የቢራ ፋብሪካዎች በጠርሙስና በድራፍት ቢራ ምርቶቻቸው ላይ የዋጋ ጭማሪ አደረጉ፡፡ ሰኞ ጥር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ቢጂአይ ኢትዮጵያ የተጀመረው የዋጋ ጭማሪ፣ በተመሳሳይ ሌሎቹም የቢራ ፋብሪካዎች የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ምርቶቻቸውን ማከፋፈል ጀምረዋል፡፡
ሁሉም የቢራ ፋብሪካዎች ያደረጉት የዋጋ ጭማሪ በተከታታይ ቀናት ተግባራዊ የሆነ ሲሆን፣ የዋጋ ጭማሪያቸውም ተመሳሳይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሰሞናዊው የዋጋ ጭማሪ መታዘብ እንደተቻለው የአንድ ሳጥን ቢራ በአዲስ አበባ የማከፋፈያ ዋጋ ከ214 ብር ወደ 251 ብር ከፍ ብሏል፡፡ የአንድ በርሜል የድራፍት የማከፋፈያ ዋጋ ከ600 ብር ወደ 700 ብር ከፍ ብሏል፡፡
የሰሞኑ የቢራ ፋብሪካዎች የዋጋ ጭማሪ አንድ ዓይነት ነው፡፡ በተከታታይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪን ተከትሎ የቢራና የድራፍት የችርቻሮ ዋጋ በመጨመር ላይ ነው፡፡ የቢራ ፋብሪካዎች ለዋጋ ጭማሪያቸው ምክንያት ሆኖ እየተጠቀሰ ያለው፣ የብር የምንዛሪ ለውጥና በአንዳንድ ጥሬ ዕቃዎች ላይ የታየው ዋጋ መጨመር ነው፡፡
ከሦስት ወራት በፊት የብር ምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ የቢራ ፋብሪካዎች በማከፋፈያ ዋጋቸው ላይ ጭማሪ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ምክንያታዊ ያልሆነ ነው በማለት ጭማሪው ተግባራዊ እንዳይሆን ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከቢራ ፋብሪካዎቹ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለሰሞኑ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት በዋናነት የተጠቀሰው የገብስ ዋጋ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ገበያ መጨመር ነው፡፡ ሌሎች ለቢራ ማምረቻ የሚሆኑ ግብዓቶችም የዋጋ ጭማሪ እንደታየባቸው፣ የውጭ ምንዛሪ ለውጡ የጥሬ ዕቃ መግዣ ዋጋን ከፍ ማድረጉ ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቢራ ፋብሪካዎች የማምረቻ ዋጋ መጨመሩን የጠቀሱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ገበያ ለቢራ ጠመቃ የሚውለው ገብስ ዋጋ በ25 በመቶ ጨምሯል ይላሉ፡፡
በአገር ውስጥ የቢራ ገብስ ዋጋ በተመሳሳይ መጨመሩን ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም አንዱን ኪሎ ግራም የቢራ ገብስ 18 ብር ሲገዙ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ይህ ዋጋ 21 ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሥራ ያሉት ሰባት የቢራ አምራች ኩባንያዎች በአጠቃላይ ከ12 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር በላይ ቢራ የማምረት አቅም እንዳላቸው ይታመናል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ከ20 በላይ የተለያዩ የቢራ ምርቶች ያሉዋቸው ቢሆንም፣ በዋናነት ግን በ250 ሚሊ ሊትር አሽገው የሚሸጡት ቢራ ሰፊ ገበያ አለው፡፡
ካሁን ቀደም ከ2,100 እስከ 2,150 ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ ኩንታል ብቅል ወደ 2,885 ብር ከፍ ማለቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በቅርቡም የአሰላ ብቅል ፋብሪካ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ለቢራ ፋብሪካዎቹ በደብዳቤ የገለጸ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት እስካሁን ሲሸጠው የነበረውን አንድ ኩንታል ብቅል ወደ 2,400 ብር ከፍ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ ይህ ዋጋ ቫትን ሳያካትት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጠርሙስ ላይ የሚለጠፍ አንድ የወረቀት ኅትመት ከአሥር ሳንቲም ወደ 13 ሳንቲም፣ የቆርኪ ዋጋ በፍሬ ከ17 ሳንቲም ወደ 22 ሳንቲም፣ የማጣበቂያ ዋጋ በኪሎ ግራም ከ135 ብር ወደ 155 ብር፣ የኮስቲክስ ሶዳ ዋጋ በኪሎ ግራም ከ26 ብር ወደ 34 ብር፣ እንዲሁም የነዳጅ ዋጋ በሊትር ከ14 ብር ወደ 15.73 ብር በአሥር ወራት ውስጥ ብቻ ማደጉን ከተለያዩ ምንጮች የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡