፣ ከልዩነት ይልቅ ለአንድነት ትልቅ ግምት በመስጠቱ ነው፡፡ ይህ አንድነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የዘለቀውም በመከባበርና በመተሳሰብ የጋራ እሴቶች ላይ በመገንባቱ ነው፡፡ ለጥላቻ፣ ለክፋት፣ ለአሻጥርና ለሴራ ሳይንበረከክ አገሩን በጥልቅ ፍቅር ይወድ የነበረው ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ኩራትና ሞገስ የሆነውን ታላቁን የዓደዋ ጦርነት በማሸነፍ ኮሎኒያሊስቶችን አንገት ማስደፋት ችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መመሥረት መነሻ በመሆን ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን የጋራ ቤት እንድትሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ ሰላሳኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ በሚከናወንበት በዚህ ወቅት፣ ለአፍሪካውያን ወገኖቻችንና ለሌሎች እንግዶች የተለመደውን ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ እያደረግን ውስጣችንንም መፈተሽ አለብን፡፡

ኢትዮጵያ አገራችንን ለዚህ ክብር ያበቋትን የቀድሞ ጀግኖችን እየዘከርን አፍሪካውያን ወገኖቻችንን ስናስተናግድ፣ ለዓመታት ውስጣችን የመሸጉትን ለአገር ጠንቅ የሆኑ ችግሮችን መመልከት ይገባናል፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው የአገሪቱ ፖለቲካ ዛሬም በአሳዳጅና በተሳዳጆች መካከል የሚከናወን አስከፊ ውድቀት መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች ክብር የነፈገ የጽንፈኞች መራኮቻ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ያንገበግባል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ዴሞክራሲንና ሰብዓዊ መብቶችን በግርድፍ የሚያነበንቡ፣ ነገር ግን ለተግባራዊነታቸው ምንም ግድ የማይሰጣቸው ስመ ፖለቲከኞች መብዛት አገሪቱን ቅርቃር ውስጥ ከቷታል፡፡ ሥልጣን የያዘው ኃይል  ተፎካካሪዎች እንዳይኖሩበት ሲል ብቻ ሰላማዊውን የፖለቲካ ምኅዳር ባዶ አድርጎታል፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ የማይመጥን ምርጫ እየተካሄደ የፓርላማ መቀመጫዎችን ጠቅልሎ መያዝ አንዱ በሽታ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ የዘለቀው ቀውስ አሁንም ባለበት እንዲቀጥልም ምክንያት ሆኗል፡፡ ተቃዋሚን ማየትም ሆነ ድምፁን ለመስማት አለመፈለግ ከጽንፈኝነት በላይ ምን ዓይነት ስያሜ ይሰጠዋል? በሰብዓዊ መብት ጥሰት አገሪቱ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ገብታ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መሳለቂያ የሆነችው፣ ከእኔ በላይ ላሳር የሚል ጽንፈኝነትና ጨለምተኝነት በፈጠረው ችግር ሳቢያ ነው፡፡ አገርን ለቀውስ ሕዝብን ለትርምስ ዳርጓል፡፡ በአፍሪካውያን ወገኖቻችን ፊት በኩራት እንዳንቆም እያደረገን ነው፡፡

እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ በርካታ የአፍሪካ አገሮች የቀድሞ የአምባገነንነት ጎዳናን እየተው በፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ገጽታቸውን እየቀየሩ ነው፡፡ ለግጭትና ለትርምስ በር የሚከፍቱ ኢዴሞክራሲያዊ ድርጊቶችን እያስቀሩ ለአዲሱ ትውልድ የሚመጥኑ የፖለቲካ ምኅዳሮችን እያስተዋወቁ ነው፡፡ ከውስን የአፍሪካ አገሮች በስተቀር ብዙዎቹ በአንፃራዊነት ሰላማዊና የተረጋጉ እየሆኑ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካውያን የአርነት ትግል ተምሳሌት እንዳልሆንን ዴሞክራሲ እስከ መቼ ብርቅ ይሆንብናል? ጀግኖቹና አስተዋዮቹ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በከፈሉት ወደር የሌለው መስዋዕትነት ምክንያት ብቻ የአፍሪካ ኅብረትና የታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የመሆን ዕድል አግኝተን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ለምን ያቅተናል? የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ልዩነቶችን አክብረን ለጋራ ብሔራዊ ጥቅም በአንድነት መሠለፍ ለምን የሞት ያህል ይከብደናል? ከሥልጣንና ከሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በላይ አገርን የምታህል ትልቅ የጋራ ቤትን ማስከበር ለምን ይቸግረናል? የአንድ ጎራ የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት? ወይስ በብሔራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ይበልጣል? የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ ከመደጋገፍና ያለውን ተካፍሎ በፍቅር ከመኖር የበለጠ የሚያስደስተው እንደሌለ ሁሉ፣ በአገሩ ጉዳይም ከዚህ በተቃራኒ አጀንዳ እንደሌለው ይታወቃል፡፡ ይህንን የጋራ እሴት ማስቀጠል አለመቻል ደግሞ በአፍሪካውያን ወገኖቻችን ፊት ትዝብት ላይ ይጥለናል፡፡

ሥልጣን ላይ ካለው ኃይል በተጨማሪ በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያለው ውጥንቅጥ አገርን የሚመጥን አይደለም፡፡ ግለሰቦች ፓርቲ ሆነው ወይም በቤተሰብና በሽርክና ተደራጅተው በአገር ላይ ሲቀልዱ እንደማየት የሚያበግን ነገር የለም፡፡ ሕዝብ የት እንዳሉ የማያውቃቸው ነገር ግን በቴሌቪዥን በሕዝቡ የሚነግዱ ደካሞች ያሉትን ያህል፣ ምራቃቸውን የዋጡት ጭምር በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ካለፉት ዓመታት ስህተቶች መማር የማይችሉ፣ በስህተት መንገድ ላይ የሚመላለሱ፣ ለዘመኑ አስተሳሰብና ፍላጎት የማይመጥኑ፣ ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው› በሚባለው የደካሞች አስተሳሰብ እየተመሩ ለሥልጣን የሚቋምጡና በቀቢፀ ተስፋ የሚኖሩ ሞልተዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ድጋፍ ያላቸው፣ ነገር ግን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከመዘጋጀት ይልቅ ትርምስ ለመፍጠር እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ብዙ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ትግል አሰልቺ፣ ከፍተኛ የሆነ ትዕግሥትና ፅናት የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ ሁሌም አቋራጭ መንገድ ፍለጋ እየባዘኑ ካሰቡበት መድረስ ያቃታቸው ከንቱዎችም አሉ፡፡ ሲጀመር ለዴሞክራሲ መሠረታዊ መርሆዎች ከማይገዙ ቂመኞች፣ እልኸኞች፣ ግትሮችና ጽንፈኞች ምን ይጠበቃል? ዕድሜ ልካቸውን ባልበሰለ አስተሳሰብ ተጀቡነው የግልና የቡድን ጥቅም ሲያጋብሱ ኖረው ለዘመኑ ትውልድ የሚመጥን ነገር ሲያጡ ብሔርተኝነትን እያቀነቀኑ አገርን ያተራምሳሉ፡፡ ወይም ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት ሐሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረኩ ቀውስ ይፈጥራሉ፡፡ የሚጠሉትን ሥርዓት በአምባገነንነት እየወነጀሉ እነሱ ግን ተቃራኒ ሐሳቦችን መስማት አይፈልጉም፡፡ ይልቁንም የገዛ ወገናቸውን ‹‹ባንዳ›› እያሉ በመወንጀል ያሸማቅቃሉ፡፡ በአፍሪካውያን ወገኖቻችን ፊት የሚያሳፍር ድርጊታቸውን ይዘው መቀጠላቸው ያሳፍራል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንቅልፍ አጥተው አገሪቷንና ሕዝቧን ቀውስ ውስጥ እየከተቱ ያሉ ጽንፈኞች ደግሞ ብሶባቸዋል፡፡ ከብሔርተኝነት ውጪ ምንም የማይታያቸው እነዚህ ጽንፈኞች፣ የእነሱን ሠልፍ ያልተቀላቀለን ባልታረሙ ቃላት ከመሳደብ አልፈው ወጣቱን ትውልድ እየበከሉት ነው፡፡ ግጭት እየቀሰቀሱ እየማገዱት ነው፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር በትውልዶች መስዋዕትነት እዚህ መድረሷን ወደ ጎን እያሉ፣ እንደ ጎራ አሠላለፋቸው ባለታሪኮችን ሲክቡና ሲያንቋሽሹ በስፋት ይታያሉ፡፡ ለአገራቸው በጀግንነት የተሰው ኢትዮጵያውያንን ማክበርና ታሪካቸውን በደግ ማውሳት ሲገባ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽንፈኞች የሚታየው ግን ብሔርን ማዕከል ያደረገ የክፋት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው ምድር ውስጥ በበቀሉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ታፍራና ተከብራ መኖሯ እየተዘነጋ፣ በጽንፈኛ ብሔርተኞች ታሪክ እየተዛባ ጀግኖች ይዘለፋሉ፣ ሕዝብ ይሰደባል፣ ትውልድ ይበከላል፡፡ ‹‹አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል›› እንደሚባለው፣ ለአቅመ ፖለቲካም ሆነ  ለታሪክ ትንተና የማይበቁ ጥሬዎች አገርን እያዋረዱ ነው፡፡ በመርዛማ ፕሮፓጋንዳቸው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን እየናዱ ነው፡፡ ለሚዛናዊት ግድ ስለሌላቸው ተቃራኒ የሚሉትን ሁሉ መደፍጠጥ ይፈልጋሉ፡፡ እነሱ ዘንድ ዴሞክራሲ ከወሬ በዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ በአፍሪካውያን ወገኖቻችን ፊት በኩራት እንዳንቆም እያደረጉን ነው፡፡ ጽንፈኝነት ይህንን ያህል ያሳምማል፡፡

ኢትዮጵያ የ100 ሚሊዮን ልጆቿ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያን ወገኖቻችን የጋራ ቤት ናት፡፡ አፍሪካውያን ወገኖቻችን ለነፃነታቸው ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ኅብረ ቀለማት ከመጠቀማቸው በተጨማሪ፣ የጋራ ቤታቸው እንድትሆን የመረጧት የነፃነታቸው ተምሳሌትና አብሪ ኮከብ መሆኗን በማመናቸው ነው፡፡ እኛ ግን ይህችን ታሪካዊትና ኅብረ ብሔራዊት አገር ስናውቅ በድፍረት ወይም ሳናውቅ በስህተት ወዳልሆነ አቅጣጫ እየመራናት ነው፡፡ ከጽንፈኛ አስተሳሰብ ውስጥ በፍጥነት መውጣት ያስፈልገናል፡፡ ኢትዮጵያ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የደቡብ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋምቤላ፣ የሶማሌ፣ የሐረሪ፣ ወዘተ. ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያን ጭምር መሆኗን ማመን ይገባናል፡፡ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑት አፍሪካውያን እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ የጋራ ቤታቸው መሆኗን ነው የሚያውቁት፡፡ እኛ እርስ በርስ እየተራኮትን ግን እንዴት ለያምኑን ይችላሉ? እኛ እርስ በርስ ሳንግባባ ሌላውን እንዴት ማስተናገድ እንችላለን? ጽንፈኝነት ውስጣችን እየተፍለቀለቀ እንዴትስ የጋራ አገር ይኖረናል? የዴሞክራሲን መሠረታዊ መርሆዎች በቅጡ ሳንረዳ እንዴት ሆኖ ነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምንገነባው? ጽንፈኝነት እኮ ፀረ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብትን ማክበር አይችልም፡፡ የሐሳብ ነፃነትን አይቀበልም፡፡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲኖር አይፈቅድም፡፡ ወዳጅነቱ ከአምባገነንነት ጋር ብቻ ነው፡፡ የጽንፈኝነት ውጤቱ ውድመት ነው፣ ጥፋት ነው፡፡ በቂም በቀልና በጥላቻ ተነሳስቶ አገር ማተራመስ፣ ሕዝብን ለዕልቂት መዳረግ የሚመጣው ከጽንፈኝነት ብቻ ነው፡፡ ጽንፈኝነት ለማንም አይበጅም!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...

በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ አጠቃላይ ገበያው እንዳይታመም ትኩረት ይደረግ!

መንግሥት ነዳጅን ከመደጎም ቀስ በቀስ እየወጣ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚያደርገውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ...