‹‹የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ ላይ ዕገዳ እንጂ የመዝጋት ውሳኔ አላስተላለፍኩም››
የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን
‹‹በሕግ የተሰጠ ይዞታን ከሕግ አግባብ ውጪ መንጠቅ አይቻልም››
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር
የኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን የሚገኘውን የቀንጢቻ ታንታለም ማዕድን ማምረቻ በመዝጋት ለወጣቶች የማስተላለፍ ጉዳይ በሐሳብ ደረጃ የተነሳ እንጂ የፌዴራል መንግሥት የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ ፊዩል ኮርፖሬሽንን ከይዞታው ለማፈናቀል አለመሆኑን የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።
የአካባቢው ወጣቶች በተፈጥሮ ሀብቱ ላይ የተጠቃሚነት ጥያቄ እንደሚያነሱ የተናገሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ዋድራ፣ በዞኑ የታንታለም ማዕድንን እያመረተ የሚገኘው የፌዴራል መንግሥት ኮርፖሬሽን የወጣቶቹን የተጠቃሚነት ጥያቄ የመመለስ ፍላጎትና ዝግጁነት እስካለው ድረስ የሚፈጠር ችግር እንደማይኖር አስታውቀዋል።
‹‹የወጣቶች የተጠቃሚነት ጥያቄ ከዓመትና ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበረው አይደለም፤›› ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ኮርፖሬሽኑ ከዞኑ አስተዳደርና ከወጣቶቹ ጋር በመወያየት የተጠቃሚነት ጥያቄያቸውን መመለስ ከቻለ ችግር አይፈጠርም ብለዋል። ‹‹ማዕድኑን በጥሬው ከመሸጥ እሴት ለመጨመር በመንግሥት የተያዘው ዕቅድ ለዞኑም ሆነ ለወጣቶቹ ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው፤›› ብለዋል።
በመሆኑም የታንታለም ማዕድን ይዞታውን ለወጣቶች ለማከፋፈል የተያዘ ዕቅድ አለመኖሩን፣ ነገር ግን በይዞታው የማምረት ፈቃድ የተሰጠው ኮርፖሬሽን ወጣቶች የሚያነሱትን ጥያቄ ካልመለሰ ዞኑ ለወጣቶች ጥያቄ ይዞታውን በማከፋፈል ከመመለስ ውጪ አማራጭ እንደማይኖረው ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ ምርቱን እንዲያቆም የተደረገው ከአካባቢ ጉዳት ሥጋት ጋር በተያያዘና ውሳኔውም በክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በጊዜያዊነት የተወሰነ መሆኑን ተናግረዋል። በተመሳሳይ የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ኃላፊ ሐሰን የሱፍ (ዶ/ር)፣ የታንታለም ማዕድኑን ለማጣራት ኮርፖሬሽኑ የሚጠቀምበትን ውኃ ያቆረ ግዙፍ ግድብ ሞልቶ በመደርመስ በአካባቢውና በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ሥጋትን በመፍጠሩ ኮርፖሬሽኑ መታገዱን ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ግድቡ ሞልቶ የሰውና የእንስሳት ሕይወት እንዳጠፋ፣ አሁንም የተደቀነውን ሥጋት የማስወገድ የገንዘብ አቅም ኮርፖሬሽኑ እንደሌለው ግልጽ በማድረጉ የማገድ ዕርምጃው መወሰዱን ተናግረዋል። ይህ ዕርምጃ በዞኑ ከተያዘው ከወጣቶች ሥራ ፈጠራ ጉዳይ ጋር የሚያገናኘው ነገር አለመኖሩም ገልጸዋል። ሁለቱም ባለሥልጣናት ከቀናት በፊት ለኦሮሚያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሰጡት መግለጫ የማዕድን ማምረቻውን ስለመዝጋታቸው ተናግረው ነበር።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን በቀጣይ የማዕድን ይዞታውን አጋማሽ ለአካባቢው ወጣቶች እንደሚከፋፈል በዘገባው ላይ ሲናገሩ ተደምጠዋል። የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ ፊዩል ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቡልቲ ወዳጆ በበኩላቸው፣ ማዕድኑን የማምረት ሥራ ከኅዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ እንደቆመ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል። የውኃ ግድቡ ሞልቷል በሚል የኮርፖሬሽኑ የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ በክልሉ ባለሥልጣን መዘጋቱን የተናገሩት ኃላፊው፣ ግድቡ የፈጠረውን ሥጋት ኮርፖሬሽኑ ተገንዝቦ የማሻሻያ ግንባታ ለማከናወን በመንግሥት በጀት እንደተፈቀደለት አስረድተዋል። ግድቡ ሞልቷል የተባለው ትክክል እንዳልሆነና ለአንድ ዓመት የሚያሠራ መሆኑን፣ የውዝግቡ ምንጭ የማዕድን ይዞታውን ለወጣቶች ለማከፋፈል ቀድሞ የተወጠነ ዕቅድ በመኖሩ ነው ብለዋል።
የአካባቢው ወጣቶች ተጠቃሚነት አልተረጋገጠም የሚል የዞኑ አስተዳደር ቅሬታ መኖሩን በመረዳትም፣ የኮርፖሬሽኑን ቦርድ በማስፈቀድ ለሥራ ዕድል መፍጠሪያ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ብር መፈቀዱን ተናግረዋል። በተፈቀደው በጀት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ኮርፖሬሽኑ ያቀረበው አማራጭ ሐሳብም የዞኑ አስተዳደር እንዳልተቀበለው ገልጸዋል። የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሁሉንም ወገኖች በመጥራት ለማግባባት ያደረገው ሙከራ፣ እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ ከዞኑ አስተዳደር ጋር ለመመካከር ለሚያደርገው ጥረት መልስ እንኳን እንደማይሰጥ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ላለፋት 28 ዓመታት ማዕድኑን በማምረት ለውጭ ገበያ ሲቀርብ የነበረ ሲሆን፣ ማዕድኑን እዚሁ በማቀነባበር እሴት መጨመር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን እንደሚያስገኝ የፌዴራል መንግሥት ወስኗል። በውሳኔው መሠረትም ኮርፖሬሽኑን የሚቆጣጠረው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻን በከፊል ለመሸጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቷል። የዚህ ጨረታ ሒደት በሚያዚያ ወር የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ የተፈጠረው ውዝግብ በጨረታው ላይ እክል ሊፈጥር እንደሚችል ኮርፖሬሽኑ ሥጋት አድሮበታል። ጨረታውን ያወጣው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ውዝግቡ በጨረታው ላይ የሚፈጥረው እክል እንደማይኖር ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ የአካባቢውን ማዕድን ለማምረት በሕግ አግባብ ከማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ፈቃድ የተሰጠው እንደሆነና በኦሮሚያ ክልል ፍላጎት ብቻ ይዞታውን መንጠቅ እንደማይቻል ተናግረዋል። የዞኑ ፍላጎት ለፌዴራል መንግሥት ቀርቦ ተቀባይነት ሲያገኝና በሕግ አግባብ የኮርፖሬሽኑ ፈቃድ ከተመለሰ ይዞታውን ሊተው እንደሚችል የተናገሩት አቶ ወንዳፍራሽ፣ ይህ የመንግሥት ተቋም ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በሕግ አግባብ እየሠራ የሚገኝ የግል ተቋምም ቢሆን የተፈቀደ ይዞታው ሊተላለፍ የሚገባው በሕግ አግባብ ብቻ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ቀንጢቻ በተባለ አካባቢ ከሚገኘው የታንታለም ማምረቻው፣ ላለፋት 28 ዓመታት ታንታለም በማምረት ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ ነበር፡፡ የኮርፖሬሽኑ አቅም በአሁኑ ወቅት ክፋኛ ከመዳከሙ ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በዓመት ያስገኝ ነበር። ከጥቂት ወራት በፊት ግን ለሠራተኞቹ እንኳን ደመወዝ መክፈል ተስኖት እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡