Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዓባይና የካይሮ ዲፕሎማሲ

ዓባይና የካይሮ ዲፕሎማሲ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው                                                   

ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳላኝ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን በግብፅ ካይሮ በመሪ ደረጃ ውይይት አድርጎ ተመልሷል፡፡ ይኼ ምክክር ቀደም ሲል መርሐ ግብር የተያዘለት በናይል ውኃ አጠቃቃምና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በተጨማሪም በአገሮቹ መካከል መተማማንና ትብብርን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገልጸዋል፡፡

ምንም ተባለ ምን ግን የሁለቱ አገሮች ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ዓባይና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡ ባለፉት ጊዜያት የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ ቢቀጥልም፣ እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ መግቢያ አንስቶ ለአሥር ዓመታት ገደማ የተደከመበት የናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምነት ነበር ሲያገናኛቸው የከረመው፡፡ በተናጠልም ባይሆን ከተፋሰሱ አገሮችም ጋር ኢትዮጵያና ግብፅን ሲያከራክር፣ ሲያግባባ በመጨረሻም በሐሳብ ተለያይቶ በስምምነቱ ላይ እስከ መፈረምና አለመፈረም ያደረሳቸውም ይኼው መድረክ እንደነበር ይታወቃል።

በዚሁ መነሻ አገራችን የብዙኃኑን የተፋሰሱ አገሮች ውሳኔ ተከትላና የውስጥ የዝግጁነት አቅሟን ፈትሻ ታላቅ የሆነውን የኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባት ስትጀምርም  ከየትኛዎቹም  የግብፅ መንግሥታት መሪዎች፣ የውኃ ሚኒስትሮች፣ የውጭ ጉዳይ የሥራ ኃላፊዎችና ባሙያዎችም ጋር በርካታ ምክክሮችን ስታደርግ ነው  የቆየችው፡፡ ቢያንስ ባለፉት አምስት ዓመታት ገደማ ለ17 ጊዜ የሦስቱ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ) ኤክስፐርቶችና ፖለቲከኞች የተሳተፉባቸው የድርድር መድረኮችም ተከናውነዋል፡፡ በመሪ ደረጃም በተደራቢ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ተገናኝቶ ከመወያያት ባሻገር፣ የተለያዩ ይፋዊ መርሐ ግብሮች በአዲስ አበባም በካይሮም ተዘጋጅተው ዓይተናል፡፡

እስካሁን እንደታየው ግን ከተለመደው የዲፕሎማሲ ውይይት ባለፈ የፀና የአቋም ለውጥና መቀራራብ ጎልቶ አለመንፀባረቁን ነው፡፡ በተለይ በግብፃውያኑ በኩል ተደጋግሞ የሚነሳው የታሪካዊ የውኃ ሀብት ባለቤትነት መብት ጉዳይ ወደ ቅኝ ግዛት አስተሳሳብ የሚመልስ እንደሆነ ብዙዎች ተችተውታል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የታላቁ  ህዳሴ ግድብ የውኃ ፍሰትና የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ለማጥናትና በጉዳዩ ላይ ለመነጋጋር የግንባታ ሥራው ቆሞ እንወያይ፣ በሁለትዮሽ ደረጃ ብቻ እንነጋጋር፣ ሌላ ሦስተኛ አገር ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅት ያደራድረን የመሳሰሉትን ደረቅ ሐሳቦች ማንሳት የተለመዱ ነጥቦች  ሆነዋል፡፡

ለነገሩ ገና ከተፋሰሱ አገሮች ጋር በተደረገው ለዓመታት የዘለቀው (የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ፎረም) ስምምነትም ላይ  ግብፆች ሲያሻቸው ምንም እንኳን በፊርማቸው ማረጋገጥ ባይፈልጉም፣ “የትብብር ማዕቀፉን እንደግፋለን” ማለታቸውና የሌሎች አገሮች የልማት እንቅስቃሴዎች “የግብፅን የውኃ ደኅንነት እስካልነኩ ድረስ እንደግፋለን” ማለታቸው፣ የተውሸለሸለ አስተሳሰብ እንደነበር በዘርፉ ምሁራን ሲተች ቆይቷል፡፡ ከዓለም አቀፉ ሕግ ጋር ፊት ለፊት ላለመላተም የሚያደርጉት የዲፕሎማሲ ብልጣ ብልጥነት እንደሆነም የሚታመን ነው፡፡

የካይሮ ዲፕሎማሲ ከራር አቋምን የተላበሰ ሆኖ ለመቆየቱ በየጊዜው በሚደረጉ መድረኮች ተወያዮችም ይባሉ ተደራዳሪዎች ያያዙትን ገንታራ አቋም በማራመድ፣ ተቀባይነትን ሲያጡ ስብሰባ ረግጠው ወይም የድርድር መርሐ ግብርን አቋርጠው የሚሄዱ የመሆናቸው እውነታ ነው፡፡

ለአብነት ያህል ከሦስት ዓመታት በፊት ካርቱም ውስጥ በተካሄደ “የምሥራቅ ናይል አገሮች የምክክር መድረክ” ላይ አዘጋጆቹ ኢትዮጵያና ሱዳን በህዳሴው ግድብ የግንባታ ሒደት ላይ ያላቸውን ተመሳሳይ አቋም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የባለሙያዎች ማብራርያ አስደግፈው ማቅረብ በመቻላቸው ምክንያት፣ የምክረ ሐሳብ ሒደቱን ለመታዘብ በሥፍራው ከታደሙ የበርካታ አገሮች አምባሳደሮች ዲፕሎማሲያዊ  ከበሬታን አግኝተዋል። ቀደም ሲል የዚሁ “የምሥራቅ ናይል አገሮች የምክክር መድረክ’’ የተሰኘው ተከታታይ ውይይት አባል የነበረችው ግብፅ በአንፃሩ፣ መድረኩን ጥላ እንደወጣችና ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን የህዳሴ ግድብ ለማስቆም ያለመ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ ፊቷን ወደ ምዕራባውያኑ ኃያላን መንግሥታት እንዳዞረች አይዘነጋም። ምንም እንኳን ይኼ አካሄድ የትም የሚያደርስ እንዳልነበር ዘግይተው የተረዱት ቢሆንም፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን ታላቁ የህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ ስለተገነባ የታችኞቹን የተፋሰሱ አገሮች ህልውና ሊፈታተን የሚችል አሳሳቢ ችግር ሊፈጠር ቀርቶ፣ ከቶንውም ከግድቡ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን በጎ ውጤት እንደሚያመጣ የጋራ ግንዛቤ ከመጨበጣቸው የተነሳ፣ ይኼንኑ የትብብር መንፈስ ይበልጥ እያጎለበቱት መቀጠላቸው አንድ ገንቢ ዕርምጃ ነበር፡፡

ይሁንና በግብፅ ፖለቲከኞች በኩል ነገሩ የተዋጠላቸው አለመምሰሉ ሌላኛው የሰሞኑ የካይሮው ዲፕሎማሲ ማጠንጠኛ እንደሚሆንም ተገምቷል፡፡ በተለይ ከሰሞኑ የሱዳንና የግብፅ የይዞታ ይገባኛል ውዝግብ አንፃር፣ የሱዳንና የኤርትራ ድንበር የመዝጋት ዕርምጃና የመካካለኛው ምሥራቅ ኃያላን አገሮች አሠላለፍ አወዛጋቢነት  አኳያ፣ ነገሮች ከአገራችን ዘላቂ ጥቅም እኳያ እየተመዘኑ መታየት እንዳለባቸው ጥርጥር ለውም፡፡

እንዲያው ለነገሩ ቢሆንስ የቅርብ ጊዜዎቹን የዓባይ ጉዳይ የዲፕሎማሲ ነጥቦችን አነሳን እንጂ፣ የኢትዮጵያና የግብፅ መንግሥታት በተመጣጣኝ ደረጃም ባይሆን በናይል ውኃ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ ሳይነጋገሩ ቀርተው አይደለም፡፡ ይሁንና በቀደሙት  ሥርዓቶች በታችኛው ተፋሰስ አገሮች በተለይም በግብፅና በአጋሮቿ በነበረው ጫና፣  በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ በነበሩ መንግሥታት የአቅም ማነስና የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ መዳከም ምክንያት፣ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ሕዝቦች  ከውኃው ተጠቃሚ ሳይሆኑ ዘመናት እንዲያልፉ የካይሮ የፖለቲካም ይባል የዲፕሎማሲ የበላይነትና ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው የተፋሰሱ አገሮች መዳከም አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም የፈርኦናዊያን ገዥዎች በየዘመናቸው የተዛባውን የውኃ አጠቃቀም  በመላው ግብፃውያን ልብ ውስጥ ሳይቀር ሸንቅረው ሲያደናግሩት እንደኖሩ የተለያዩ  አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በርካታ ግብፃዊያን ዓባይ ከየት እንደመጣ መገንዘብ የጀመሩት ከኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት የታላቁ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ሥራው ሲጀመር ታላቅ አገራዊ ሕልምና ተስፋ ሆኗል፡፡ የዛሬው ብቻ ሳይሆን የመጪውም ትውልድ ታላቅ አገራዊ የልማትና የዕድገት ራዕይ በተግባር የሚገለጥበት ግዙፍ ግድብ እንደሆነ ታምኖበት፣ ከዘመናት ቁጭት በኋላ እተከናወነ የሚገኝ ታላቅ ፕሮጀክትም ነው፡፡ ለዚህም ነው በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ በአሁኑ ጊዜ የታላቁ ህዳሴ ግድብ 63 በመቶ የግንባታ ደረጃ ላይ መድረሱን መንግሥት እየገለጸ የሚገኘው፡፡

ይህ ግድብ ሲጀመር አንስቶ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ለግርጌው አገሮች ግልጽነት የመፍጠር ሥራን ሲያከናውን መቆየቱም አይዘነጋም፡፡ የውኃ ፍሰቱ ላይ ለሚነሳ ሥጋት ማረጋገጫ ለመስጠት ጥናት እንዲጠናም መፍቀዱም አይዘነጋም፡፡ ከዚህ አገራዊ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሕዝቦችም ትልቅ ትርጉም ካላው ፕሮጀክት ትግበራ ጋር በተያያዘ በቀዳሚነት ስማቸው የሚጠቀሰው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ “መሐንዲሶቹም እኛ፣ አናጢዎቹም እኛ፣ ግንበኞቹም እኛ ሆነን በታላቅ አገራዊና ሕዝባዊ መነሳሳት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በራሳችን አቅም፣ ያለ አንዳች የውጭ ዕርዳታና ዕገዛ እንሠራዋለን፤” ባሉት መሠረት ልጅ አዋቂው፣ አርሶ አደሩ፣ ምሁሩ እንዲሁም በውጭና በአገር ውስጥ ያለው ሕዝብ ከሞላ ጎደል እየተሳተፈበት ያለና ቢያንስ በሐሳብ እየደገፈው ያለ ፕሮጀክትም ለመሆን በቅቷል፡፡ ዜጎች በመንግሥት ላይ ባላቸው ቅሬታ፣ እንዲሁም በፖለቲካና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሻሻልና የልማት መስፋፋት ፍላጎታቸውም እየናረ ባለበት ወቅት እንኳን፣ በህዳሴው ፕሮጀክት ላይ ድርድር እንደሌላቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያነሱ መደመጣቸው የፕሮጀክቱን ትውልድ ተሻጋሪነትን የሚያመላከት እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅምሩ ጀምሮ ብዙ ያከራከረ፣ ብዙ የተባለለት፣ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረትን የሳበና ያነታርከ የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በራስዋና በልጆችዋ አቅም የጀመረችውን የግድቡን ግንባታ ቃሏን ጠብቃ ወደ ፍፃሜው ለማድረስ በትጋት እየሠራች ትገኛለች፡፡ አሁንም ቢሆን ቢቻል በድርድር መግባቢያው መሠረት ካልሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት በፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በደረሰበት የውሳኔ አግባብ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታው አስፈላጊው ደረጃ ላይ ሲደርስም የውኃ መሙላትና ማከማቸቱ ተግባር በየደረጃው እንደሚቀጥል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በመሆኑም የዓባይ ወንዝ የእኛው ቢሆንም ድንበር ተሻጋሪና ዓለም አቀፍ ወሰኖችን የሚያቋርጥ በመሆኑ ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ ግድቡን ከሠራች የውኃው ፍሰት ይቀንሳል በሚል፣ በተለይ የግብፅ ፖለቲከኞች በየዘመኑ የሚያነሱትን ሥጋት ተኮር እሳቤና ሴራ በመተው ወደ መደራደርና መስማማት መምጣት ይጠበቅባቸዋል መባሉም ለዚሁ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከአሁኑ የመሪዎቹ ምክክርም ሆነ በቀጣይ ከሚካሄዱ ምክክሮች እውነተኛውን መተማማን መፍጠር ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቅ ነው፡፡ በመሠረቱ ተደጋግሞ እንደሚባለውም ሆነ አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ እየተከተለው ያለው መንገድ እንደሚያሳየው፣ አገራችን በሰላም የምታምንና ሰላም አክባሪ ነች፡፡ የዓባይ ውኃ በጋራ እንድንጠቀምበት ተፈጥሮ የሰጠን፣ የተጋሪዎቹም የጋራ ሀብት ስለሆነ በጋራና በሰላም ልንጠቀምበት እንችላለን በሚል ዛሬም በእምነትዋ ፀንታ ቀጥላለች፡፡

ያም ሆኖ ይህ እውነትና እምነት የማይዋጥላቸው አካላት (በተለይ ግብፅና ከጀርባዋ እንዳሉ የሚገመቱ አንዳንድ የአገራችን ባላንጣዎች) እንደ ጥንቱ የሴራና የደባ ዘመን ሁሉ፣ ዛሬም አገራችንን ለማደናቀፍ እንደማይቦዝኑ የሚናገሩ ተቆርቆሪዎች አሉ፡፡ ምንም እንኳን አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ የግብፅ መሪዎችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አባላት በውይይት መንፈስ ውስጥ እንዳሉ ባይታበልም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በተለይም በኤርትራ በኩል የግብፅ ጦር እንቅስቃሴ መታየቱና የሱዳን መንግሥትንም ጫና ውስጥ የሚከት የሚመስል ተግባር መንፀባረቁ የሰላም እንዳልሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ነገ ለኢትዮጵያ ሌላ የሥጋት ምንጭ እንዳይሆን ከወዲሁ ቀዳዳውን በንቃት መድፈንም ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት የዓባይን ወንዝ ውኃ በመጠቀም የማልማት መሠረታዊ መብት እንዳላት፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ከውኃው ማግኘት ያለባቸውን ድርሻ ያገኛሉ ብላለች፡፡ የግድቡ መሠራት በውኃው መጠን ላይ የሚያደርሰው ችግር እንደሌለ፣ ግድቡ የአካባቢውንም አገሮች ተጠቃሚ ያደርጋል የሚለውን አቋሟን በተደጋጋሚ እያንፀባረቀች ትገኛለች፡፡ እስከ ሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የካይሮ ጉብኝት ድረስም እየተደመጠ ያለው ንግግር ማጠንጠኛው ይኼው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ አገሪቱ የያዘችው ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ በጠንካራ መርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አመላካች ነው፡፡

ኢትዮጵያ  ዛሬም ለእኔ ብቻ ሳትል የዓባይ ውኃ ሁላችንም በጋራ እንድንጠቀምበት ተፈጥሮ የሰጠችን በረከት ስለሆነ ለውዝግብ መነሻ ሊሆን አይገባም በሚለው እምነት መፅናቷ የሚያስመሰግናት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ተገቢና ትክክለኛ አቋምም  ነው፡፡ ግብፆች የእነሱ ያልሆነው የተፈጥሮ ሀብት ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗን እያወቁ የዓባይ ውኃ ታሪካዊ ባለቤቶች ነን በማለት ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ለማድረግ ቢሞክሩ ዓለም እንደማይቀበላቸው ያውቁታል፡፡ ስለሆነም በእጅ አዙር የማዳከሚያ ሥልትን እንደ አማራጭ ይዘው ሊቀጥሉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው በዚያ በኩል ነው የሚሉ ምክሮች እየበዙ መጥተዋል፡፡

ባለፉት ዘመናት የግብፅ መንግሥታትና ሕዝቦች ለዘመናት በዓባይ ውኃ ሲጠቀሙ፣ የተለያዩ ግድቦች ሲሠሩ፣ ልማቶችን ሲያካሂዱ፣ ሰው ሠራሽ ሐይቆችን ሲፈጥሩ፣ ታላላቅ የሙዝና የብርቱካን እርሻዎችን በማልማት ለዓለም አቀፍ ገበያ እያቀረቡ ብሔራዊ ገቢያቸውን ሲያሳድጉ፣ ወዘተ ባለቤቷ ኢትዮጵያ በራስዋ የዓባይ ውኃ ግድብ እንዳትሠራ ዓለም አቀፍ ጫና እስከ መፍጠር ተራምደው እንደነበር ሊካድ አይችልም፡፡ በዚህ ጦስ እኛ በድርቅና ድህነት አዙሪት ውስጥ ስንዋትት እነሱ በፈጣን ዕድገት ወደ መካካለኛ ገቢ ተርታ እስከ መሠለፍ መድረሳቸውም የተደበቀ እውነት አይደለም፡፡

ግብፅ በዓባይ  ተጠቃሚነት ብዙና ሰፊ  ነው፡፡ ለአብነት ያህል ከአገሪቱ የመጠጥ ውኃ፣ ቱሪዝምና መዝናኛ ባሻገር አንዱን ፕሮጀክት የግብፅ አስዋን ግድብ እንኳን ብንመለከት ግብፅን ወደ 840 ሺሕ ሔክታር መሬት ዓመቱን በሙሉ በመስኖ እንድታለማ  ያደረጋት ነው፡፡ ዋና ዋና የግብፃዊያኑ ምርቶች ጥጥ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ሩዝና ስንዴ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይኼ ሁሉ ተዳምሮ ግብፅ ምዕራብና ምሥራቅ አፍሪካን እ.ኤ.አ. 1964-1965 እና 1975-1979 ያጠቃው ድርቅ እንዳልደረሰባት በታሪክ ተከትቦ ይገኛል፡፡

ግብፅ የራሷን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ አሟልታ ለሌሎች አገሮች ኃይል እስከ መሸጥ የደረሰችውም በዚሁ መንገድ ነበር። ሱዳን፣ ሊቢያና ቻድ ግብፅ የኤሌክትሪክ ኃይል የምትሸጥላቸው አገሮች ናቸው። አሁንም በቀጣይ ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል በማመንጨት ገበያዋን ማስፋፋት እንደምትሻ በዕቅድ ሰነዶች ተጠቅሶ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ በተለያየ መንገድ ለማደናቀፍ ከመጣር ትቆጠባለች ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል የሚሉ አስተያየቶችንም ንቆ መቀመጥ ያዳግታል።  ያም ሆኖ አሁን በመሪዎች ደረጃ የተካሄደውን ውይይትም ሆነ የድርጊት መርሐ ግብር በአዲስ ተስፋና በቀናነት መመልከት ተገቢነት አለው፡፡

በመሠረቱ አሁንም የኢትዮጵያና የግብፅ ዲፕሎማሲ ገባ ወጣ ማለቱ ጥርጣሬ ማጫሩ እንጂ፣ ኢትዮጵያ በዕድገት ላይ እንዳለች፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በማታቋርጥበት ቁመና ላይ መገኘቷን ግብፃዊያኑ በሚገባ  ተገንዝበዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጀመረችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በምንም መንገድ ሊቆምና ሊገታ እንደማይችል ብቻ ሳይሆን፣ የግብፅን ሕዝብ ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት የመገደብ ፍላጎት እንደሌላትም በተለይ ምሁራኑና ሚዛናዊ እይታ ያላቸው ዜጎች የተገነዘቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ይሁንና በድርድር ስም ማንገራገሩም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጫና የመፍጠር ጥረቱ የሚመነጨው ‹ይቺ ጥሬ ከዋለች ካደረች …› ከሚለው የሥጋት ፈሊጥ እንደሆነ ዕሙን ነው፡፡ አገራችን በዓባይ ላይ ተጨማሪ የውኃ ፍላጎቶችን እንዳታሳድር በድርድር ለማሰር እንደሆነም በርካታ የዘርፉ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

ማጠቃለያ

ውኃ ያውም ድንበር ተሻጋሪ የገጸ ምድር ውኃ ማንንም አገር የሚያወዛግብ ነው፡፡ በአንድ በኩል ውኃ አመንጪ አገር አለ፣ በሌላ በኩል ከሚመነጭ የተፈጥሮ ውኃ በጋራ የሚጠቀም ወገን አለ፡፡ በእነዚህ ወገኖች በኩል የሚነሳ የፍላጎት ግጭት ነው ውዝግብ ሊያስነሳ የሚችለው፡፡ ለአብነት ያህል ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ የመጀመርያው የውኃ አጠቃቀም ውዝግብ የሚባለው ‹‹የሃርሞን ቀኖና›› በሚል ስያሜ የሚጠራው እ.ኤ.አ. በ1895 በአሜሪካና በሜክሲኮ መካከል “የሪያ ግራንዴ” ወንዝ የጋራ ውኃን ስለመጠቀም የተነሳው ውዝግብ ነው፡፡

ከዚያም ወዲህ ምንም እንኳን የከፋ ግጭት እስከ መቀስቀስ ያደረሰ አደጋ የተከሰተበት ታሪክ ባያጋጥምም፣ የድንበር ተሸጋሪ ወንዞች አጠቃቃም ሲያወዛግብ መታየቱ አልቀረም፡፡ ከዚህ አንፃር በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በናይል ተፋሰስ አገሮች መካካል የሚታየው የውኃ አጠቃቀም ውዝግብና ንትርክ መለስተኛ የሚባል እንጂ የሚጋነን እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ የግብፅም ሥጋት ቢሆን ለዘመናት የራስ ያልሆነን ጠቅልሎ በመያዝ ከመጠቀም ፍላጎት የሚመነጭ አደጋን በምናብ ከመሳል የሚመነጭ እንደመሆኑ በሰከነ መንገድና በመተማማን ማስገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት መረጃ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 63 በመቶ ደርሷል፡፡ በተቀመጠለት አቅጣጫ መሠረት ሥራው ሌት ተቀን በተጠናከረ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ የግድቡ እዚህ ደረጃ መድረስ ራሱን ችሎ ታላቅ አገራዊ ስኬትና ድል ቢሆንም፣ አሁንም የመጨረሻው ድል ግን ግድቡ ተጠናቆ በተሟላ መንገድ ኃይል ማመንጨት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የተጣለባቸውን ታሪካዊና አገራዊ አደራ ሳያዛንፉ መወጣት አለባቸው፡፡ እነ ግብፅም ቢሆኑ ከቀልባቸው ሆነውና ከተንሻፈፈው የታሪክ ውዝግብ ወጥተው በሠለጠነው የሰጥቶ መቀበል መርህ መጓዝና የጋራ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ብቻ ይበጃቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...