Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ሰላምን ማደፍረስ መዘዙ የከፋ ነው!

  በአሁኑ ጊዜ በምክንያታዊነት ሳይሆን በስሜት በመነዳት አገርን ለማተራመስ፣ ሕዝብን ደግሞ የማይወጣበት ቀውስ ውስጥ ለመክተት ያለ መታከት የሚባዝኑ እየበዙ ነው፡፡ የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዙሪያውን አሰፍስፈው ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ነገ ይዞት ሊመጣ የሚችለውን ቀውስ አሸጋግረው ማየት የተሳናቸው የአገሪቱን አንፃራዊ ሰላም እያደፈረሱ ነው፡፡ ሰላምን ማደፍረስና ወደለየለት ግጭት ውስጥ መግባትን ከቁብ ባለመቁጠር፣ በገዛ እጅ ለመጥፋት የሚደረገው እሽቅድምድም ከጥፋት በስተቀር ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡ አገር እየመራ ያለው መንግሥት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ገጽታቸውን እያቀያየሩ የሚከሰቱ ግጭቶችን ማስቆም ባለመቻሉ፣ አሁንም ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት እንደ ቀልድ እየረገፈ ነው፡፡ በአንፃራዊነት ሰላም የነበሩ ሥፍራዎች የግጭት መናኸሪያ እየሆኑ ነው፡፡ ለሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች ቃል በተገባው መሠረት ምላሽ በመስጠት ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ቀጣይ ተግባራትን በአፋጣኝ ማከናወን ሲገባው፣ አሁንም ዘገምተኛ በሆነው አካሄዱ ምክንያት ሰላም የበለጠ እየደፈረሰ ነው፡፡ የአገርና የሕዝብ ህልውናም አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ መዘዙ የከፋ ነው፡፡

        የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት የግድ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ወይም የሚመራው መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች ተሳትፎ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ላጋጠሙ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሔ ሊገኝ የሚችለው፣ በብሔራዊ መግባባት መነጋገርና መደራደር ሲቻል ብቻ መሆኑን ማመን ይገባል፡፡ ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል የሚፈለገውን ርቀት በመጓዝ በሰጥቶ መቀበል መርህ መነጋገር የሚያስፈልገው፣ የአገር ህልውና ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚስተዋለው አሳዛኝ ጉድለት ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ማስተካከያ ሊደረግለት ይገባል፡፡ የዜጎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከመቼውም ጊዜ በላይ በተግባር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ፍትሕ በገንዘብ የሚሸቀጥ እንዳይሆን መተማመኛ ሊኖር ይገባል፡፡ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ሆነ የሥልጣን ክፍፍል ጉዳይ በአስተማማኝ ሁኔታ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አጋዥ የሆነው ምርጫ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲከናወን የሚረዱ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ወሳኝ መሆናቸውን ማስተማመኛ የሚሰጠው የሕግ የበላይነት ስለሆነ ትልቅ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ በእነዚህና በመሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ መነጋገርና መደራደር ሲቻል ሰላም ይሰፍናል፡፡ ግጭት ሥፍራ አይኖረውም፡፡

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያገረሸበት ግጭት ሰሞኑን በሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ ሥፍራዎች ብሶበት ነው የከረመው፡፡ አሁንም ሆነ ቀደም ሲል ብሔር ተኮር የሆኑ ግጭቶች በተለያዩ ሥፍራዎች መከሰታቸው ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቧ ፈተና እየጋረጡ ነው፡፡ የዜጎችን ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ሥጋት ውስጥ የከተቱት እነዚህ ግጭቶች፣ ለዓመታት በአንድ ሥፍራ ተደላድለው ይኖሩ የነበሩትንም ሥቃይ ውስጥ እየከተቱ ነው፡፡ በተለይ ሰዎችን በማንነታቸው እየለዩ ጥቃት የሚፈጽሙ ወገኖች በየቦታው ብቅ ጥልቅ ሲሉ መታየታቸው፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ህልውናና የሕዝቡን የዘመናት መስተጋብር አደጋ ውስጥ እየከተተ ነው፡፡ ሰላምን ማስከበር ባለመቻሉ ምክንያት የሰው ሕይወት አደጋ ውስጥ እየወደቀና የአገር ሀብት እየወደመ ምን ያህል ርቀት መጓዝ ይቻላል? ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሕዝቡ ለቀረቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ቃል ከገባ በኋላ በየቦታው ሁከት እየተፈጠረ ሕይወት ሲያልፍ ምን ማለት ነው? አገሪቱ የገባችበትን አጣብቂኝ በውል ተገንዝቦ ለመፍትሔ መፍጠን ይሻላል? ወይስ ችግሮቹ መጠናቸው እየጨመረና አድማሳቸውም እየሰፋ የበለጠ ጥፋት መጋበዝ? ሰላም እየደፈረሰ አገሪቱ የበለጠ ወደ አሳሳቢ የጥፋት ቀጣና ውስጥ ከመቀርቀሯ በፊት የመፍትሔ ያለህ ማለት ይበጃል፡፡

  ዘወትር እንደምንለው ሕዝብ ዘንድ ምንም ችግር የለም፡፡ ሕዝቡ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረውን አብሮነቱን አሁንም ቀጥሏል፡፡ ይህ እውነታ ግጭት በተከሰተባቸው ሥፍራዎች ሳይቀር ሕዝቡ እርስ በርስ ከለላ ሲሰጣጥና ሲደጋገፍ በተግባር ታይቷል፡፡ አሁን ዋናው ችግር ያለው ፖለቲከኞችና በፖለቲካው ዙሪያ የተኮለኮሉ ኃይሎች ዘንድ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ ችግር ኢሕአዴግን ጨምሮ በተቃውሞ ጎራ ያሉትን በሙሉ የሚመለከት ሲሆን፣ ራሳቸውን በፖለቲካ አቀንቃኝነት (Activism) ላይ ያሰማሩ የትርፍ ሰዓት ሰዎችን ይመለከታል፡፡ ኢሕአዴግ ሌላው ቀርቶ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶችን ማክበር ባለመቻሉ ያለፉት ሁለት ዓመታት ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ከዚያ ወዲህ እንኳ በተለያዩ መንገዶች ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም፣ አሁንም ከግጭት አዙሪት መውጣት አልተቻለም፡፡ ከሚቃወሙት ጋር ያለበት ሽኩቻ እንዳለ ሆኖ፣ በውስጡ የተፈጠረው አለመተማመን አገሪቷንና ሕዝቡን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ አሁንም የጠራ ነገር ባለመኖሩ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በተደጋጋሚ እየታዩ ነው፡፡  ሥርዓቱ ውስጥ ሆነው ግጭት የሚቀሰቅሱና አገሪቱን ለውድመት የሚያዘጋጁ ኃይሎች ጭምር አደጋ ጋርጠዋል፡፡ ምንድነው እየተጠበቀ ያለው? ሕዝብ ምላሽ ይፈልጋል፡፡

  በሌላው ጎራ የተሠለፉ ኃይሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግጭቶችን በማጦዝ ላይ ናቸው፡፡ አርቀው የሚያስቡና የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ የሚያሳስባቸው ወገኖች ካልሆኑ በስተቀር፣ በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉት እሳቱን የበለጠ ለማቀጣጠል እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ፡፡ በዚህ መሀል ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት ይረግፋል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅሙ የፖሊሲ ሰነዶችን ይዞ የነገዋን አገር ከማሰብ ይልቅ፣ ጠላቴ እንደምንም ይውደቅ እንጂ ሌላውን እደርስበታለሁ በሚል ግብዝነት የአገርን ህልውና ችግር ውስጥ ይከታሉ፡፡ ይቃወመናል ወይም አይደግፈንም ብለው የሚያስቡትን በጅምላ ማብጠልጠልና ለአገር የማይጠቅም ጽንፈኛ አቋም ብቻ በማራመድ የፖለቲካ ጨዋታ ሕጎችን ይደፈጥጣሉ፡፡ ኢሕአዴግ የሚወቀስበትን ተቃዋሚን የመጥላትና የማግለል አካሄድን በመከተል እነሱም ያንኑ ስህተት ይደግማሉ፡፡ ተቃውሞን መስማት አይፈልጉም፡፡ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ መልስ አይሰጡም፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ ፍትሐዊነትና የመሳሰሉትን በኩር ሐሳቦች እየተጋፉ ስለራሳቸው የበላይነት ብቻ እየሰበኩ ወጣቶችን ይማግዳሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጮርቃነት ጭምር ነው የአገሪቱን ፖለቲካ ዳዋ ያለበሰው፡፡ ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡

  ኢትዮጵያም ሆነች ይህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ የሚያስፈልጋቸው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር ተቀምጦ መነጋገርና መደራደር ሲቻል ለሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል ምላሽ መስጠት ይቻላል፡፡ በመከባበርና በመርህ ላይ የተመሠረተ ሥልጡን ውይይትና ድርድር ሲኖር ለግጭትና ለትርምስ በር አይከፈትም፡፡ ኢትዮጵያን ለዘመናት ለማዳከም ሲያሴሩ የኖሩ ታሪካዊ ጠላቶችም ክፍተት አያገኙም፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን እንኳን ለመነጋገርና ለመደራደር በየተራ የጠላት ዒላማ መሆን ይከተላል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ውዥንብር ውስጥ ሆኖ ሥልጣን ላይ ተረጋግቶ መቀመጥ አይቻልም፡፡ ሥልጣንን በትርምስ መቆናጠጥም ዘበት ነው፡፡ በአጠቃላይ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡ ነገር ግን ሰከን ብሎ በማሰብ ሰላምም ሆነ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡ ይህንን መልካም አጋጣሚ ለግላዊና ለቡድናዊ ጥቅም አሳልፎ መስጠት በታሪክም ሆነ በትውልድ ዘንድ ያስጠይቃል፡፡ ሰላምን ማደፍረስ መዘዙ የከፋ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

  በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

  ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

  በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

  ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

  በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...

  ወጋገን ባንክ ከገጠመው ቀውስ በማገገም በ2014 የሒሳብ ዓመት የተሻለ ትርፍ አገኘ

  ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው ከተስተጓጎለባቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል ነው!

  በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው የሚጨፈጨፉበት ምክንያት ብዙዎችን ግራ ከማጋባት አልፎ፣ የአገርና የጠቅላላው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰበ ነው፡፡ መንግሥት...

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...