መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና አገራዊ ስምምነት ለማምጣት በማለት፣ ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያሉና በተከሰሱበት ወንጀል የተፈረደባቸውን እንደሚለቅ በተናገረው መሠረት፣ ከአማራ ክልል በአጠቃላይ 2,905 ግለሰቦች እንዲለቀቁ ተወሰነ፡፡
ፈቃደ ሥልጣኑ የፌዴራል ሆኖ በክልል ማረሚያ ቤቶችና ማቆያ ቤቶች የሚገኙ ተከሳሾችና ፍርደኞች፣ በከባድ ሰው ግድያ ወንጀል፣ በከባድ አካል ማጉደል ወንጀል፣ ሕግ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመገርሰስ በተደረጉ የወንጀል እንቅስቃሴዎች ውስጥ አለመሳተፋቸው የተረጋገጠ ፍርደኞችና ተጠርጣሪ ተከሳሾች ክስ እንደሚቋረጥ የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በመሆኑም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሊቀመናብርቱ በተናገሩ ጥቂት ቀናት ውስጥ 2,345 እስረኞችን መልቀቁ የተነገረ ሲሆን፣ በፌዴራልና በደቡብ ክልል በድምሩ የ528 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡ ይታወሳል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም፣ ክሳቸው በፌዴራል ፈቃደ ሥልጣን ሥር ሆኖ በክልል ፍርድ ቤቶች በመታየት ላይ የነበሩ 598 ተጠርጣሪዎች ክስ እንዲቋረጥና 2,305 ፍርደኞች ደግሞ በምሕረት እንዲለቀቁ፣ ማክሰኞ ጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የክልሉ ምክር ቤት መወሰኑን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡
በፌዴራልና በክልል በቀጣይ ቀሪ ቀናት ክሳቸው የሚቋረጥና በምሕረት የሚለቀቁ እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡