Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ባለፈው ሳምንት በሆቴል አዳራሽ የተዘጋጀ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚታደም አንድ ዘመዴን አድርሼው እየወረደ ሳለ፣ አንድ ረዥም ቀይ ሰው በእጁ ወደ እኔ አቅጣጫ እያመላከተ ይጣራል፡፡ እኔ ደግሞ ዘመዴን ከመኪናው አስወርጄው እየተሰናበትኩት ነው፡፡ ይኼ የማላውቀው ሰው ማን ነው? ወይስ ሌላ ሰው ነው የሚጣራው? ገልመጥ ገልመጥ ብል ከእኔ በቀር ማንም የለም፡፡ ሰውዬው በረዥም ቅልጥሙ እየተሳበ መጥቶ መኪናዬ አጠገብ ቆሞ መሳቅ ይጀምራል፡፡ ይኼ ደግሞ ማን ነው? ግራ እንደተጋባሁ ገብቶት ኖሮ በጎርናና ድምፁ፣ ‹‹ዓምደ ወርቅ ረሳኸኝ እንዴ?›› ሲል በዕውኔ ሳይሆን በህልም ውስጥ ያለሁ መሰለኝ፡፡

  የዛሬ 40 ዓመት ከቀድሞው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በከፍተኛ ውጤት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አልፈን፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባን የድሮ ጓደኞቼ መካከል አንዱ ነው፡፡ ድሮም በጎርናና ድምፁና በሚያስተጋባው ሳቁ የምናውቀው ጓደኛችን አሁንም በአስገምጋሚ ድምፁ እያወራና እየሳቀ አጠገቤ ቆሟል፡፡ ድሮ በጣም ቀጭን የነበረው ሰውነቱ አሁን እንደ አሜሪካ ራግቢ ተጫዋቾች የፈረጠመ በመሆኑ ነው ያላወቅኩት፡፡ ከሁሉም በላይ የሚገርመኝ ያ የድሮው ‹‹ያሬድ ቀጭኑ›› አሁን ሰውነቱ በሚያስገርም ሁኔታ ቢፈረጥምም ድምፁ ግን ያው ነው፡፡

  ከያሬድ ጋር ለረዥም ጊዜ ተቃቅፈን በናፍቆትና በመገረም የታጀበ ጥልቅ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ የስልክ ቁጥር ተሰጣጥተን ተለያየን፡፡ እሱ ወደ ሠርጉ እኔ ደግሞ ወደ ጉዳዬ፡፡ የጥንት የጠዋቱ ወዳጄ የሠርጉን ሥነ ሥርዓት ከጨራረሰ በኋላ በነጋታው ደወለልኝ፡፡ በቀጠሮአችን መሠረት ተገናኝተን ወደ ቤቴ ይዤው ሄድኩ፡፡ ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር ካስተዋወቅኩት በኋላ የቀረበልንን ቀማምሰን ቡና ጠጣን፡፡ ከዚያም ወይናችንን ይዘን ወሬ ጀመርን፡፡ እኔና ያሬድ መጨረሻ የተያየነው በ1970 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ ያኔ ሁላችንም በኢሕአፓ ምክንያት ከያለንበት በአብዮት ጠባቂዎች በየከፍተኛችን ተወስደን በታሰርንበት ጊዜ ማለት ነው፡፡

  እኔ ከፍተኛ 12 እስር ቤት ከበርካታ ወጣቶች ጋር ታስሬ ነበር፡፡ በኋላም በአንደኛ ፖሊስ ጣቢያና በማዕከላዊ ምርመራ፣ በኋላም ከርቸሌ ለአምስት ዓመታት ከታሰርኩ በኋላ ነበር የተፈታሁት፡፡ በወቅቱ ጓደኛሞች ከነበርነው መካከል አራቱ በቀይ ሽብር ተገድለዋል፡፡ በወሬ የሰማነው ነገር ቢኖር እነ ያሬድ ወይ አሲምባ ገብተዋል ወይም በሱዳን በኩል ተሰደዋል የሚል ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የያሬድ ብቸኛ እህቱ የነበረችውን ታናሹን ብጠይቃት ምንም እንደማታውቅ ትነግረኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን እሷ አሜሪካ መግባቷን ሰምቻለሁ፡፡ አሁን ከበርካታ ዓመታት በኋላ ይህንን የወጣትነት ጓደኞዬን አገኘሁት፡፡ ብዙ ነገር አወራን፡፡

  ያሬድ በወቅቱ ሊይዙት የመጡትን የደርግ አብዮት ጠባቂዎች በማምለጥ፣ ተደብቆ የቆየው መቂ ገጠር ውስጥ ዘመድ ቤት ነበር፡፡ ከዚያም በሞያሌ አድርጎ ከሌሎች ወጣቶች ጋር ኬንያ ገባ፡፡ ኬንያ በስደት ለአንድ ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አማካይነት አሜሪካ ገባ፡፡ አሜሪካ ሲገባ የሚያውቀው ሰው ስላልነበረ ለብዙ ጊዜ የኖረው ከሜክሲኮና ከሌሎች የላቲን አሜሪካ ዜጎች ጋር ነበር፡፡ እሱ ይኖርበት በነበረው ቴክሳስ ግዛት ብዙ ኢትዮጵያዊያን ስላልነበሩ ለመላመድ ብዙ ጊዜ ፈጅቶበታል፡፡ በኋላ ግን እንደ ምንም ብሎ በአንድ ኢትዮጵያዊ ረዳትነት ሎስ አንጀለስ ገብቶ መኖር ጀመረ፡፡ እዚያ ብዙ ኢትዮጵያዊያን በማግኘቱ ኑሮውም በመጠኑ የተረጋጋ ሆነ፡፡ ከሥራ በኋላ ለመማር ቢያስብ ግን አልተሳካለትም፡፡

  ከአንዲት ኢትዮጵያዊት ጋር ፍቅር ይዞት ኖሮ ትዳር በአቋራጭ መጣ፡፡ ልጆች ተወለዱ፡፡ በወጣትነቱ አገሩን ከባላባት አገዛዝ ለማላቀቅ ከፍተኛ ምኞት የነበረውና አብዮቱ ሲፈነዳ ዓላማውን ለማሳካት የታገለው ወጣቱ ያሬድ የደርግ ጠመንጃ ከአገር አባረረው፡፡ አሜሪካ ገብቶ በቅጡ ሳይመቻች ትዳር ውስጥ ገባ፡፡ ወጣትነቱን ሳያጣጥም የልጆች አሳዳጊ ሆነ፡፡ በቀን እስከ 16 ሰዓታት እየሠራ ሦስት ልጆቹን አሳድጎ ለወግ ለማዕረግ አበቃ፡፡ ለአገሩ ያሰበውን ለልጆቹ አደረገው፡፡ ሌላው ቀርቶ ደርግ ከተወገደ በኋላ አገሩን ለማየት ሲናፍቅ የቆየው ያሬድ ዛሬ ነገ ሲል ሳይሳካለት ቆየ፡፡ አሁን ግን እሱና ባለቤቱ ልጆቻቸውን አስተምረው፣ ከዚያም ኩለው ድረው ከጨረሱ በኋላ ዕፎይ ያሉ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን የአሜሪካ ኑሮ በዚህ ዘመን ዕፎይ የሚባልበት ባለመሆኑ በአገራቸው ሥራ ለመጀመር ፈልገዋል፡፡

  ድምፀ ጎርናናው ያሬድ በዚያ የተለመደ የሚያስተጋባ ሳቁ ይኼንን ሁሉ ከነገረኝ በኋላ በፅናቱ ተገረምኩ፡፡ ለምን ቢባል? እሱ እንደነገረኝ አሜሪካ ውስጥ አንድም ቀን መጠጥ ቤት ገብቶ ቢራ ጠጥቶ አያውቅም፣ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር፡፡ የምሽት ክለብና ሌሎች ሱስ የሚያሲዙ ነገሮች ሳያታልሉት ሙሉ ጊዜውን የሰጠው ልጆቹ እዚህ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ያቋረጠውን ትምህርት በስኬት እንዲያጠናቅቁ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አገራቸው እንዲያልፍላት ሲሉ እንደ ቅጠል የረገፉት እነዚያ የዚያ ዘመን ልበ ብርቱ ወጣቶችን ሲያስብ፣ የራሱን በሕይወት መኖር ይሳቀቅበት እንደበር ሲነግረኝ ገረመኝ፡፡ ባህታዊ የሆነ ያህል ይሰማው ነበር፡፡

  አሁን ዕቅዱ ከባለቤቱ ጋር ጠቅልሎ መጥቶ በአገሩ መሥራት ነው፡፡ ለዚህም ዝግጅት አድርጓል፡፡ ሌላው ያስገረመኝ ደግሞ ያኔ ያቋረጠውን ትምህርት በአስቸኳይ ጀምሮ በቀረው ዕድሜ ቢያንስ የማስተርስ ዲግሪ ለመያዝ አቅዷል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ባለቤቱም ጭምር ለትምህርት መዘጋጀቷን ነገረኝ፡፡ ያለፈው አሰቃቂ የመበላላት አባዜ ቆሞ በነፃነት የሚኖርበት ዘመን በኢትዮጵያ እንዲኖር የሚመኘው ያሬድ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ደግ ሕዝብና ከአኩሪው ታሪካችን በመማር ለሰው ልጆች ክብር እንስጥ ይላል፡፡ ‹‹እኛ እርስ በርስ ተበላልተን ስንጨራረስ ሌሎች ጥለውን ነጎዱ፡፡ አሁንም ከዚያ ዓይነቱ መጥፎ መንፈስ ያልተላቀቁ ሰዎች አሉ፡፡ በመመካከርና በመወያየት ክፋትን አስወግዶ አገርን ማሳደግና ለዘመናት በድህነት ይማቅቅ የነበረን ይህንን ኩሩ ሕዝብ በደስታ ለማኖር መረባረብ ይበጃል፤›› በማለት ምክሩን አካፍሎኛል፡፡ እኔ ደግሞ እላለሁ ይህንን ክፉ ጊዜ በትዕግሥትና በጨዋነት አሳልፈን አገራችንን ከገባችበት ማጥ ውስጥ እናውጣት፡፡ ከሰላም በላይ ምንም ነገር የለም፡፡

  (ዓምደ ወርቅ ባህሩ፣ ከገርጂ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img