መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት በማሰብ በውጭ አገር የሥራ ስምሪት ላይ ለዓመታት ጥሎት የነበረውን ዕገዳ ከጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲነሳ ወሰነ።
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዕገዳ ው እንዲነሳ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡ የሚታወቅ ሲሆን፣ ዕገዳው እንዲነሳ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዛሬ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. መወሰኑን የካቢኔ ጉዳዮች ሚንስትሩ አቶ አለማየው ተገኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል ።
ሳውዲ ዓረቢያ ከአራት ዓመታት በፊት በግዛቷ የሚገኙ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን በፀጥታ ኃይሎች እያስገደደች ባስወጣችበት ወቅት ነበር መንግሥት በውጭ አገር የስራ ስምሪት ላይ ዕገዳውን የጣለው።
በወቅቱ ከመቶ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ ዓረቢያ ተገደው የወጡ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን በብዛት ከሚገኙባቸው የዓረብ አገሮች ጋር የኢትዮጵያውያንን መብትና ደኅንነት ማስከበር የሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች እና የሠራተኛ ልውውጥን የተመለከቱ ስምምነቶች ወይም የሕግ ማዕቀፎች እስኪበጁ ነበር ዕገዳው የተጣለው። ይሁን እንጂ ዕገዳው ሕገወጥ ስደትን እንዳባባሰና በአሁኑ ወቅትም በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሳውዲ ዓረቢያን ለቀው እንዲወጡ በአገሪቱ መንግሥት ተወስኖባቸው ጥቂቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ አብዛኞቹ ግን በአሁኑ ወቅት ከሳውዲ መንግሥት ጋር ድብብቆሽ ውስጥ መሆናቸው ይነገራል።