የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ባላቸው አገልግሎቶች ላይ ባካሄደው ኦዲት፣ 1,439 ጉዳዮች የአሠራርና የመመርያ ጥሰት ያለባቸው መሆኑን ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡
የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት ያካሄዳቸውን ሥራዎች በገመገመበት ሪፖርት ላይ እንዳስታወቀው፣ በ2010 በጀት ዓመት በመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት 4,736 አገልግሎት አሰጣጦችን ኦዲት አድርጓል፡፡
ኦዲት ከተደረገባቸው አገልግሎቶች ውስጥ 1,344 የሚሆኑት የአሠራር ጥሰት፣ 95 የሚሆኑት ደግሞ የመመርያ ጥሰት ያለባቸው መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ቢሮው ባወጣው የስድስት ወራት ሪፖርት እንዳስታወቀው ከመመርያ ጥሰቶች መካከል ያላግባብ ክፍያ ማስከፈል፣ የመስክ ልኬት ሳይደረግ በጂአይኤስ ታይቶ ብቻ ካርታ አትሞ መስጠት፣ በባዶ መሬት የስም ዝውውር መፈጸም፣ በሽንሻኖ ከፀደቀው ካሬ ሜትር በላይ ካርታ አዘጋጅቶ መስጠት፣ ለየብቻቸው መልማት የማይችሉ ይዞታዎች በተነፃፃሪ (ፕሮፖርሽን) ከመሥራት ይልቅ ማካፈልን መምረጥ፣ እንዲሁም ከምትክ ቦታ አሰጣጥ ጋር ያሉ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ሆነው ቀርበዋል፡፡
ቢሮው እንዳለው በማዕከልና በክፍለ ከተማ ደረጃ በአሠራርና በመመርያ ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉ አካላት ላይ ዕርምጃ መውሰዱንም አስታውቋል፡፡ በተወሰደው ዕርምጃ ሦስት አመራሮች ከኃላፊነት እንዲነሱ፣ ስድስት ባለሙያዎች ከሥራ እንዲሰናበቱ፣ 100 ሠራተኞች ደግሞ በአስተዳደራዊ ዕርምጃ በጽሑፍና በደመወዝ ተቀጥተዋል፡፡
የመሬት ዘርፍ በአገር አቀፍ ደረጃ የሙስና መፈልፈያና ዋነኛ ተጋላጭ ቦታ ነው ተብሎ መፈረጁ ይታወሳል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ መርህ መነሻ ላለፉት አሥር ዓመታት የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮን በማያቋርጥ መዋቅር ለውጥ ውስጥ ቢያሳልፈውምና በርካታ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ ቢወስድም፣ የሙስና ምልክቶች አሁንም መታየታቸውን ቀጥለዋል፡፡
አስተዳደሩ በ2009 ዓ.ም. የመጨረሻዎቹ ስድስት ወራት 600 ከሚሆኑ አመራሮች ሠራተኞች ላይ እስከማባረር የደረሰ ዕርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡