Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቤቶች ኤጀንሲ ከሁለት ሺሕ በላይ የኮንዶሚኒየም ንግድ ቤቶች ለመሸጥ ጨረታ ያወጣል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለቀበሌ ቤቶች ካርታ ለመስጠት ዝግጅት ተጀመረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በሰባት ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ 2,331 የኮንዶሚኒየም ንግድ ቤቶችን ለመሸጥ፣ ሰኞ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጨረታ ሊያወጣ ነው፡፡

ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡ ከ175 ሺሕ በላይ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ወለል ላይ የሚገኙ 12,500 ቤቶች በ13 ዙር ጨረታዎች ለነጋዴዎች መተላለፋቸው ይታወሳል፡፡

ኤጀንሲው በ14ኛው ጨረታ በተለይ በቦሌ አራብሳ፣ በቦሌ አያት 3፣ 4፣ 5 እና በቦሌ ቡልቡላ በአጠቃላይ 1,543 ንግድ ቤቶችን አቅርቧል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ኮዬ ፈጬ፣ ገላን ሦስት፣ ቱሉ ዲምቱና ገነት መናፈሻ በድምሩ 464 ቤቶች አቅርቧል፡፡ እነዚህን ጨምሮ በሰባቱ ክፍላተ ከተሞች ያወጣቸውን የኮንዶሚኒየም ንግድ ቤቶች ለጨረታ ያቀረበ ሲሆን፣ አንድ ተጫራች ከሦስት ቤቶች በላይ መወዳደር አይችልም ተብሏል፡፡

ዓርብ ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅና የቤት ርክክብና ማስተላለፍ ዋና ሥራ ሒደት መሪ ወ/ሮ አፀደ ዓባይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ጨረታው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በይፋ ከተከፈተ በኋላ አሸናፊዎችን የመለየት ተግባር ከፍተኛውን የሥራ ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ፣ ሥራውም ግልጽና ፍትሐዊ በሆነ አሠራር ኤጀንሲው ባዋቀረው የጨረታ ኮሚቴ ይከናወናል፡፡

የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ከዚህ ጎን ለጎን የቀበሌ ቤቶችን በመቁጠር ያሉበትን ሁኔታና የቦታቸውን ስፋት የሚገልጹ መረጃዎችን በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡

የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ተሰማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስካሁን በአምስት ክፍላተ ከተሞች በተደረገ ቆጠራ የ85 ሺሕ ቤቶች መረጃ ተሰብስቧል፡፡ በአጠቃላይ ከማስፋፊያ ክፍላተ ከተሞች ውጪ በተለይ በመሀል ከተማ በሚገኙ ስድስት ክፍላተ ከተሞች 150 ሺሕ የቀበሌ ቤቶች አሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ነገር ግን በመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶቹ በርካታ የቀበሌ ቤቶች በመፍረሳቸው አሁን የቀሩት በውል እንዳልተለዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የቤቶቹ መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጋር በጋራ የእያንዳንዱ የቀበሌ ቤት ካርታ ይዘጋጅለታል፡፡ ካርታውን የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ እንደሚረከበው አቶ ግርማ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

‹‹እንደ አዲስ የቀበሌ ቤቶች መረጃ ተሰብስቦ አዲስ ካርታ የሚዘጋጅላቸው የጠራ መረጃ ለመያዝ ነው፤›› ሲሉ አቶ ግርማ ገልጸው፣ ‹‹በተለይ በመልሶ ማልማት ሥራዎች የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን የሚሰበሰበው መረጃ ይፈታዋል፤›› በማለት የኤጀንሲው ሥራ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች