Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፃዊያን በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ውይይት ሊያደርጉ ነው

ግብፃዊያን በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ውይይት ሊያደርጉ ነው

ቀን:

ግብፃዊያን ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው፣ ይህንን አመለካከት ወደ አንድ ሐሳብ ለማምጣትና የጋራ አቋም ለመያዝ ውይይት ሊያደርጉ መሆኑ ታወቀ፡፡

30ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመካፈል የመጡና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የግብፅ ዲፕሎማት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ አብዛኛው የግብፅ ሕዝብ ጥያቄ ያነሳል፡፡ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስና ሁሉም ግብፃውያን የጋራ አቋም እንደሚኖራቸው ለማድረግ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ የአገሪቱ ሕዝብ ከመንግሥት አመራሮች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በግንባታው ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው የጠቆሙት ዲፕሎማቱ፣ ሕዝቡ ግን አሁንም ቅሬታ አለው ብለዋል፡፡ ‹‹በበረሃ ያለን ሕዝቦች በመሆናችን አንድ ቀን እንኳ የናይል ወንዝ መጠኑ ቢቀንስ ተጎጂዎች እንሆናለን፤›› በማለት ጥያቄ እንደሚያነሳ ጠቁመዋል፡፡ የግብፅን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ የአብዱልፈታህ አልሲሲ መንግሥት ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ዲፕሎማቱ፣ የውይይቱ አጀንዳና የሚጠበቀው ውጤት የኢትዮጵያን የመልማትና በተፈጠሮ ሀብቷ የመጠቀም መብት የሚጋፋ እንደማይሆን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በፊት የነበሩት የግብፅ መሪዎች ኢትዮጵያ የምትገነባውን የህዳሴ ግድብ እንደሚቃወሙና ኢትዮጵያ ግንባታውን የማታቆም ከሆነ የኃይል ዕርምጃ እንወስዳለን የሚል ዛቻ ሲያስተላልፉ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አብዱልፈታህ አልሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በአንፃራዊነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

ዲፕሎማቱ እንደገለጹት፣ የአሁኑ የግብፅ መንግሥት የህዳሴ ግድቡ ግንባታን በተመለከተ ያለውን ችግር ሁለቱ አገሮች በመግባባት ይፈታሉ የሚል እምነት አለ፡፡

በውይይቱ መጨረሻ ላይ የግብፅ ሕዝብ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ የሚቃወም ከሆነ ግብፅ ምን ዓይነት አቋም ሊኖራት ይችላል የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹መንግሥት ሕዝቡን ለማሳመን ይሞክራል፡፡ ግድቡ በእኛ ላይ ጉልህ ጉዳይ እንደማይኖረውና የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያመነጭ የሚኖረውን በጎ ተፅዕኖ ማየት ጥሩ እንደሆነ ገለጻ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

ዲፕሎማቱ ኤርትራን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ከኤርትራ ይልቅ ወዳጃችን ኢትዮጵያ ነች፤›› የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል፡፡ ዲፕሎማቱ ኤርትራን በተመለከተ ከዚህ በላይ ማብራሪያ ለመስጠት አልፈቀዱም፡፡

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የመሠረት ድንጋይ ከጣለች ሰባተኛ ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን፣ የግንባታ ሒደቱም ከ60 በመቶ በላይ መድረሱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖና የውኃውን አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ተቋም ቀጥረው ለማሠራት ስምምነት ላይ እንደደረሱ ቢታወቅም፣ አጥኚ ቡድኑ በሚሠራበት የመነሻ ሐሳብ ላይ ስምምነት አልደረሱም፡፡ በዋናነት ግብፅ እ.ኤ.አ. የ1959 የውኃ ስምምነት የዚህ ስምምነት አካል ይሁን የሚል ጥያቄ በማቅረቧ በኢትዮጵያ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ከድርድሩ ሱዳን እንድትወጣና በምትኩ የዓለም ባንክ እንዲያደራድራቸው ግብፅ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቧም የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንን ሐሳብም ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ቀርታለች፡፡

ግብፅና ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ላይ የሚያደርጉት ድርድር አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ወደ ግብፅ አቅንተው ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ውይይት ማድረጋቸው  አይዘነጋም፡፡

በተመሳሳይ በ30ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የግብፅ ፕሬዚዳንት፣ ሰኞ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ጋር በህዳሴ ግድቡ ላይ ተወያይተዋል፡፡  

ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ እንደ ሦስት ሳይሆን አንደ አንድ አገር ተስማምቶ ለመሥራት ከስምምነት ላይ እንደ ደረሱ ተገልጿል፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ በመሪዎች ደረጃ እየተገናኙ በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርና አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡

የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ፣ የውኃ ሀብትና ሌሎች የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች ሌሎች ተቋማት በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ በሚደረጉ ቀጣይ ውይይቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመሪዎች ሪፖርት እንዲያቀርቡ መመርያ መሰጠቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሦስቱ አገሮች መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል የሦስትዮሽ የመሠረተ ልማት ፈንድ ለማቋቋም መስማማታቸው ተገልጿል፡፡ ፈንዱም ሦስቱ አገሮች እኩል የሚያዋጡት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡   

ኢንዲፔንደንት የተሰኘው የግብፅ ሚዲያ ሰሞኑን እንደ ዘገበው ፕሬዚዳንት አልሲሲ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ምክንያት ወደ ግጭት አይገቡም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ ‹‹ለጋዜጠኞች ላረጋግጥላችሁ የምወደው በመካከላችን ግጭት የለም፡፡ ሁላችንም አንድ ነን፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ጉዳት አያደርስም፤›› ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ በበኩላቸው፣ አንደኛው አገር በሌላኛው አገር ላይ ጉዳት ላለማድረስ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ማለታቸው በዘገባው ተካቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...