Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሆይ!

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሆይ!

ቀን:

ከጥቅማችሁ በላይ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለች!

በገነት ዓለሙ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. ‹‹ጥልቅ›› የግምገማና የውሳኔ ዜና እና ሪፖርት ዛሬም ጥር ወር አጋማሽ ላይ እያለንም በእንጥብጣቢ ከሚነገረን በላይ፣ የፓርቲውንም ሆነ የመንግሥትን ሙሉ እምነትና ሁሉንም እውነት ዝርግፍ አድርጎ የሚያሳይ አይደለም፡፡ የዓለም የመገናኛ ብዙኃንና ስም ያላቸው መንግሥታትና የመንግሥታት ማኅበራትና ቡድኖች በተለይ ትኩረት ሰጥተው ዜና ያደረጉትና ያበረታቱት፣ ‹‹የታሰሩ ፖለቲከኞች›› ወይም ‹‹የፖለቲካ እስረኞች›› ጉዳይም ገና እንዳወዛገበ ነው፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ሰኞ ጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ ያደረጉት ‹‹የአጭር ጊዜ›› ውስጥ በተለይም ደግሞ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ይፈም ዘንድ ቀጠሮና አጀንዳ የተያዘለት ተከሳሾችን ክስ በማቋረጥ፣ ፍርደኞችን ይቅርታ በማድረግ ከእስር የመልቀቁ የመጀመርያው ዙር ዕርምጃ ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ደረጃ 115፣ በጠቅላላው 528 እስረኞች መለቀቃቸው እውነት ነው፡፡ እነዚህ የመጀመርያ ዙር ተፈቺዎች፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ መግለጫ መሠረት በ‹‹መጀመርያው ዙር፣ በፈጣን ሁኔታ ልንደርስ የቻልንበትን ያህል ደርሰን›› የተለዩ ናቸው፡፡ ለጥቆም፣ ‹‹በተቀመጠው መመዘኛና መሥፈርት መሠረት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በክሱ ሒደት ላይ ያሉ የተጠርጣሪዎች ጉዳይ እየተጠና ለግብረ ኃይሉ ይቀርባል፡፡ በግብረ ኃይሉ እየፀደቀ የክስ ሒዳታቸው በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲቋረጥ የሚደረግበት ሁኔታ ተጠናክሮ . . . ›› ይቀጥላል፡፡

- Advertisement -

የተፈረደባቸው ሰዎች ጉዳይም በክልልም በፌዴራልም ደረጃ ዝርዝር ጥናት ከተደረገ በኋላ ለሚመለከታቸው የይቅርታ ቦርዶች ይቀርባል ተብለናል፡፡

ሁለት ወራት፣ ‹‹እንዴት ሆኜ አድሬ?›› የሚል ጥያቄ የሚያስነሱ ረዥም ጊዜ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩ ፖለቲከኞችን ለይቶ፣ አንጠርጥሮ፣ ቆጥሮ፣ ‹ስለእናት አገር ፍቅር የጥላቻ ፖለቲካ ይቅር ብሎ ሁለተኛም በማያዳግም ሁኔታ ይህን የመሰለ የጀግንነት ጀብዱ የማከናወን ተግባርም ለአላስፈላጊ ረዥም ቀጠሮ ተዳረገ አንልም፡፡ አያያዙ ግን ከወዲሁ ጥርጣሬ ይፈጥራል፡፡ የነበረውን አለመተማመን ያጠነክራል፡፡ ካልታዘልኩ አላምንምን ወደ ‹‹እከሌን ማመን ቀብሮ ነው›› ይለውጣል፡፡

ይህን የሚያሳዩ ማመላከቻዎችን ልጠቁም፡፡ ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም.  ከተፈቱት ‹‹የፌዴራል›› 115 እስረኞች መካከል አንደኛውና የታወቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡ ዶ/ር መረራ የታሰሩት ከእነ ብርሃኑ ነጋ፣ ጃዋር መሐመድና፣ እንዲሁም ከኢሳትና ከኦኤምኤን ቴሌቪዥኖች ጋር ተከሰው ነው፡፡ የተቋረጠው ክስ ‹‹እነ መረራ ጉዲና›› ብሎ ከሚጠራቸው ተከሳሾች መካከል የክስ መቋረጡ ስታትስቲክስ እንኳን በይፋ ያስመዘገበው የአንድ ተከሳሽ ብቻ ነው፡፡ በአምስቱም ተከሳሾች ላይ በጠቅላላው አራት ክሶች ሲቀርቡ፣ በክሶቹ ዝርዝር ውስጥ በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥቱ ሥርዓት ላይ ወንጀል መፈጸምና የሽብር ወንጀል ድርጊትም ተካትተው ነበር፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ቀጠሮ ላይ በቆየው በዚህ የክስ መዝገብ ከተቆጠሩት አራት ‹‹የደረጃ ምስክሮች›› መካከል ሁለቱ ብቻ የተሰሙበት ይህ ጉዳይ፣ ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎች ሊሰሙበት ተለዋጭ ቀጠሮ የተያዘው ለጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም ሲል በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በኢሕአዴግ መካከል የተካሄደው በፀረ ሽብር ሕጉ ላይ የሚደረገው ውይይት ነበር፡፡   

የኢሕአዴግ ዋነኛው ችግሩና አሁን ለደረሰበት ያበቃው ተቃውሞን የሚያስተናግድበት ዋናው መንገዱ ነው፡፡ የማያወላውል ቅጣት መስጠቱ፣ ቃታ ለመሳብ መቸኮሉ፣ እንቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው ማለቱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር የተጀመረው ከ2008 ዓ.ም. በኋላ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ፣ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ባህል ያደረገው አሠራሩ ነው፡፡ ሕግን አክብረውም ይሁን ተላልፈው ወደ ጎዳና የሚወጡትን ሰላማዊ ተማሪዎች ሆነ መምህራን፣ ምዕመናን ይሁን ሌላ፣ ቀድሞ የሚያናግራቸው ሹም ሳይሆን ቃታ ነው፡፡ አሳውቆ የመሰብሰብና ሠልፍ የማካሄድ፣ ተቃውሞ የማሰማት መብት አይከበርም፡፡ እንኳን አሳውቆ ፈቃድ ተለምኖም የማይሆን እየሆነ መጥቷል፡፡ ጨክኖ መብትን በተግባር ለማዋል ሲሞከርም በማያወላውል ጥይት መቀጣት አይቀሬ ሆኖ ተሾመ፡፡

በዚህ ‹‹ሁሉ በጄ›› ባህርይው ላይ ነው መንግሥት በስመ ፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ሰውንና ቤትን እንዳሻ መፈተሽን፣ ደብዳቤና ስልክን፣ ወዘተ መጥለፍን ሁሉ የሚፈቅድ የልማት አውታሮችንና ሰላማዊ ዜጎችን አዘናግቶ በማጥቃት የሽብር ቀውጢ መፍጠርን ገድሉ ያደረገ እንቅስቃሴን ነጥሎ ዒላማው ያላደረገ አስፈሪ አዋጅ ተጨመረበት፡፡ ኢሕአዴግ በሚስጥር የመደራጀት ሙከራንና የትጥቅ ትግልን፣ ሌላው ቀርቶ በሕጋዊ የሕዝብ ስብሰባና ሠልፍ ላይ ብልጭ የሚል ቁጣና የሕግ ጥሰትን ሁሉ በሽብርተኝነት እፈርጃለሁ አለ፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የኢሕአዴግ ሕግን የመጣስና የተቃዋሚ ማጥቂያ አድርጎ የመጠቀም ልማድ ብቻውን ቦርቃቃውን የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ለመቃወም በቂ ምክንያት ነው፡፡ ‹‹የፖለቲካ እስረኛ›› ማለትን ያመጣው ይኼው ተቃውሞን መተናነቅ ነው፡፡

በዚህ ላይ ደግሞ ተቃውሞ፣ ጥላቻ፣ ያጠነነ ብሶትና መጠራጠር በደራበት ፖለቲካ ውስጥ ገዥዎች አሁንም በዓለ ጥምቀትና ቃና ዘገሊላ ላይ ብልህነት አጥተው አደባባይ የወጣ አቤቱታንና ቅዋሜን ማብረድ እያቃታቸው፣ የጥፋትና የብጥብጥ ኃይል አድርገው እየኮነኑ ቃታ፣ ጅምላ እስራትና ‹‹ተሃድሶ›› በሚወድ አልሸነፍ ባይነት ላይ ሲደርቁ ሌላ የሚፈነዳ ቁጣና እልህ ሲያመርቱ፣ ከበፊቱ የበለጠ ብዙ ሰዎችን አበራክቶ አደባባይ የሚያወጣ ተቃውሞ ሲጠሩ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሲሆኑ እናያለን፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር መንስዔ የፖለቲካ ኃይሎች ትግል ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ ይህን ያደረገውና ለዚህም ተጠያቂው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ስለ ‹‹የሕግ የበላይነት›› ሲያወራ፣ ስለሕግ ማስከበር ሲናገር ግን በዚህ የሚጠረጠር አይመስልም፡፡ እውነቱ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የመጀመርያውን የጨዋታ ሕግ ያፈረሰው ኢሕአዴግ ነው፡፡ እሱ ራሱ ሰላማዊ የሐሳብ ትግልን ከተቃዋሚዎች ጋር ማድረጉን ትቶ፣ የመንግሥት ኃይልን ብቸኛው መድኅኑና ዘዴው አድርጎ መጠቀምና መመካት ተያያዘ፡፡

ይህም የዱሮ አባሪዎች ሳይቀሩ እየካዱ በግልጽ ተቃዋሚነት እንዲወጡ፣ አዲሶችም እንዲቋቋሙና የተቃውሞውም ደረጃ እያደረ እየተዳከመም፣ እየሰፋም፣ የአገሪቱን ሰላም በየቦታው የሚፈትን አደጋ ሆነ፡፡ የዚህ መነሻ ኢሕአዴግ ራሱ እንደ ፓርቲ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት ለመለወጥ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዞ ለመገኘት አለመቻሉ ነው፡፡ በረሃ ከለመደው የጦርነት ሥልት መውጣት ባለመቻሉ ገና ‹‹ሀ›› ሳይባል በተማሪው/በተማረው ኃይል ላይ በሰነዘረው ጥቃትና ጥላቻ ዛሬ የደረሰበትን ረዥም የቁጣ መንገድ መርቆ ከፈተ፡፡ ኢሕአዴግ በየትኛውም ሥርዓት የተማረው ክፍል የፖለቲካ ልዕልና ማግኛ መሣሪያ መሆኑን ሊገነዘብ ባለመቻሉ፣ ከሕዝብ ጋር ሊኖረው የሚፈልገውን የፖለቲካ አግባብ ለመፍጠር የሚያስችለውን ዋና መንገድ ገና ከመጀመርያው ጥርቅም አድርጎ ዘጋው፡፡ በመብቶች ውስጥ መኖር መጀመራችንን ዛሬም በቀጠሮ ያሳደረው በፖለቲካ መንጓለልን፣ በጥቅም መደለልን የአገር ዋና ዘይቤ አድርጎ ያቋቋመው፣ የፖለቲካ እስረኞችንም የፈለፈለው ይኼው የኢሕአዴግ የራሱ ከሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ውጪ መሆን ነው፡፡     

የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎቹ ትንቅንቅ በተለይም የኢሕአዴግ የራሱ ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ እስከሆነ ድረስ ለአገሪቱ የፖለቲካ ሰላም ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ በድርድርና በዕርቅ ተቀራርበው በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለሕዝቦች አዲስ ሕይወት ሊበጁ የሚችሉ ወገኖች መቀናደብ፣ ለቡድኖቹም ለአገሪቱም ሕዝቦች በምንም ዓይነት ጥቅማቸው ሊሆን አይችልም፡፡ መቀራረብ የሚቻልበትን መንገድ የመፈለግ ተግባር የሽብርተኝነትና የትርምስ ማጥ ባልደረቀበት አካባቢ ለምትገኝና ከማዶዋ የእነ የመንና የእነ ሶሪያን አወዳደቅ እየተመለከተች ላለች አገር ቸል የማይባልበት ነው፡፡

የውስጥ ተቃዋሚን ማዳከም ለኢሕአዴግ ጥንካሬ እንዳልሆነው፣ ከውስጥ ያስቸገሩ ተቃዋሚዎችንና አፋኞችን አስደንብሮ ወደ ውጭ እንዲፈረጥጡ ማድረግም መገላገል እንዳልሆነ፣ ከውጭ ሆኖ መቆሚያ መቀመጫ መንሳት እንደሚቻል ይኼው የቅርብ ልምዳችን ወለል አድርጎ አሳይቷል፡፡ በፖለቲካ ሰላም ላይ ያልተመሠረተና በስነጋ የተገኘ የሕዝብ ፀጥታ ያፈተለከ ቀን ምን ያህል መዝረክረክና ጥፋት ሊያመጣ እንደሚችል፣ የቁጣ መፈንጃ መዘዝ እየሆኑ ያሉት ሕዝብን ያስመረሩ የአገዛዙ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራት እንደሆኑ መማር ለሚሻ ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. (የቀጠለ) የፖለቲካ ቀውስ ልምድ ከበቂ በላይ ነው፡፡

በኮንፈረንስና በሥልጠና ስም ብዙ የሕዝብ ገንዘብ ሲያነክት የቆየውና የኢሕአዴግን ሥልጣን ለኢትዮጵያ ልማትና ሰላም ብቸኛ ቁልፍ ያደረገና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የብሔሮች እኩልነት ተረጋግጧል፣ ብሔረሰባዊ የበላይነት ተሰርዟል የሚል ፕሮፓጋንዳ ከንቱ ጩኸት ከመሆን አልፎ ቁጣ ሊጭር የሚችል ሆኗልና ሊቆም አሊያም ሊያስጠይቅ ይገባል፡፡ የቅርቡን የቁጣ ማዕበል ንብረት አውዳሚነት እያነሱ መንቀፍ እንኳ ለኢሕአዴግ መንግሥት የተቆርቋሪነት ብልጫን የሚያቀዳጀው ሳይሆን፣ ከቅዋሜ ፍንዳታ በፊትም ሆነ ከዚያ ወዲያ በነበረ ረዥም ጊዜ ውስጥ ከውድመት የሚያርቅ መፍትሔ ያለመስጠት፣ ጥፋተኝነቱንና በዚህም ለደረሰው ውድመት ተጠያቂነት እንዳለበት የሚያስታውስ ነው፡፡

ከመስከረም 2009 ዓ.ም. ጀምሮ  የተካሄዱት ከኢሕአዴግ ግቢ ያልራቀ የካቢኔ ሹም ሽርና ሽግሽግም የፓርቲ የሥልጣን አካላት፣ ብወዛ፣ ወዘተ ቢሆን መሠረታዊ የዴሞክራሲ ለውጦች ተከትለውት እስካልመጡ ድረስ ዕርባናው ገርሮ የነበረ ቅዋሜን ከመደለልና ከካቢኔ ወይም ከፓርቲ ጀርባ ያለ አምባገነናዊ ማጅራትን ከመከለል አያልፍም፡፡ የፓርላማ አወካከልን ሥርዓት ማስፋት ለዴሞክራሲ ግንባታችን የሚበጅና አስፈላጊ ቢሆንም፣ ብቻውን ትንሽ ነገር ነው፡፡ በዋናነት ለከተማና ለገጠር ወጣቶች ሥራ የመፍጠር ተግባር ከተቃናልኝ ወጣቱን ከቅዋሜ ውጪ አደርጋለሁ፣ ለተቃዋሚዎች የፓርላማ ወንበሮች አቃምሼ በተለመደው የምርጫ ጨዋታዬ ሥልጣኔን አረዝማለሁ የሚል ንድፍ ተይዞ ከሆነም ንድፉ የእሳት መንገድን የመረጠ ጅልነት ነው፡፡

የኢሕአዴግ በውድም በግድም በሥልጣን ላይ መቆየት ለመደቤ/ለአካባቢዬ ጥቅም ይበጃል፣ ኢትዮጵያም የልማት ገነት ትሆናለች ብለው የሚያስቡ ካሉም ዓይናቸውን ከፍተው ያለፈውን (ገና ያላለፈውን ጭምር) የቁጣ መዓት ውስብስብ ፈትል ቢመረምሩ ይሻላቸዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ለአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ጠንቃቃና የተሟላ መፍቻ ከመስጠት መቦዘንና በድብስብስ ለመግዛት መሞከር ድንገት ፈንድቶ ገዥንም አገሪቱንና ሕዝቦቿን ሊበላ ለሚችል ገሞራ ማጋለጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ምን ያህል የቋያ አደጋ ውስጥ እንደሆኑ በትክክል ለመረዳት የሚሹ የሚያስፈልጋቸው በምድሯ ውስጥ ከላይ እስከ ታችና ከአዲስ አበባ እስከ ዳርቻ ድረስ በየዕለቱ ስንት የሚያበግኑ ጥፋቶችና ሸሮች እንደሚፈጸሙ፣ እነዚህ ብቻቸውንም ሆነ ከውጭ ጠላት ሴራና ከሽብርተኝነት ትንኮሳ ጋር ተገናኝተው ምን ያህል አቅጣጫው አስቀድሞ የማይታወቅ ድንገተኛ የቁጣ እሳት ሊያቀጣጥሉ እንደሚችሉ ማስተዋል ብቻ ነው፡፡

 የኢትዮጵያ ሕዝቦች ህልውናና ዕጣ ከአንድ ቡድን የሥልጣን ጥቅም በላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግም የሕዝብን ጥቅም የሚያበልጥ ከሆነና ከሽንገላ ያለፈ “ዴሞክራሲን የማጥለቅና የማስፋፋት” ዓላማ ካለው፣ እስከ 2012 ዓ.ም. ምርጫ ድረስ ምን ምን ለመሥራት እንዳቀደ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ዴሞክራሲ የሚጠልቀውና የሚስፋፋውም በካድሬያዊ ስብከት አዕምሮን ለመቀየር በመሞከር አይደለም፡፡ ኢዴሞክራሲያዊነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ከሰዎች መራገፍ የሚችለው ሕይወት ራሷ የካድሬነቱን ቦታ ከወሰደችና ዴሞክራሲና ተሃድሶን ለመስበክ ከቻለች ነው፡፡ ማለትም የዴሞክራሲ ነፃነቶች በተግባር ተከብረው በማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ሲሠሩ፣ በነፃነት መወያየት/መከራከር፣ መደራጀትና መንቀሳቀስ ዕውን ሲሆኑ፣ የአጥፊዎች ተጋላጭነትና ተጠያቂነት ከታች እስከ መንግሥት አናት ድረስ የሚሠራ ሆኖ ሽፍንፍ ሽፍጦችና ስርቆቶች ከወዲሁ መሸማቀቅ ሲደርስባችው፣ በሥራ ማደግና መኩራት ወለል ተደርጎ በር ሲከፈትላቸው ነው፡፡ መልካም አስተዳደር የሚበቅለው ከዚህ ዓይነቱ ለውጥ ነው፡፡

ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ከወረት የዘለለ ዕድሜ ሊኖራቸው የሚችለው ደግሞ ህልውናቸው ከሥራ አስፈጻሚው በጎ ፈቃድ ውጪ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይኼውም የሥልጣነ መንግሥቱ ወታደራዊና ሲቪል ዓምዶች ከቡድናዊ ሙሽትና መረባዊ ውጦሽ ሲፀዱና ሲጠበቁ፣ እንዲሁም የሕግ ተርጓሚው፣ የሕግ አውጪውና የአስፈጻሚው የሥልጣን ዘርፎች፣ የመባለግ ዝንባሌዎችን ለመቆጣጠር በሚያስችል ተገናዛቢነት ሲደራጁ ነው፡፡

እነዚህ ተግባራት በኢትዮጵያ ውስጥ ዕውን የመሆናቸው ጉዳይ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን በጥንቃቄና በብልኃት እየተጠቀሙ የአገሪቱን ጣጣዎች ለማቃለል ከመቻል ጋር በቀጥታ የተቀራኘ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ቢፈጠርም የሐሳብ ሥርጭቱ፣ ቅስቀሳና ክርክሩ ሁሉ የመመራረዝና የመጠማመድ ክንዋኔ ከሆነ፣ ከዚሁ ጋር የተፋተሉ የሠልፍና የንቁሪያ ጋጋታዎች ምኅዳሩን ካመሱ፣ የምርጫ ውድድሩም ሸፍጥ፣ የገንዘብ ጉርሻ፣ ማስፈራራትና የኃይል ተግባራት ሁሉ የተሠማሩበት ግብግብ ሆኖ ካረፈ ልፋቱ ሁሉ ዞሮ ዞሮ እዚያው የፍጅት እሳት ውስጥ መግባት፣ ከዚያም ካነሰ ደም አፋሳሽ በሆነ ወታደራዊ ግልበጣ መድፈጥፈጥ ይሆናል፡፡

መመራረዝን ከፓርቲዎችና ከሕዝብ ውስጥ የማስወገድ ሒደት በሥልጡንነት እየተወያዩና እየተከራከሩ ለችግሮች ቅን መፍትሔ የመፈለግ ብቃት፣ እንዲሁም ለቡድን አዘንብለው የቆዩ የመንግሥት ተቋማትን እንዳያገረሽባቸው አድርጎ ወደ ገለልተኝነት የማምጣት ሥራ፣ ጊዜ የሚወስዱና የሁሉንም ወገን መተባበር የሚጠይቁ ናቸውና ከሁሉ በፊት ይህን ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎቹ አጢነውና የጋራ ስምምነት ፈጥረው ለተልዕኮው አንድ ላይ መሠለፍ ግድ ይላቸዋል፡፡ ፓርቲዎች እዚህ ወሳኝ ተግባር ላይ ከተገናኙና  አቅማቸውን  ማስተባበር ከቻሉ ለአገሪቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት፣ ለሕዝቦቿ ሕይወት መቃናት፣ ለኢሕአዴግና ለተቃዋሚዎቹ ፍሬያማ አስተዋጽኦ እጅግ አስፈላጊ የማዕዘን ድንጋይ ተቀመጠ ማለት ነው፡፡

ይህ ከተሟላ ፓርቲዎች በእርስ በርስ የመሰራረግ ተንኮል ሳይጠቃቁ፣ በመከባበርና በቅንነት እየተወያዩና እየተራረሙ ለችግሮች መፍትሔ ለመፈለግና ለመቀባበል ይችላሉ፡፡ በውጭም ሆነ በጫካ ውስጥ ያሉ በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ መሳተፍ የሚሹ ኃይሎችን ማሰባሰብ ቀላል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከመንግሥት የቃል መግለጫ ይበልጥ ራሱ የሕጋዊ መድረኩ ሆደ ሰፊነት በጠመንጃ ጎዳና ውስጥ ያሉትን ወደ ሰላም የመጥራት ጉልበት ስለሚኖረው ነው፡፡ “የዴሞክራሲ ግንባታና መስፋፋት ማዕከል” ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት የሚችለውም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከሚኒስትርነት የወረዱ ሹሞችን አዝሎ ሲፈጠር ሳይሆን፣ የፓርቲዎችን የጋራ ተልዕኮ ተቆናጦ ሁሉንም ፓርቲዎችና የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችን አካትቶ እስከ ታች ድረስ ከሕዝብ ጋር የሚሠሩ ቅርንጫፎች ሲኖሩት ነው፡፡

እየተጠቃለለ በመጣው ዓለም ውስጥ መልካም ኑሮን በልማት ለመጨበጥ ከሚካሄድ አገር ዘለል የመሰባሰብ ጉዞ ጋር የሚያጣጥመንና ፍሬያማ ለመሆን የሚያበቃን ምን ዓይነት አገራዊ አደረጃጀትና አዕምሮ ነው? ብሔረሰባዊ ልዩ ልዩ ማንነቶችንና ኅብረ ብሔራዊ የጋራ ማንነትን እንዴት ማጣጣም ይቻላል? በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ የፖለቲካ መጣመምና መበረዝ ሳይደርስበት እንደምን ይደራጅ? ማኅበረሰቦች ባለቤትና መጤ ተባብለው የማይላተሙበት፣ አንዱ ወገን አሽቆጥቋጭ ሌላው ተሽቆጥቁጦ አዳሪ የማይሆኑበት እኩል የዜግነት ግንኙነት እንዴት ይበጅ? ማኅበረሰቦችን ከማኅበረሰቦች የሚያዛንቀውን የዕድገትና የመጠቃለል ጉዞ ተቃርነን ዜጎችን በየብሔረሰባዊ ምድራቸው እንዘርዝርና ጥንቅራቸው እንዳይቀየጥ እንጠብቅ? ወይስ ከዕድገትና ከመጠቃለል ጋር የማያላትም ሌላ መፍትሔ አለን? የፌዴራል አባላቱ የአስተዳደር ይዞታዎች ምድር መቃረጪያና መናጪያ ከመሆንስ እንዴት መላቀቅ ይችላሉ? ለአንድ ብሔረሰብ እታገላለሁ የሚል ብሔርተኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በሚወክል ሥልጣን ላይ መቀመጥ ይገባዋል? እንዲቀመጥ ተፈቅዶለት ለብሔረሰቡ ሲያደላ ቢገኝ ጥፋተኛው እሱ ሊሆን ነው? የፖለቲካ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ወደ ብረት ትግል እንዳይሻገሩና አገሪቱ ዳግም የጠመንጃ ሜዳ እንዳትሆን የሚጠብቃት ምንድነው? አገርና ሕገ መንግሥት በመጠበቅ ሽፋን ከሚካሄድ ጭፍጨፋ ሕዝቦች መጠበቅ የሚችሉት እንደምን ነው? “የኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት”፣ “የደርግ ሕገ መንግሥት” እና “የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት” የሚሉት ታሪክ ተዘግቶ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀጥተኛ የእኛ ባይነት የታተመበት የሕገ መንግሥትና የሰንደቅ ዓላማ ምዕራፍ ውስጥ እንዴት ይገባ? … እነዚህን የመሳሰሉትን የአገሪቱን ብዙ ጉዳዮች ያለ ስሜታዊ መታወርና ያለጥድፊያ የመመርመርና የማብላላት ሥራ ከላይ የተገለጸውን ዓይነት ከፀብ የወጣ ሽግግራዊ ሒደት ይፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ ለአገሪቱ የፖለቲካ ሰላምና ግስጋሴ የፓርቲዎች ተከባብሮ መኖር አስፈላጊነቱ ተጢኖ መጠማመድ ከተወገደ፣ በሕዝብ ምርጫ ውጤት መሠረት ከሥልጣን መውረድ የሞት አፍንጫን ማሽተት ተደርጎ አያስፈራም፡፡ ወደ ሥልጣን የሚወጣውም ወራጁን በመበቀል ፍላጎት አይጠመድም፡፡ ኢትዮጵያን ማተራመስ የሚሹ የውጭ ኃይሎችም የተቃዋሚ ታኮ ማግኘት ይቸግራቸዋል፡፡

ኢሕአዴግና የዛሬ ተቃዋሚዎቹ የኢትዮጵያን ሕዝቦች እዚህ ምዕራፍ ላይ ለማድረስ ተጋግዘው መሥራት ከቻሉ፣ በአዲሲቱ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ማንም የማያነቃንቀው የስም ሐውልት ያቆማሉ፡፡ ልብ እንበል! ኢትዮጵያን ለመበታተንና ከእሳት ጋር ለማገናኘት በጎረቤት “ጠላቶች” ጉርሻ መገዛትን ወይም የአሮጌዎቹ ኦነግና ሻዕቢያ ደቀ መዝሙር መሆንን አይጠይቅም፡፡ በታኞችንና የትርምስ ኃይሎችን እንታገላለን እያሉ ከሕዝብ እውነተኛ የድምፅ ፈቃድ ውጪ የአንድ ቡድን በሥልጣን ላይ መማዘዝም እዚያ ውጤት ላይ ያደርሳል፡፡ በኢሕአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎቹ ውስጥ ያሉ የሕዝብ ተቆርቋሪዎች ይህ እንዲሆን ከፈቀዱ ታሪካቸውን የሚጽፍላቸው ፍምና ነበልባል ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...