Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውዥንብር የፈጠረው የቀረጥ ነፃ መመርያ

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ታኅሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. አወጣ የተባለውና ለመንገደኞች የቀረጥ ነፃ መብት የሚሰጠው መመርያ ያልታሰበ ነበር ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሹልክ ብሎ ዱብ ያለ የሚመስለው ይህ መመርያ፣ እውነት መሆኑን ለማመን ብዥታ ውስጥ  ገብተው ከነበሩት አንዱ ነኝ፡፡ ግን ትክክል መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ መመርያው እንዲተገበር ከተፈለገበት ምክንያቶች አንዱ ‹‹ላልረባ ቀረጥ›› የመንገደኞችን ሻንጣ እየበረበሩ ላለመጉላላት የሚለው ነጥብ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ የረባና ያልረባ ቀረጥ ብሎ ነገር ያለ ባይመስለኝም ስለመመርያው መውጣት በተገቢው መንገድ ሳንሰማ ከመመርያው ጋር ተያይዞ ተፈጠረ ስለተባለው ቀውስ ጎልቶ ሰማን፡፡ ‹‹ላልረባ ቀረጥ›› የምትለዋን ቃል የሰማሁት አንድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ በዚህ መመርያ ዙሪያ ስለተፈጠረው ችግርና መመርያው የወጣበትን ምክንያት በቴሌቪዥን ሲገልጹ ነው፡፡ መንገደኞች በመመርያው የተገለጸ ውስን ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት ዕድል የሚሰጥና በፍተሻም እንዳይንገላቱ የሚያደርግ መመርያ ነው በሚለው እንስማማለን፡፡

ይህ ለመልካም ታስቦ ሥራ ላይ የዋለው መመርያ ከ33 በላይ በሚሆኑ በዋና ዋና ምርቶች ሥር የተጠቃለሉ የተለያዩ ዕቃዎችን ኢትዮጵያውያን መንገዶች ይዘው እንዲገቡ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ በአውሮፕላን ጣቢያው ሲደርሱ እነዚህን ከቀረጥ ነፃ የተፈቀዱ ዕቃዎች ያለችግር ማስገባት እንዲችሉ ይረዳል ማለት ነው፡፡ እንደ አነስተኛ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ጭምር ከቀረጥ ነፃ ማስገባት የሚያስችልም ነው፡፡

ጠቅለል ብሎ ሲታይ እንዲህ ያለውን ዕድል ይሰጣል ተብሎ የታመነበት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መመርያ፣ ሥራ ላይ በዋለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን አሠራሩን በአግባቡ ከመተግበር ተያይዞ ወይም መመርያውን ባልተገባ መንገድ ለመጠቀም በተደረገ ሙከራ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን ለማለት የሚያስደፍረው በመመርያው መሠረት በዕድሉ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉ መንገደኞች ገና ከአሁኑ መንግሥት የሰጠንን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም አልቻልንም የሚል እሮሮ እያሰሙ ነው፡፡ በመመርያው መሠረት እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላትም መናበብ አልቻሉም የሚለውን እምነት እንድንይዝ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጣቸውም ቢሆን ጉራማይሌ እየሆነ ለአንዱ የተሰጠ ዕድል ለሌላው ሲነፈግ እየታየ መሆኑም መነገሩ እምነታችንን ያጠናክራል፡፡  

ከአገራችን የአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ሲታይ ችግሩ ይህ ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕድሎችን በአግባቡ ከማስፈጸምና ሊፈጠር ከሚችለው ችግር ባሻገር፣ አጋጣሚውን በጠቀም መመርያውን ከታሰበለት ዓላማ ውጪ አጣሞ የመጠቀም ወይም ለመጠቀም መሞከር ለመንገደኞች ተሰጠ የተባለውን ከቀረጥ ነፃ ዕድል አጠቃቀም ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ ማድረጉም ሌላው ችግር እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡

መመርያውን በጥሞና ተረድቶ አገልግሎቱን በአግባቡና ወጥ በሆነ መንገድ ካለመስጠት ጋር ሊከሰት የሚችለው ጉድለት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ‹‹ይቺ ዕድል ከተገኘችማ›› ብሎ በአጋጣሚው ለመጠቀም የሚደረግ ሩጫ መመርያውን ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ሊገፋው እንደሚችል መገመት አያቅትም፡፡

ምክንያቱም ከዚህም ቀደም በተደጋጋሚ ከተመለከትናቸው እውነታዎች ለበጎ ተብሎ የተሰጡ ተመሳሳይ ከቀረጥ ነፃ ዕድሎችን ያለአግባብ መጠቀም ያስከተላቸውን ቀውሶች ማስታወሱ በቂ ነው፡፡

ከቀረጥ ነፃ የተሰጡ ዕድሎችን ትልልቅ የምንላቸው ኩባንያዎች ሳይቀሩ ምን ያህል እንዳወናበዱት እናስታውሳለን፡፡ ከቀረጥ ነፃ ዕቃዎችን እንዲያስገቡና እነሱ ብቻ እንዲጠቀሙበት ዕድል የተሰጣቸው ግለሰቦችም ሆኑ ኩባንያዎች፣ ከቀረጥ ነፃ ያስገቡትን ዕቃ አየር በአየር ‹‹ጆሮውን›› ማለታቸው የአንድ ሰሞን ጉዳይ ሆኖ ብቻ ያበቃ አይደለም፡፡ ዛሬም እየተፈጸመ ላለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

በሌላ ጊዜ ደግሞ ዳያስፖራዎች ወደ አገር ሲመጡ ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪ ያስገቡ ተብሎ የተሰጠውን ዕድን ስንቱ እንዳዛባውና በዚህ መመርያ መሠረት ተሽከርካሪዎቹን አስገብተው ‹‹‹የቸበቸቡ›› ወይም ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ሲነቃና ለሦስተኛ ወገን ተላለፉ የተባሉን ተሽከርካሪዎች ‹‹በቁጥጥር ሥር ለማዋል›› የጠፋውን ጊዜና የባከነው ገንዘብ የሚረሳ አይደለም፡፡

አሁንም የሰሞኑ መመርያ እንዲህ ያለ ዕጣ አይገጥመውም አይባልም፡፡ ፍንጮች እየታዩም ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትክክል መመርያውን በአግባቡ ለመጠቀም የሚፈለገውን እየጎዳና አሠራሩንም እየደበላለቀ ለጭቅጭቅ መዳረጉን እነሆ መስማት መጀመራችን ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡  

እንዲህ ያሉ መመርያዎችን በአግባቡ ከመተግበር ጋር ለሚፈጠሩ ግድፈቶች  እንደ ትልቅ ምክንያት ሊቆጠር የሚችለው ዓብይ ጉዳይ ግን ስለመመርያዎቹ ጥርት ያለ መረጃ ኅብረተሰቡ እንዲኖረው አለማድረግ ነው፡፡ ዕድሉን መጠቀም የሚችሉት እነ ማን ናቸው? ምን ምን ዕቃዎችን ማስገባት ይቻላል? ቀረጥ ሊቀረጥ የማይችለው ምን ሲሆን ነው? የሚሉ ዝርዝር ጉዳዮች ተብራርተው አልተገለጹም፡፡ ስለመመርያው መውጣትም እኮ የተሰማው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መረጃው እንዲኖረው ባስቻለ መንገድ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ከመመርያው ይልቅ መመርያውን ለማስፈጸም በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ተፈጠረ የተባለውን ችግር በይበልጥ የሰማነው፡፡

መመርያውን የሚያስፈጽሙ አካላትም ቢሆኑ እንዴት ሊያስፈጽሙ እንደሚገባቸው በግልጽ የተብራራ ያለመሆንም ሌላው ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ከመረጃ አሰጣጥ ጋር መንገደኞች በቂ ግንዛቤ ከሌላቸው ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ መመርያው ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ አየር መንገዶች ለመንገደኞቻቸው ከሚፈቅዱት የሻንጣ መጠን ወይም ክብደት በላይ የሆነ ዕቃ ከያዙ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከቀረጥ ነፃ መብት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ይደረጋል የሚል ነገር የመጣውም፣ ስለመመርያው ጥርት ያለ መረጃ አለመስጠት ወይም እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ ብሎ መፍትሔውንም በአግባቡ ካለማስቀመጥ ነው፡፡

ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥና በቶሎ ውሳኔ የሚሰጥ አስፈጻሚም በቦታው ሊኖር ይገባል፡፡ ካልሆነ በትክክል የዕድሉ ተጠቃሚ የሆነውንና አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለትርፍ ወገቡን ሸብ አድርጎ የሚመጣውንም ለመለየት ያስቸግራል፡፡ ሰሞኑን በዚህ ጉዳይ እየተሰማ ያለው ጫጫታም እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በትክክል ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ካለማድረግ ጋር የተያያዘ ነው ሊባል ይችላል፡፡

መመርያው ስለመውጣቱ በቂ መረጃ ሳይሰጥ መመርያው የገጠመውን ችግርና እሰጥ አገባ መስማታችን ራሱ የአልግሎት አሰጣጣችንን ደካማ ጎን የሚያሳብቅ ይሆናል፡፡ ከቀደሙ ልምዶች ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አሠራር ካለመዘርጋት ጋር የተቆራኘም ነው፡፡ አሁንም ሻንጣ አስፈትሹ አታስፈትሹ፣ ይህንን ዕቃ ያለቀረጥ ማስገባት መብቴ ነው መብትህ አይደለም የሚለውን ውዝግብ ለማስቀረት መመርያው ጥርት ባለመንገድ ይገለጽ፡፡ አንዴ ዕድሉን ያገኙ ተጠቃሚዎች በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ዕቃዎችን በማምጣት ያልተገባ ተግባር እንዳይፈጽሙ በአውሮፕላን ጣቢያው የደንበኞች የመረጃ ቋት ቢኖር፣ መመርያው በአግባቡ እንዲተገበር ያግዛል፡፡

መንገደኞች እንዳይወነባበዱ በቀላሉ ከቀረጥ ነፃ የሚፈቀዱ ምርቶች እነዚህ ናቸው ብሎ በሚዲያ ማስታወቁስ፣ ችግሩን ሊያቃልለው እንደሚችል ማሰቡም ቢሆን ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት