Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክበኪነ ጥበብ ሐሳብን የመግለጽ መብት ይዘቱና ገደቡ

  በኪነ ጥበብ ሐሳብን የመግለጽ መብት ይዘቱና ገደቡ

  ቀን:

  በውብሸት ሙላት

  ባለፈው ሳምንት አርቲስቲ ቴዲ አፍሮ (ቴዎድሮስ ካሳሁን) በባህር ዳር የሙዚቃ ዝግጅት ማቅረቡ የሚታወቅ ነው፡፡ በባህር ዳር ማቅረቡም የመወያያ አጀንዳ እንደነበርም ግልጽ ነው፡፡ አጀንዳ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ላይ ተመሳሳይ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን አንድ ነጠላ አልበሙን ለማስመረቅ ሲባል የተዘጋጀው ፕሮግራም እንዲሁ አስተዳደራዊ እንደሆነ በተገለጸ ምክንያት ተከልክሎ ሳለ ባህር ዳር ላይ ግን መፈቀዱ ነው፡፡ በእርግጥ በተመሳሳይ ሁኔታ አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳም እንዲሁ ተከልክሏል፡፡ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ውጤቶች የተለያዩ መልዕክቶችን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በሚመለከት በተለይ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ይፈተሻሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥም በኪነ ጥበብ ሐሳብን የመግለጽ እንዲሁም ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ መብቶችን ምንነት፣ ይዘትና ገደብን መዳሰስ ነው፡፡

  የኪነ ጥበብ ስያሜ አደናጋሪነት

  ‘ኪነ ጥበብ’ በማለት በዚህ ጽሑፍ በወጥነት የምንጠቀመው የአማርኛ ጽንሰ ሐሳብ፣ የእንግሊዘኛውን ‹‹አርት›› የሚለውን በመተካት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(2) እና (3) ላይ ‹‹አርት›› የሚለውን ‹‹ሥነ ጥበብ›› ይለዋል፡፡ ይህንኑ ቃል አንቀጽ 91(3) ላይ ደግሞ ‹‹ኪነ ጥበብ›› ብሎታል፡፡ ለአንድ ዓይነት ጽንሰ ሐሳብ የተለያዩ የአማርኛ አገላለጾችን ተጠቅሟል፡፡ ከሁለት አንዱ መምረጥ ግድ ይላል፡፡

  ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሕገ መንግሥቱ በአማርኛው ቅጂ አንቀጽ 55 (19) ላይ ‹‹የፈጠራና የድርሰት መብቶች››፣ በአንቀጽ 55(2)(ሰ) ደግሞ ‹‹የፈጠራና የሥነ ጥበብ መብቶች››፣ በአንቀጽ 77 (5) ውስጥ ‹‹ፈጠራና ኪነ ጥበብ›› የሚሉ ሐረጎችን ይዟል፡፡ ‘ፈጠራ’ የሚለው የእንግሊዝኛውን ‘ፓተንት’ ሲሆን ‹‹ድርሰት፣ ሥነ ጥበብና ኪነ ጥበብ›› በማለት ሦስት የተለያዩ የአማርኛ አገላለጾችን ይጠቀም እንጂ የእንግሊዘኛው ቅጂ ላይ በወጥነት የተገለጸው ‹‹ኮፒ ራይት›› የሚለው ነው፡፡

  ለ‹‹ኮፒ ራይት›› የአማርኛ አቻው ‘የቅጅ መብት’ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የቅጅ መብት መጀመሪያ ላይ ‘ድርሰት’ ተብሏል፤ ትንሽ አለፍ ብሎ ደግሞ  ‘ሥነ ጥበብ’ ይለዋል፡፡ ሃያ ሁለት አንቀጾችን ካለፈ በኋላ ደግሞ ‘ኪነ ጥበብ’ ብሎታል፡፡ እንግዲህ ሦስትም አንቀጾች ላይ ሦስት የተለያዩ ለዚያው የተሳሳተ አገላለጾችን ተጠቅሟል፡፡ ዞሮ ዞሮ ‹‹አርት›› ለማለት አለመሆኑን ግን ይረዷል፡፡

  እንደሚታወቀው የሕገ መንግሥቱ የአማርኛውና የእንግሊዘኛው ቅጂ የሚለያዩ ከሆነ ተፈጻሚ የሚሆነው የአማርኛው እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥታዊ ደንብ በመጠቀም የምንቀጥል ከሆነ በአማርኛው ላይ የተቀመጠው የእነዚህ አንቀጾች ትርጉማቸው የተዛባ፣ ፋይዳቸውም ያነሰ ይሆናል፡፡ ትክክለኛው አገላለጽ የእንግሊዘኛው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እኛም እንደ ሕገ መንግሥቱ የተለያዩ አጠራሮችን ከመጠቀምና ወጥነት በጎደለው መንገድ መቀጠል ስለሌለብን አንዱን እንመርጣለን፡፡ ሕገ መንግሥቱም ወደፊት ይታረማል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

  እንግዲህ፣ ‹‹አርት›› የሚለውን አንዴ ሥነ ጥበብ ሌላ ጊዜ ኪነ ጥበብ ተብሎ መገለጹን ከላይ ተመለክተናል፡፡ በእዚህ ጽሑፍ ኪነ ጥበብ የሚለው ተመርጧል፡፡ የመጀመርያው ምክንያት ሥነ ጥበብ የኪነ ጥበብ ዓይነት ነው፡፡ በጥቅሉ ከሥዕልና ቅብ ጋር የሚያያዘውን የጥበብ ዘርፍ መጠሪያ እንጂ ሌሎቹን አይወክልም፡፡ በተለይ በቅጅና ተዛማጅ መብት አዋጁ ላይ በግልጽና ወጥ በሆነ መልኩ ‘አርት’ የሚለውን ኪነ ጥበብ በማለት ይጠቀማል፡፡ የተለያዩ መዝገበ ቃላትም ከዚሁ ጋር ተስማሚ ናቸው፡፡

  በኪነ ጥበብ ሐሳብን የመግለጽ መብት

  ኪነ ጥበብ የሰው ልጅ፣ በግሉም ይሁን በቡድን ሰብዓዊነቱን ለማጎልመስና ለመግለጽ ይጠቀምበታል፡፡ ንጽረተ ዓለሙን ይስልበታል፡፡ ነባራዊውን ሁኔታ እንዴት እንደተረዳው በመሰለው መንገድ ትርጓሜ ይሰጥበታል፡፡ በየትም የዓለም ክፍል የሚገኝ ማኅበረሰብ ኪነ ጥበባዊ ፈጠራንና ገለጻን ይጠቀማል፡፡

  ከያኒውም ሕዝብን የማዝናናት ሚና ቢኖረውም፣ በዚህ የታጠረና ተቀንብቦ የቀረ ባለመሆኑ ፈጠራውን  ማኅበራዊ ውይይቶችንና ክርክሮችን ያስኬድበታል፡፡ መንግሥት ለሚከተለው ፖለቲካዊ ተዋስኦ አጸፌታ ማቅረቢያ ይሆናል፤ እንደውም ሌላ ተገዳዳሪ ሐሳብ ይቀርብበታል፡፡ መንግሥት ብሔርን መሠረት ያደረገ የአገር አስተዳደር ሲከተል፣ ትኩረቱን ብዝኃነት ላይ ሲያደርግ ከያኒው በሙዚቃው፣ በፊልሙ፣ በቴአትሩ አንድነትን ሊያቀነቅን ይችላል፡፡ መንግሥት የቀድሞ ነገሥታትን ሲወቅስና ሲኮንን ከያኒው ሊያወድስና ሊያሞግስ ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ኪነ ጥበብ  አገዛዙን የመተቸት ሚና ኖረው፤ ተፃራሪ ሐሳብም ቀረበበት ማለት ነው፡፡ የኪነ ጥበብ መስፋፋት ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብን ለመገንባትም ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ ከኅብረተሰቡ መሻሻልና ማደግ ጋር አብሮ የሚሄድ ባህል እንዲኖርም ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የባህል አካልም፣ የባህል መኮትኮቻና ማሻሻያም ሊሆን ይችላል፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)፣ ሁሉን አቀፍ  የብዝኃ ባህል መግለጫ፣ ስለ ባህል ምንነት የሚከተለውን ይላል፡፡ ባህል ‹‹የአንድን ኅብረተሰብ ኪነ ጥበባዊ፣ የአኗኗር ዘዬ፣ የጋርዮሻዊ የመኖሪያ መንገዶች፣ ትውፊት፣ እምነትና ዋጋ ያላቸው ሥርዓቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ አዕምሮአዊ፣ ልባዊ (emotional) መገለጫዎችን ጠቅልሎ ይይዛል፤›› በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ኪነ ጥበባዊ ሐሳብን የመግለጽ መብት ራሱን ችሎ ዕውቅናና ጥበቃ ይደረግለት እንጂ ኪነ ጥበብ እንደተቋም እንዲስፋፋ የማድረግ ግዴታን የምናገኘው በጥቅሉ ከባህል ጋር ተቀላቅሎ ነው፡፡

  ባህል ከግልዊ መለያና መገለጫ ይልቅ ከማኅበረሰብ/ቡድን/ብሔረሰብ ጋር የሚኖርን ማንነታዊ ቁርኝት ያመለክታል፡፡ ባህል የአንድን ኅብረተሰብ አባል የሆነ ግለሰብ ቋንቋውን፣ ትውፊቱን፣ እንቆቅልሹን፣ እንካስላንቲያውን፣ ከብት አረባቡን፣ አስተራረሱን፣ አመራረቱን፣ አመጋገቡን፣ አለባበሱን፣ የጋብቻ ሥርዓቱን፣ ስፖርታዊ ጭውውቱን፣ ሃይማኖቱን፣ የአምልኮ ሥርዓቱንና አከባበሩን፣ ዘፈኑንና ጭፈራውንና የመሳሰሉትን የሚያካትት ሲሆን እነዚህን መሠረት በማደረግ ለመኖሩ፣ ለሕይወቱ፣ ለዓለም ያለውን አመለካከቱን፣ ችግሮችን የሚጋፈጥበትንና የሚፈታበትን ስልትም ይጨምራል፡፡

  በመሆኑም ባህል የተገነጠለ፣ ስለአንድ ነገር ብቻ የሚያውጠነጥን አይደለም፤ የሰውን ልጅ ሁለመናውን አቅፎ የሚይዝ እንጂ፡፡ ኪነ ጥበብም በዋናነት ቁርኝቱ ከባህል ጋር ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 91 ስለባህል ፖሊሲ አቅጣጫ ሲያስቀምጥ ኪነ ጥበብን ሥር መቀመጡ ለእዚሁ ነው፡፡

  የጥበቃው አስፈላጊነትና ምክንያቶች

  ኪነ ጥበብ በምክንያታዊነት ሳይገታ ለስሜት፣ ለምናብ፣ ለተብሰልስሎት ይገዛል፡፡ ለመብቱ ጥበቃ ሲደረግም ከዚህ ውጪ ለሆኑት ሐሳቦች ከሚቀርቡት ምክንያቶች በተጨማሪ  ሌሎችም አሉ፡፡ መነሻው የኪነ ጥበብ ልዩ ባሕርይ ያለው መሆኑ ነው፡፡

  በጥቅሉ፣ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት ጥበቃ የሚደረግባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡  የመጀመርው ዕውቀትን ለማስፋትና እውነትን ለማውጣት ሲባል  በሕግ ጥበቃ ተደርጎለታል፡፡ የሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ ‹‹የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ›› የፈጠራ ድርሰት ቢሆኑም የአቡነ ጴጥሮስን አርበኝነታዊ መስዋዕት፣ የአፄ ቴዎድሮስን የመቅደላ ጦርነት በመጠኑም ቢሆን ያሳውቃል፡፡ ስለሆነም በኪነ ጥበብም ዕውቀትና እውነት ስለሚገልጽ ለዚሁ ሲባል ጥበቃ ይደረጋል፡፡

  ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሐሳብን መግለጽ በራሱ የነፃነት፣ የራስን ስብዕና ዕውን የሚደረግበት በራስ ጉዳይ ላይ በግል የመወሰን ሥልጣንን መጎናፀፊያ ስለሆነ ነው፡፡ ከያኒው፣ ዓለምን የተረዳበትን፣ እውነትን የተገነዘበበትን ታሪክን ፖለቲካን የታዘበበትን በኪነ ጥበብ መግለጽ የሰው ባሕርይ ነው፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ‹‹አድዋ›› በማለት ያቀነቀነችው አድዋን በኪነ ጥበብ በእዚያ መንገድ መግለጽ በመፈለጓ ነው፡፡ የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማም ‹‹አድዋ›› የሚለው ፊልምም እንዲሁ  ነው፡፡

  በሦስተኛነት የሚታወቀው መንግሥትን የመቆጣጠር ፋይዳ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ይሁኔ በላይ ‹‹ሰከን በል›› በማለት ሲዘፍን የመንግሥትን የፀጥታ ኃይሎች ሲተች ነው፡፡ የሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››ም የአፄ ኃይለ ሥላሴን ሥርዓት ፊውዳላዊ ነው በማለት ሲተቹ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ አገራዊ አንድነትን መንግሥታዊ ሥርዓትንም ለማናጋት በፕሮፓጋንዳነት ሚና ሊኖረው ይችላል፡፡

  የመጨረሻው ምክንያት ደግሞ ኪነ ጥበብ፣ አንድ ማኅበረሰብ ባለበት የረጋን፣ ከለውጥ የራቀን፣ የታፈነና የተወጠረ ስሜትን እንዲገነፍልና እንዲወጣ ብሎም የረጋው እንዲንቀሳቀስ፣ እንዲለወጥ፣ ስሜት እንዲላላ የማድረግ ውጤት ስላለው ነው፡፡ እነዚህ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን ለመገለጻቸው ጥበቃ ለማድረግ በምክንያትነት የሚወሰዱ ናቸው፡፡

  ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ፣ የኪነ ጥበብን ልዩ ባሕርያት መሠረት ያደረጉ ጥበቃ ለማድረግ የሚያስገድዱ ምክንያቶች አሉ፡፡ ማንም ሰው በዓይነ ኅሊናው፣ በምናቡ የሚስላቸውና የሚፈጥራቸው ሐሳቦች አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት የፈጠራ ሒደቶች ከሰው ልጅ ባሕርይ ጋር የተዋሃዱ ናቸው፡፡ በእዚህ መንገድ ለደረሰበት ሐሳብ ቅርጽ ይሰጠዋል፤ በቃል ይገልጸዋል፤ ቀለም ይቀባዋል፡፡ ግዘፋዊነት እንዲነሳ ያደርገዋል፡፡ የጀርመን የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ. በ1973 በግልጽ ያስቀመጠው ይኼንኑ ነው፡፡ ይዘቱ ኪነ ጥበብም ቢሆን ፍርድ ቤቱ የሕግ ጥበቃ እንደሚስፈልገው በምክንያትነት ያቀረበው ነው፡፡

  ይህ የፈጠራ ሒደት ታዳሚን የሚያስደምም፣ የሚመስጥ፣ የሚያስፈራ፣ የሚያዝናና፣ የሚያስደነግጥ፣ የሚያስደስት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ከሌሎቹ የሐሳብ ዓይነቶችም የሚለይበት ነው፡፡

  በሁለተኛነት የሚቀርበው ደግሞ የሰው ልጅ ምሉዕ የሚሆንበት ስለሆነ ነው፡፡ በአመክንዮ፣ በሳይንስ የማንደርስባቸውን ወይም ያልተደረሰባቸውን ወይም ለሳይንሳና ለአመክንዮ ሕግጋት የማይገዙ ጉዳዮችን የሚገለጽበት በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ጋር በመደመር ሕይወትን የተሟላ ለማድረግ ስለሚረዳ ነው፡፡ የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ኸርላን ስለመጀመሪያ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማብራሪያ ሲሰጡ በተለይ ኪነ ጥበብን በተመለከተ የተናገሩት ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ኪናዊ ቃላት ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነትን የተሸከሙ፣ የሚያስተላልፉትም እንዲሁ ለስሜት በማቅረብ ስሜትን ሰቅዞ የሚይዝ ነው፡፡ ጥሬ ሐቅን ሳይሸከም ማንም በተረዳው መጠን የሚገነዘበው የሚያጣጥመው የሚደሰትበት ወዘተ እንጂ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ያለው ብዙም ኪነ ጥበባዊነት እንደሚጎድለው አስረድተዋል፡፡ ኪነ ጥበብ የራሱ ውበት አለው፡፡ ውበት ደግሞ እንደተመልካቹ ነው እንዲሉ፡፡

  በሦስተኘት የሚወሰደው ደግሞ ምናባዊ ሐሳብን ማፍለቅና መፍጠር በራሱ የነፃነት ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ ለእነዚህ ምክንያቶች ሲባል ለኪነ ጥበባዊ አስተሳሰብና ፈጠራ ብሎም መግለጽ በሕግ ዕውቅና ይሰጣል፤ ጥበቃም ይደረጋል፡፡

  ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራው ከይዘት አንፃር ፖለቲካዊ ካልሆነው ይልቅ የሆነውን ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ትርጓሜም ውሳኔም መስጠት የተለመደ ባህል ሆኗል፡፡ ግብረ ገብነትን የሚፃረሩ፣ የሆነ ሃይማኖትን የሚያንቋሽሹ ከሆነ ገድብ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ የፖለቲካ ይዘት ከሌላቸው ይልቅ ይዘታቸው ፖለቲካዊ ለሆኑ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የተሻለ የሕግ ጥበቃና ከለላ ያስፈልጋቸዋል በሚል ብዙ ውሳኔዎች ላይ ሐተታውን አስፍሯል፡፡ ፖለቲካዊ የሆኑት በዋናነት መንግሥትን የሚመለከቱ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ማኅበረሰቡን ወይም የሆነ የኅብረተሰብ ክፍልን ነው፡፡ ኪነ ጥበባዊ የፖለቲካ ትችትም ከያኒው ፖለቲካዊ ሐሳቡን የገለጠበት መንገድ ከመሆን በቀር ሌላ ነገር የለውም፡፡ 

  የመብቱ ይዘት

  የዚህ መብት ጥበቃና ዕውቅና በአገር ደረጃ ብቻ ሳይወሰን በዓለም አቀፍና በአኅጉር አቀፍ ሕግጋትም ጭምር ነው፡፡

  ሁለቱ የ1966ቹ ዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 19፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ የማኅበራዊና ባሕላዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 15 ላይ የኪነ ጥበባዊ የፈጠራ መብትና ሐሳብን በኪነ ጥበብ የመግለጽ መብቶችን በማያወላዳና በግልጽ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦችና መብቶች ቻርተርም አንቀጽ 9 እና 17 ላይ በተመሳሳይ መልኩ ጥበቃ ተሰጥቶታል፡፡

  ማንም ሰው የመሰለው ሐሳብ፣ አቋም፣ አስተያየት የመያዝ ፍጹማዊ፣ ገደብ የሌለበት መብት አለው፡፡ ይህ መብት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችም ላይ ዕውቅናና ጥበቃ የተሰጠው ነው፡፡ በአገራችንም በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 (1) መሠረት ጥበቃ ተሰጥቶታል፡፡ ቃል በቃል ሲነበብም ‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ ይችላል፤›› በማለት ተደንግጓል፡፡ ማንም ሰው እንዲህ አስብ፣ እንዲህ አታስብ ሊባል እንደማይገባ ሲገልጽ ነው፡፡

  ሐሳብህ፣ አመለካከትህ ስህተት ስለሆነ በሌላ እንዲተካ ወይም እንዲቀይር ሊገደድ እንደማይገባ ዋስትና ይሰጣል ይህ አንቀጽ፡፡ ይህ አንቀጽ  ጥበቃ የሚሰጠው ለኅሊና ነፃነት ነው፡፡ የአንድ የፖለቲካ ድርጅትን፣ የመንግሥትን የሃይማኖት ተቋምን ወዘተ አስተምህሮ ባይቀበል ወይም የተለየ አመለካከት ቢኖረውም ሊከበርለት እንጂ ጣልቃ በመግባት ኅሊናው እንዲህ ዓይነቱን ሐሳብ እንዲተው ለማድረግ የሚያስችል የግዳጅ ተግባር እንዳይፈጸም ይከለክላል፡፡

  የሐሳቡ ዓይነት ደግሞ ኪነ ጥበባዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ኪነ ጥበባዊ ሐሳብ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በቅርጽ፣ በፊልም፣ በተውኔት፣ በግጥም በልብ ወለድ ወዘተ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ይህ አንቀጽ ማንም ሰው የመሰለውን አመለካከት መያዝን እንጂ መግለጽን አይመለከትም፡፡ መያዝ ሲባል የግድ በአንጎል ውስጥ ማስቀመጥ ብቻ አይደለም፡፡ በወረቀት አስፍሮ፣ በድምፅ ቀርጾ፣ ወደ ምስል ቀይሮ በግል ማስቀመጥንም ይጨምራል፡፡

  እንግዲህ ይህ ዓይነቱ ዋስትና ከያኒውን መንግሥትን ብቻ እንዲያወድስ አለበለዚያ እንዲታቀብ ከማድረግ ይገላግላል፡፡ ለአንድ ዓይነት ግብ ብቻ የሚውሉ የኪነ ጥበብ ውጤቶች ብቻ እንዲፈጠሩ እንዲታሰቡ ማድረግ በአንድ በኩል ኪነ ጥበቡን እንዲነጥፍ ማድረግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሐሳብ ብዙኃነት ተቀራኒ በመሆኑ ለዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብም ግንባታም ፀር ነው፡፡ በደርግ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ዘፈኑም ሥዕሉም፣ ቴአትሩም፣ ልቦለዱም ግጥሙም ሁሉም የኪነ ጥበብ ውጤቶች በሙሉ ኅብረተሰባዊ አንዲት ኢትዮጵያን የሚገልጹ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ በማሰብ በኪነ ጥበብ መግለጽ የሚፈቀድ አልነበረም፡፡

  ማንም ሰው ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ነፃነት እንዳለው በሕገ መንግሥቱ ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሦስት ላይ በግልጽ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ተግባራትን የማከናወን፣ ከያኒ መሆን ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብ ኪነ ጥበባዊ በሆነ መንገድ የመግለጽ መብት አለው፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ኪነ ጥበብን የሐሳብ መግለጫ መሣርያነቱም እንዲሁም የፈጠራ ተግባሩንም ራሱን ጥበቃ አድርጎለታል፡፡

  እዚህ ላይ ከቁም ነገር መግባት ያለበት አንድ ነጥብ አለ፡፡ ይኸውም የመሰለውን አመለካከትና ሐሳብ መያዝና ይህንኑ መግለጽ የተለያዩ መሆናቸው ነው፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብ መያዝ ብቻ ሳይሆን የመግለጽ መብቱም ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ የሚገልጽበት መንገድ ደግሞ የተለያየ ሊሆን መቻሉም ግልጽ ነው፡፡

  በጥቅሉ ሲታይ የሐሳቡ ዘውግ ምንም ይሁን ምንም ማንም ሰው ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱን በሚመለከት የሚኖረው መብት ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለሆነም በኪነ ጥበብ ሐሳብን የመግለጽ መብት በሚባልበት ጊዜ የራስን ኪነ ጥበባዊ አመለካከትንና ሐሳብን፣ ያለመንግሥታዊ ማስፈራሪያና ዕቀባ (ሳንሱር) እንዲሁም ያለማኅበረሰባዊ ክልከላ፣ ምናባዊ ፈጠራውን አንጥሮ በማውጣት የማስተላለፍን መብትን ይመለከታል፡፡

  ከያኒውም ይሁን ተደራሲው ኪነ ጥበባዊ ሐሳብን በነፃነት የመሻትና የመሰብሰብ እንዲሁም የመቀበል መብቶች አሏቸው፡፡ በተለይ ከያኒው ደግሞ የፈጠራ ውጤቱንም የማሠራጨት መብትም ጭምር አለው፡፡ በመሆኑም ኪነ ጥበባዊ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሲባል እነዚህ ሦስት ፈርጆችን ይይዛል ማለት ነው፡፡ በሕገ መንገሥቱ በአንቀጽ 29(2) ላይ የተገለጹ ናቸው፡፡

  ኪነ ጥበባዊ ሐሳብን የመሰብሰብ ወይም የመሻት ነፃነት የሚመለከተው መረጃ መሰብሰብን፣ መፈልግን፣ ማግኘተን፣ መከታተልን፣ መታደምን፣ መጎብኘትን የመሳሰሉትን ነው፡፡ ከየትም ቦታ የሚተላለፍን ኪናዊ የሚዲያ ሥርጭቶችን መከታተልንም ያካትታል፡፡

  መቀበሉ ደግሞ በዋናነት ሚዲያ ከመከታተል ጋር ቢያያዝም፣ ከመሻት አልፎ በአካል በመገኘትም የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ማግኘትንም ይጨምራል፡፡ ከያኒያንም ሆኑ ሌሎች ተቋማት ኪነ ጥበባዊ ውጤቶችን የሚያቀርቡ የሚያስተላልፉ ቢኖሩ እንደዚህ ዓይነቱን የመረጃ ምንጭነት ላይ ገደብ መጣል ወይም እንዳይደርስ ማድረግን ይከለክላል፡፡ ዜጎችንም ኪነ ጥበባዊ ሥራውን እንዳያገኙ አለማስፈራራትን (ከፍርሃት ነፃ) መሆንን ይመለከታል፡፡

  ኪነ ጥበባዊም ይሁን ሌላ ሐሳብን የማሠራጨት መብቶችን ማክበርና ማስከበር  ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ማኅበረሰብም ግንባታ መሠረት ነው፡፡ ሐሳብን ማሠራጨትና መቀበል የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም ማለት ነው፡፡ የሚያሠራጭ ነገር ካለ የሚቀበል አለ ማለት ነው፡፡

  ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራ ሐሳብን ከመግልጽ በዘለለ ሀብትና ንብረትም ነው፡፡ ሀብት በመሆኑ ከኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥበቃ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ በተጨማሪም ከያኒነት ደግሞ ሙያም ነው፡፡ ማንም ሰው በፈለገው የሙያ ዘርፍ የመሰማራት መብቱ እንዲሁ በተለያዩ ሕግጋት ዕውቅናና ጥበቃ ተችሮታል፡፡ ስለሆነም ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሀብትን ከሌሎች ሰዎች አላግባባ አንዳይጠቀሙ ሕግ ዋስትና ይሰጣል፡፡ በተለይም ደግሞ ለቅጅ መብት ጥበቃ በማድረግ ማለት ነው፡፡

  ገደቦቹ

  መብቶች ስለሚገደቡባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በርካታ ፈላስፋዎች፣ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች፣ የሕግ ባለሙያዎች የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦችን ይከተላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱና በሰፊው የሚታወቀው የጉዳት መርሕ ነው፡፡ በዚህ መርሕ መሠረት መብት ሊገደብ የሚገባው የሌላን ሰው መብት የሚጎዳ ከሆነ ነው፡፡ የገደቡ ምክንያት ሌሎችን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲባል ነው፡፡ የራስን ሐሳብ በሚያስኬደው መጠንና ጥግ ድረስ ለመግለጽ እንጂ ሌላ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚሰጥ ጥበቃ መሆን እንደሌለበት ይገልጻል፡፡

  ሌላው፣ የጥፋት መርሕ የሚባለው ነው፡፡ ለማኅበረሰቡ ጥፋት ወይም የወንጀል ባሕርይ ካለው ማለትም ንግግሩ የሚመለከተው ሰው መጠን፣ የተነገረበት ወቅት እንዲሁም፣ የተናጋሪውን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ማኅበረሰቡን ማስቀየሙን ወይም ጥፋት መሆኑን ብሎም ከመገድብ በመለስ በሌላ መንገድ ማስቀረት የማይቻል ከሆነ ሊገደብ እንደሚገባው የሚያስረዳ መርሕ ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል ማድረግ ሌሎችን ይታደጋል፡፡

  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በሕትመት ውጤትና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት መሠረት አድርጎ የሚኖር ክልከላ አይደረግም፡፡ መከልከልን የሚፈቅድ ሕግ ማውጣትም አይፈቀድም፡፡ አንድ ዘፈን መንግሥትን ስላወደሰ ወይም ስለተቃወመ በሚል አይገደብም፡፡ የኪነ ጥበብ ሥራው ይዘት ፖለቲካዊም ይሁን ፍቅር አይታገድም፡፡

  ኪነ ጥበባዊ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤትን በመገመትም መከልከል አይቻልም፡፡ በሕግ የሚገደብባቸው ‘የወጣቶችን ደህንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብዓዊ ክብርን  የሚነኩ የአደባባይ መግለጫ ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ’ ብቻ ናቸው፡፡

  ብዙዎች የግለሰብን መብትና ሰብዓዊ ክብርን በኪነ ጥበብ አማካይነት የመንካቱን ጉዳይ አሳማኝ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ የፈጠራ ሥራ በባሕርው ብዙ ትርጉሞች የሚኖሩት እንጂ ጥሬ ሐቅን የማያስቀምጥ በመሆኑ በእዚህ ሰበብ ገደብ ሊኖረው አይገባም ይላሉ፡፡ እንደ ቡድን የወጣቶች አስተዳደግን የሚመለከት፣ እንደ ተቋም ደግሞ ከጦርነት ቅስቀሳን የሚመለከቱን ግን በርካታ አገሮች ይገድባሉ፡፡ 

  የአገሮች ግዴታዎች

  ኪነ ጥበባዊ ሐሳብን የመግለጽ መብትን በሚመለከት የየትኛውም አገር መንግሥት በርካታ ግዴታዎች አሉበት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የኪነ ጥበባዊ ሐሳብን የመግለጽና ፈጠራ መብት ልዮ ራፖርተር፣ ፋሪዳ ሻሒድ፣ በ2013 ለድርጅቱ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ባቀረበችው ሪፖርት ላይ የሚከተሉትን ግዴታዎች አገሮች መወጣት እንዳለባቸው ገልጻለች፡፡ አገሮች ግልጽነት የጎደለቻውን ሕጎች በማስወገድ ለከያኒያንን ጥበቃ የሚያደርጉ ሕግ የማውጣት፣ ሳንሱርን የማስወገድ፣ ለሕዝብ የሚቀርቡ ሥራዎች የሚለዩበትን አሠራር ግልጽ ማድረግ (ለአብነት ሕፃናት የማይመለከቷቸውን መለየት)፣ የኪነ ጥበብ ውጤቶች ለሕዝብ የሚቀርቡባቸውን ቦታዎች ማመቻቸትና ከአድልኦ በፀዳ ሁኔታ ከያኒያን እንዲጠቀሙበት ማድረግ፣ ከቦታ ቦታ ወይም ከአንድ ከአገር ወደ ሌላ እንዳይሄዱ አለመከልከልን፣ መንግሥታዊ ተቋማትን በፍትሐዊነት ለሁሉም ማስጠቀም፣ የከያኒውን የሞራልና የኢኮኖሚ ጥቅም ማስጠበቅ ከብዙው በጥቂቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ግዴታዎች፣ ኢትዮጵያም ጭምር ፈርማ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተገኙ የተቀዱ ናቸው፡፡ መንግሥትም የኪነ ጥበብ ውጤቶችን በሚመለከት በእዚሁ መንፈስ ግዴታውን መወጣት ለኪነ ጥበብ ያለበት ግዴታም ኃላፊነትም ነው፡፡

  አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img