Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱት ቻይናዊ ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው ለመንግሥት አቤቱታ አቀረቡ

በወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱት ቻይናዊ ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው ለመንግሥት አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

ሕግን በመጣስ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ባሉት የግብር ዘመናት አሳውቆ መክፈል የነበረበትን 4,013,586 ብር የትርፍ ገቢ ግብርን ባለመክፈሉ ክስ ከተመሠረተበት ሲሲኤስ ኮም ሰርቪስ ሶሉዩሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር ክስ የመሠረተባቸው ቻይናዊ፣ ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው ለመንግሥት አቤቱታ አቀረቡ፡፡

ዋና ቢሮው ቻይና የሚገኘው አንሁይ አንታኢ ቴክኖሎጂ ሊሚትድ ድርጅት እህት ኩባንያ አንሁይ አንቲ ኤፒጂ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዮንግ ዳኢ ክስ የተመሠረተባቸው፣ በኢትዮጵያ ሲሲኤስ ኮም ሰርቪስ ሶሊዩሽን በሚባለው ድርጅት ውስጥ በሚሠሩበት ወቅት ከነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የድርጅቱ ተወካይ ሆነው፣ ድርጅቱ ሕግ ጥሶ ግብር አለመክፈሉን የመከላከል ግዴታ ባለመወጣታቸው መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ሚስተር ዮንግ ዳኢ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባቀረቡት ‹‹የቀረበብኝ ክስ ያላግባብ ስለሆነ ይቋረጥልኝ›› አቤቱታ እንደገለጹት፣ ሲሲኤስ ኮም ሰርቪስ ሶሉዩሽን ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ባለው የሥራ ዘመን ኦዲት ተደርጎ፣ ያልተከፈሉ የግብርና የታክስ ክፍያዎች ነበሩ፡፡ ክፍያዎቹ ቅጣትን ጨምሮ እንዲከናወኑ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ሲሲኤስ የከፈለውን ከፍሎ ቀሪውን እየከፈለ መሆኑን፣ በተጠቀሱት የሥራ ዘመናትና ስለተከናወኑ ሥራዎች ኦዲት ሲደረግ ሐሰተኛ ደረሰኞች ተገኝተዋል ተብሎ ድርጅቱ ሲሲኤስ፣ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሶንግ ቻንጊንግ፣ ከነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በውክልና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሚስተር ዩንግ ዳኢና ድርጅቱን በመምራት ላይ በሚገኙት ሚስተር ዱ ዮ ላይ ክስ መመሥረቱን በአቤቱታ ደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡

ሐሰተኛ ደረሰኞች ናቸው በማለት ለዓቃቤ ሕግ ክስ መመሥረቻ መነሻ የሆኑትና በክሱ ላይ የተጠቀሱት ደረሰኞች የተቆረጡት፣ እሳቸው ሲሲኤስ ድርጅትን በውክልና እንዲመሩ ከተመደቡበት ነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. በፊት መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹የድርጅቱ ውክልና ሳይሰጠኝ ለተሰበሰቡ ደረሰኞችም ሆነ ለተሠራው ሥራ ተጠያቂ ልሆን አይገባኝም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የቀረበብኝ ክስ አግባብ አይደለም›› የሚሉት ሚስተር ዮንግ ዳኢ፣ ሲሲኤስ ድርጀትን ለቀው ዋና ቢሮው ቻይና የሚገኘው አንሁይ አንታኢ ቴክኖሎጂ ሊሚትድ ድርጅት እህት ኩባንያ አንሁይ አንቲ ኤፒጂ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሆነው እየሠሩ ቢሆንም፣ ከአገር እንዳይወጡ ዕግድ ስለተጣለባቸው ከእናት ድርጅቱ ጋር መገናኘትና ቤተሰቦቻቸውንም ማግኘት ባለመቻላቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡

ሲሲኤስ ድርጅትን ከ2003 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩት ሚስተር ሶንግ ቻንጊንግና በአሁኑ ጊዜ ሥራ አስኪያጅ ሆነው እየሠሩ የሚገኙት ሚስተር ዱዮ በክሱ ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም፣ ሚስተር ሶንግ ከአገር መውጣታቸውንና የሚስተር ዱ ዮ ክስ ደግሞ መቋረጡን ገልጸዋል፡፡

ውክልና ከተሰጣቸው የሥራ ዘመን በፊት በተቆረጡ ደረሰኞችና በውክልና እንዲሠሩ በተገለጸላቸው የንግድ ሥራ ውሎች፣ የጨረታ ሰነዶች፣ የይግባኝ ደብዳቤዎች መፈረምና ሰነዶች መቀበል ሥራዎች እንደ ወንጀል ተቆጥረው በተመሠረተባቸው ክስ ከአገር እንዳይወጡ መከልከላቸው ተገቢ ባለመሆኑ፣ ክሱ ተቋርጦላቸው ሥራቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ጠይቀዋል፡፡ ክሱ እንዲቋረጥ ያቀረቡት አቤቱታ የሚታለፍባቸው ከሆነ፣ በዋስትና ያስያዙት 400,000 ብር በቂ ሆኖ ወይም ሌላ ተጨማሪ ማስያዝ ካለባቸውም አስይዘው ወደ አገራቸው መሄድና መመለስ እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው አቤቱታቸውን ማስገባታቸው ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ሚስተር ዩንግ ዳኢ የተመሠረተባቸውን ክስ ተቃውመው ለፍርድ ቤት መቃወሚያ አስገብተዋል፡፡ በክስ መቃወሚያቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(2) መሠረት ማንኛውም የተከሰሰ ሰው በከሳሹ በኩል ክሱ ተዘርዝሮ ሊነገረው እንደሚገባ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 112 ደግሞ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ጉዳይ ለይቶና አውቆ መልስ መስጠት እንሚችል መደንገጉን ጠቁመው፣ ሕጎቹን ያልተከተሉና የተከሳሹን መብት ካለማክበራቸውም በተጨማሪ የተሳሳቱና የሚያደናግሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀረቡባቸው ክሶች አራት ቢሆኑም፣ በገቢ ግብርና በተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ የተደነገጉ አንቀጾችን በመጥቀስ ተመሳሳይ ክስ መቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አንቀጽ 112ን የተከተለ ባለመሆኑ ውድቅ ሊደረግ እንደሚገባም በመግለጽ ተቃውሞአቸውን አቅርበዋል፡፡ ይህ ደግሞ ‹‹ተደራራቢ ወንጀሎች እንደ አንድ ወንጀል ይቆጠራሉ›› የሚለውን ድንጋጌ የጣሰ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ሌላው ተከሳሹ ያቀረቡት መቃወሚያ የቀረበባቸው ክስ በግብር ገቢ አዋጅ ቁጥር 286/94 እንደተሻሻለውና በአዋጅ ቁጥር 693/2003 አንቀጽ 103 በተደነገገው፣ እንዲሁም በአንቀጽ 97 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ወንጀልነቱን ቀሪ በሚያደርግ ሕግ በመሆኑ ስህተት መሆኑን በተቃውሞአቸው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...