Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቆቦ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ሕይወት ጠፋ

በቆቦ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ሕይወት ጠፋ

ቀን:

ረቡዕ ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኃላ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በቆቦ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የሰው ሕይወት መጥፋቱ ታወቀ፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበባው ሲሳይ ዓርብ ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በቆቦ ከተማ በወጣቶችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ የሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ቢነገርም፣ የሟቾቹ ቁጥር ገና በመጣራት ላይ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ተከስቶ በነበረው ግጭትም በበርካቶች ላይ አካላዊ ጉዳት ከመድረሱ በተጨማሪ፣ በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ የወደመው ንብረት ምን ያህል እንደሆነ ገና በመጣራት ላይ ስለሆነ አይታወቅም ብለዋል፡፡

የግጭቱ መንስዔም ሆነ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነና እስካሁን የተጣራ መረጃ እንደሌለ ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ይህን ቢሉም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለክልሉ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ በቆቦና በወልዲያ ከተሞች ለተከሰተው ግጭት ዋነኛው ምክንያት የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አመራሮች የኅብረተሰቡን ችግር ካለመፍታት የመነጨ ነው፡፡ አቶ ገዱ ችግሩን የክልል አመራሮች እንደፈጠሩት ጠቁመው፣ ጥያቄው መቅረብ የነበረበት በሰላማዊ መንገድ ነበር ብለዋል፡፡

ግጭቱ የተቀሰቀሰው በከተማዋ ወጣቶችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ አበባው በቆቦ ከተማ ግጭቱ የከፋ ጉዳት እንዳደረሰ፣ መንገዶችን በመዝጋት እንቅስቃሴን ለመገደብ ጥረት ሲደረግ እንደነበርና በከተማዋ ሕዝብና በፀጥታ ኃይሎች አማካይነት መንገዶች ሊከፈቱ እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡

መንገዶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተው የፀጥታ አካላት በሔሊኮፕተር ነው መግባት የቻሉት ይባላልና ይህ መረጃ ምን ያህል ትክክለኛ ነው? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አበባው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የመጣ አንድም ሔሊኮፕተር የለም፤›› ብለዋል፡፡

ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ወቅትም ተኩስ ከእኩለ ቀን እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ድረስ እንደነበር አቶ አበባው አስረድተዋል፡፡ ለግጭቱ መቀስቀስ ዋና ምክንያት የነበረው ቅዳሜ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልዲያ ከተማ ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት እንደሆነ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በወልዲያ በተከሰተው ግጭት የተናደዱ ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ፊት ለፊት እስከመፋለም ደርሰው እንደነበርም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ቅዳሜ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልዲያ ከተማ ታቦት አጅበው ሲሄዱ በነበሩ ወጣቶችና በፀጥታ ኃይሉ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት የሰባት ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ በግጭቱ የሰው ሕይወት ከመጥፋቱም በላይ፣ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ነበር፡፡

በወልዲያና በቆቦ ከተሞች ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ዓርብ ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ድረስ መረጋጋት ቢታይም፣ ዜጎች ተረጋግተው ሥራቸውን እያከናወኑ እንዳልሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በወልዲያና በቆቦ ከተሞች የተከሰተውን ግጭት ለማብረድ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቦታው ድረስ ሄደው ከሕዝቡና ከአካባቢው አመራሮች ጋር እየተነጋገሩ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...