Friday, April 19, 2024

30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔና የአኅጉሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኝነት ማጣት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት፣ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመው በ1955 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ነው፡፡ ድርጅቱ ለመጀመርያ ጊዜ የተቋቋመው በ32 የአፍሪካ አገሮች ነው፡፡ ኅብረቱ ደቡብ አፍሪካ አባል እስከሆነችበት እ.ኤ.አ 1994 ድረስ 53 አገሮችን በአባልነት የያዘ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት 55 አገሮችን ያቀፈ አኅጉራዊ ድርጅት ቢሆንም፣ ከእነዚህ መካከል በኅብረቱ ንቁ ተሳትፎ የሌላቸው አገሮች ይገኙበታል፡፡

በአንደኛውም ሆነ በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸው ከነበሩ አኅጉሮች መካከል የአፍሪካ አኅጉር በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ኮሎኒያሊስቶች ከአፍሪካ ምድር የሰውን ልጅ በባርነት ስም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ከማጋዝ ባሻገር፣ የአኅጉሪቱን ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ሀብቶች መዝረፋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ የአፍሪካ አገሮች ባደረጉት ትግል እ.ኤ.አ. ከ1960 ጀምሮ ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት መጀመራቸው ይታወሳል፡፡ የአገሮችን ነፃ መውጣት ተከትሎ የተቋቋመው የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል፣ የአኅጉሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት፣ የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ግንኙነቶች ማጠናከር፣ ሰላምና ፀጥታን ማረጋገጥ፣ ዓለም አቀፍ ችግሮችን በኅብረት መቋቋም፣ የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ የአኅጉሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበር፣ ቅኝ ግዛትን ከአፍሪካ ማስወገድ፣ በአገሮች መካከል የሚፈጠረውን የድንበርና ሌሎች ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተሰሚነት ያለው መሆን፣ የሰው ልጆች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግ፣ ወዘተ የሚሉትና ሌሎች ይገኙበታል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ከተቋቋመ ወዲህ አባል አገሮች በሚኒስትሮች ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ፣ በመሪዎች ደረጃ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡

አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ከቅኝ ግዛት ነፃ ብትወጣም አሁንም ድረስ በድህነት፣ በኋላቀርነት፣ በስደት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ዕጦት ተተብትባ የምትገኝ አኅጉር እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በዓመት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞትና ለስደት እንደሚዳረጉ ‹‹አርምድ ኮንፍሊክት ሎኬሽን ኤንድ ኢቨንት ዳታ ፕሮጀክት›› የተሰኘው ተቋም እ.ኤ.አ. በ2016 ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡ አኅጉሩ የአሸባሪዎች መናኸሪያ ከመሆኑ ባሻገር፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ችግሮች ሳቢያ በርካታ ንፁኃን ዜጎች ለስቃይና ለመከራ እንደሚዳረጉ ተቋሙ ይፋ አድርጓል፡፡ ተቋሙ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በዓመት በፖለቲካ ልዩነት የተነሳ መሪዎች በሚወስዱት ዕርምጃ ብቻ በኤርትራ 29 ሺሕ፣  በደቡብ ሱዳን 20 ሺሕ፣ በሶማሊያ 18 ሺሕ እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 16 ሺሕ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አብዛኛዎቹ አፍሪካውያን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው መጣሳቸውን የሚያሳይ መሆኑን ተቋሙ ጠቁሟል፡፡

ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘም አኅጉሪቷን ለቀው ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚሄዱ ዜጎች ቁጥር በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ መረጃው አመልክቷል፡፡

በአፍሪካ እየከሰተ ላለው ችግር ዋነኛው ምክንያት የመሪዎች በሙስና መዘፈቅና የሥልጣን ጥም እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ አብዛኛዎቹ መሪዎች በትግል እንደመጡና ሥልጣናቸውንም በትግል ካልሆነ በስተቀር መልቀቅ እንደማይፈልጉ ተንታኞቹ አስረድተዋል፡፡

ታዋቂው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአፍሪካ ለሚታየው ቀውስ ምክንያቱ መሪዎች ናቸው፡፡ መሪዎች ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ገለልተኛ ምርጫ ባለማካሄድ ሥልጣን ላይ መቆየት፣ የዴሞክራሲ መርሆዎችን ተግባራዊ አለማድረግ፣ በሥልጣናቸው ለመቆየት ሲሉ ለዴሞክራሲ ግንባታ የሚታገሉ ወገኖችን ሕይወት ከማጥፋት በተጨማሪ እንዲሰደዱ ማድረግ የመሪዎቹ ዋነኛ መገለጫዎች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አፍሪካ አሁን ላለችበት ችግርና ቀውስ መነሻው መሪዎች እንደሆኑ አውስተዋል፡፡ የሕግ የበላይነትን በማክበር ለዴሞክራሲና ለፍትሕ የሚሠራ መሪ ባለመኖሩ (ያሉት ጥቂት ናቸው) ምክንያት፣ የአኅጉሪቱ ሕዝቦች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ችግሮች ተተብትበው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በአፍሪካ የሚታዩ ሁለንተናዊ ችግሮች የመፍቻ ቁልፍ ያለው በመሪዎች እጅ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ልዑልሰገድ፣ መሪዎች በተናጠልም ሆነ በክልላዊ ቀጣናዎች እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ሆነው ችግሮችን እንፈታለን የሚሉ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ የተለመደ እንደሆነና ሲፈቱ ግን እንደማይታይ ገልጸዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች የአኅጉሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት ሰላሳ መደበኛ ጉባዔዎችን እንዳካሄዱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በ2009 ዓ.ም. በሰኔ ወር በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው መደበኛ ጉባዔ፣ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት በጉባዔው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካን በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረፁትን አጀንዳዎችና ሌሎች ተግባራት ዕውን ለማድረግ መሪዎች ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል ብለው ነበር፡፡ አጀንዳ 2063 የዘላቂ የልማት ግቦች፣ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረፁ ፕሮግራሞችና ሌሎች አጀንዳዎች ዕውን እንዲሆኑ መሪዎች ቁርጠኛ ሆነው መሥራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ሊቀመንበሩ በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲመጣና ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ እንዲቻል መሪዎች የዘወትር የቤት ሥራቸው አድርገው እንዲሠሩ ማሳሰባቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ መሪዎች በ29ኛው ጉባዔ የተቀረፁትን አጀንዳዎች ተግባራዊ ለማድረግና የአኅጉሪቱን ሁለንተናዊ ችግር ለመፍታት ውሳኔ ላይ ደርሰውም ነበር፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ይህ የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ተሰብስቦ ከማውራትና ተገናኝቶ ከመጫወት የተለየ ትርጉም የለውም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ለአኅጉሪቷ ተቆርቋሪ በመሆን እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ካለመቻላቸውም በላይ፣ የኅብረቱን የፋይናንስ አቅም በአባል አገሮቹ መሸፈን እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ የኅብረቱን ወጪ እንኳን መሸፈን ያልቻለ አኅጉር፣ ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሚና ይኖረዋል ብለው እንደማይገምቱም ተናግረዋል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹30ኛውን ጉባዔ ሲያካሂዱ የኅብረቱን የፋይናንስ ችግር መቅረፍም ይመለከታል፡፡ አሁንም ኅብረቱ ራሱን ችሎ የቆመ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የአፍሪካ መሪዎች አብዛኛዎቹ የዴሞክራሲ መርሆዎችን የማይከተሉ፣ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የራሳቸውን ፍላጎት የሚያራምዱና በብዙ ችግሮች የተተበተቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አሁን የሚያደርጉት ጉባዔም ዓመቱ ሲመጣ ስብሰባ ልሄድ ነው ከማለት ውጪ የሚያሳዩት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ አቶ ልዑልሰገድ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ እ.ኤ.አ. በ2007 በአዲስ አበባ የተረቀቀውንና የአፍሪካ ዴሞክራሲ፣ ገቨርናንስና የምርጫ ቻርተር የተሰኘውን ሰነድ እስካሁን ድረስ 30 የአፍሪካ አገሮች ብቻ ማፅደቃቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይህን ቻርተር ተቀብለው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያልገቡ አገሮች እንዳሉ ጠቁመው፣ ይህ የሚያሳየው ደግሞ መሪዎች ምን ያህል ለራሳቸው ብቻ የሚያስቡ እንደሆነና ለዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥ የሚሠሩ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ አብዛኛዎቹ መሪዎች ሥልጣን የሚያዘው በአመፅ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ልዑልሰገድ፣ መሪዎች ሕገ መንግሥቱን እየጣሱ የራሳቸውን ፍላጎት የሚያራምዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መሪዎች አጀንዳ 2063 ተግባራዊ ለማድረግ በልበ ሙሉነት አለመንቀሳቀስና የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያንሳቸው ገልጸዋል፡፡

30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚካሄደው ‹‹በአፍሪካ የሙስና ትግል በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ›› በሚል መሪ ቃል ሲሆን፣ የመሪዎች ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት 32ኛው የሚኒስትሮች ጉባዔ ከሐሙስ ጥር 17 ቀን ጀምሮ በኅብረቱ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ የኅብረቱ ሊቀመንበር የሚኒስትሮችን ጉባዔ ሲከፍቱ እንደተናገሩት፣ ሙስናን ለመታገል የኅብረቱ አገሮች መሪዎች ቁርጠኝነታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ ነው፡፡ ኮሚሽነሩ እንደተናገሩት እ.ኤ.አ. በ2017 በተደረገ ጥናት በአፍሪካ በግለሰቦች ደረጃ ብቻ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ይዘዋወራል፡፡

ኮሚሽነሩ ሌላው የጠቀሱት ጉዳይ ሽብርተኝነትን የተመለከተ ነው፡፡ አኅጉሪቱ በሽብርተኝነት የተነሳ በዓመት በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎቿን ታጣለች፡፡ ይህን ለመከላከልና የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ለማረጋገጥ፣ በጉባዔው ወቅት መሪዎች ቁርጠኝነታቸውን ያሳያሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በአምስት ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ አጀንዳዎችም የኅብረቱ ስብሰባዎች በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ወሳኝ በሆኑ የአኅጉሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለሚዳስሱ ጥቂት ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት አቅሙን እንዲያጠናክርና አመራር እንዲሰጥ፣ የኅብረቱን አሠራር ማሻሻል፣ ዜጎችን በኅብረቱ መወከል፣ በኅብረቱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊነትና አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችና ጉድለቶችን ማስተካከልና የኅብረቱን የገንዘብ አቅም ማጎልበት የሚሉ እንደሆኑ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

የፋይናንስ ነፃነት ሳይኖር ነፃ መሆን እንደማይቻል የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ፣ የአፍሪካ መሪዎች ራሳቸውን በቅድሚያ ከሙስና የፀዳ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በአኅጉሪቱ የተንሰራፋው ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ሙስና፣ የዴሞክራሲ ዕጦትና ሌሎች ችግሮች መወገድ የሚችሉት የመሪዎች ቁርጠኝነትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲኖር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መሪዎቹ ራዕይ ያላቸው፣ አገራቸውን ጠቅመው ለአኅጉራቸው የሚተጉ ሊሆኑ እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ በበኩላቸው አፍሪካን ከችግሮች መታደግ የሚቻለው ለለውጥ የሚተጋ መሪ ሲኖር እንደሆነ ጠቅሰው፣ የኅብረቱ ቻርተሮች ማለትም የምርጫ፣ የዴሞክራሲና ሌሎች ጉዳዮች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት ራሱ ኅብረቱ ጠንካራ ሲሆን ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ወጣቱን በፖለቲካና በኢኮኖሚ ቀጥተኛ ተሳታፊ ማድረግ አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

29ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት ሙሳ ፋቂ፣ ‹‹በአፍሪካ ለሚነሱ ግጭቶች የሌላ አኅጉር አገር ጣልቃ ሳይገባ ራሳችን መፍታት አለብን፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ በዋናነት በኤርትራና በጂቡቲ ድንበር አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ችግር በኅብረቱ መፈታት እንዳለበት አሳስበው ነበር፡፡

አቶ ልዑልሰገድ መሪዎች የገቡትን ቃል ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ጠቁመዋል፡፡ እንደማሳያ የጠቀሱት ጉዳይ ደግሞ በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የነበረው ውዝግብ በዘላቂነት አለመፈታቱን ነው፡፡

የኅብረቱ መሪዎች በየጊዜው እየተገናኙ የሚያደርጉት ስብሰባ ፍሬው እንደማይታይ፣ አሁንም ጉንጭን ከማልፋት የዘለለ ትርጉም ይኖረዋል ብለው እንደማያስቡ ፕሮፌሰር በየነ ተናግረዋል፡፡

በኅብረቱ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ተመሳሳይ ሰዎች እየመጡ ውሳኔ አስተላልፈው ከመሄድ የዘለለ ትርጉም እንደሌላቸው ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ 30ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ከሌሎች ጉባዔዎች ለየት የሚያደርገው በሁለት ጉዳዮች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሮበርት ሙጋቤ ከረዥም ጊዜ በኋላ በጉባዔው ላይ አለመሳተፋቸው፣ ሁለተኛው ደግሞ በላይቤሪያ ተካሂዶ በነበረው ምርጫ አሸናፊ የሆኑት የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋቹ ጆርጅ ዊሃ በጉባዔው ተሳታፊ በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም. በተካሄደው በ29ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተገኝተው የነበሩት የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ 300 ከብቶችን በመሸጥ ለአፍሪካ ኅብረት ፋውንዴሽን የሚውል የአንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገው ነበር፡፡ በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም፣ ‹‹አፍሪካ ራሷን ችላ በሁለት እግሯ መቆም አለባት፡፡ ለዚህም ነው ድርጅቴ በፈቀደው መጠን ይህንን ገንዘብ ያበረከትነው፤›› ሲሉ መናገራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ላይ በመገኘት ሳቢና አከራካሪ ንግግሮችን ያደርጉ የነበሩት የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ ሥልጣናቸውን በኃይል በመነጠቃቸው ምክንያት ከረዥም ዓመታት በኋላ በመሪዎች ጉባዔ ላይ ስለማይገኙ፣ በምትካቸው አዲሱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ይወክላሉ፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የሚገኙት መሪዎች የአፍሪካን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ እንዲሆኑ የሚያሳስቡ ወገኖች አሉ፡፡ ከተለመደውና ባህላዊ ከሆነው አሠራር ወጥቶ አኅጉሪቱን እየተፈታተኗት በሚገኙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መስጠት አለባቸው ይላሉ፡፡ መሪዎች አሁንም በተለመደው ሁኔታ ለሁለንታናዊ ችግሮችና ፈተናዎች እጅ በመስጠት ተመልካች በመሆን፣ የራሳቸውን ጥቅምና ሥልጣን ያሳድዳሉ? ወይስ ቁርጠኛ በመሆን የሕዝባቸውንና የአኅጉሪቱን ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የበለፀገች፣ የለማችና በሕዝቦቿ ዘንድ የምትወደድ አፍሪካን ለመመሥረት መሠረት ይጥላሉ? የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ምላሽ የሚሻ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -