Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሙዚቃ ለሰላም

ሙዚቃ ለሰላም

ቀን:

‹‹ሚውዚክ ፎር ፒስ›› (ሙዚቃ ለሰላም) የተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት የተካሄደው የአፍሪካን አርቲስትስ ፒስ ኢንሽዬቲቭ (ኤኤፒአይ) ፎረምን ተከትሎ ነበር፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ አርቲስቶችና የመብት ተሟጋቾች ስብስብ የሆነው ኤኤፒአይ፣ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን አስታኮ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

የውይይቱ ቀዳሚ ትኩረት ሙስናን በመዋጋት ረገድ አፍሪካውያን አርቲስቶች ምን ሚና አላቸው? የሚለው ነበር፡፡ በውይይቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ድምፃውያን፣ ገጣሚዎች፣ ዲዛይነሮች፣ ፊልም ሠሪዎችና ሌሎችም የጥበብ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የተጀመረው ውይይት የተገባደደው ጥር 19 በተካሄደው የሙዚቃ ኮንሰርት ነው፡፡

ኮንሰርቱ ‹‹ሙዚቃ ለሰላም›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ድምፃውያንን በማሳተፍ ነበር፡፡ በአህጉሪቱ ያሉና ሥራዎቻቸው በሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና ፍትሕ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አርቲስቶች የኤኤፒአይ አባል ናቸው፡፡ በመላው ዓለም ወደ 15,000 የሚጠጉ አባላት ያሉ ሲሆን፣ 90 ታዋቂ አርቲስቶች በሰላም በአምባሳደርነት ተሹመዋል፡፡ በኮንሰርቱ ሙዚቃቸውን ያቀረቡት ስድስት አርቲስቶችም ከአምባሳደሮቹ መካከል ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

30ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ፣ ‹‹ዘላቂ የፀረ ሙስና ዘመቻ ለአፍሪካ ሥር ነቀል ለውጥ›› (ዊኒንግ ዘ ፋይት አጌንስት ኮራብሽን፣ ኤ ሰስቴነብል ፓዝ ቱ አፍሪካስ ትራንስፎርሜሽን) በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ሙስናን በመዋጋት ዙሪያ ካደረጉት ውይይት ጎን ለጎን፣ ኤኤፒአይ ‹‹ቢውልዲንግ ኦን አክሽን ፋክተሪ ፎር አንቲ ኮራብሽን ኢን አፍሪካ›› የሚል ፎረም አካሂዷል፡፡

ለማኅበራዊ ችግሮች መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ የአርቲስቶች ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ‹‹ሙዚቃ ለሰላም›› ኮንሰርትም ይኼንን ታሳቢ በማድረግ፣ በአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በሙዚቃ መልዕክት ማስተላለፍን ግቡ አድርጓል፡፡

በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንዜስ በተካሄደው ኮንሰርት በሰላም አምባሳደርነት የሚሠሩት ፀደንያ ገብረማርቆስ፣ ሲዲኒ ሰሎሞን፣ ክሪቲካል (ከኬንያ)፣ የቨስ ካሚግዌ (ከቡሩንዲ)፣ ጊላድ ሚሎ (ከኬንያ) እና ሔኖክ መሐሪ ሙዚቃ አቅርበዋል፡፡ ሙዚቀኞቹ ስለ ሰላምና ፍቅር የሚሰብኩ ሥራዎቻቸውን ሲያቀርቡ፣ የተሻለ አፍሪካ ለመፍጠር ሙስና መወገድ እንዳለበት በማሳሰብ ነበር፡፡

ኮንሰርቱ የተጀመረው በሔኖክና መሐሪ ብራዘርስ ነበር፡፡ ከሁሉም ነገር ፍቅር እንደሚበልጥና በዘር፣ በጎሳ በሃይማኖት መከፋፈል ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጹ ዘፈኖች አስደምጠዋል፡፡ ሔኖክን በአህጉራዊው የሙዚቃ ውድድር አፍሪማ (ኦል አፍሪካ ሚውዚክ አዋርድስ) ተሸላሚ ያደረገው ‹‹እወድሻለሁ›› የተሰኘው ዘፈንም በሬጌ ስልት ቀርቧል፡፡

ኮንሰርቱ ስለ ሰላም ለመስበክ እንደመዘጋጀቱ፣ በእያንዳንዱ ሙዚቃ መካከል አፍሪካን ሰላማዊ አህጉር ለማድረግ አርቲስቶች ስላላቸው ሚና ተገልጿል፡፡ አፍሪካን ከሙስናና ሌሎችም የዕድገት መሰናክሎች የፀዳች ማድረግ የአህጉሪቱ መሪዎች እንዲሁም የሕዝቦችም ኃላፊነት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ስለ ሙስናና ሌሎችም ማኅበራዊ ችግሮች በተለያየ መንገድ መግለጽ ይቻላል፡፡ ከእነዚህ መንገዶች ጥበብ አንዱ ሲሆን፣ መልዕክትን በማስተላለፍ ረገድ ውጤታማ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ማኅበረሰቡ በጥበባዊ ሥራዎች የሚቀርበውን መቀበልም ይመርጣል፡፡ ይኼንን ከግምት በማስገባት ‹‹ሲኒማ ፎር ፒስ›› (ሲኒማ ለሰላም) የሚል መርሐ ግብር በኤኤፒአይ ፎረም ተካቷል፡፡ ከሙዚቃ በተጨማሪ ፊልምን በመጠቀም ማኅበረሰባዊ መልዕክት የተላለፈበት ነበር፡፡

በ‹‹ሲኒማ ለሰላም›› ከናይጄሪያ ‹‹93 ደይስ››፣ ከታንዛኒያና እንግሊዝ ‹‹አይ ሻት ቢ ኪዱዴ›› እና ከጋምቢያ ‹‹ዌልካምቱ ዘ ስማይሊንግ ኮስት›› የተሰኙት ፊልሞች ታይተዋል፡፡

በኮንሰርቱ ሙዚቃ ካቀረቡበት አንዷ የሆነችው ፀደንያ ገብረማርቆስ ከራሷ ዘፈኖች በተጨማሪ የቦብ ማርሌን ‹‹ኖ ውመን ኖ ክራይ›› አቀንቅናለች፡፡ ከታዳሚው ሞቅ ያለ ድጋፍም ተሰጥቷታል፡፡

ኬንያውያኑ ክሪቲካልና ጊላድ ሚሎ በሬጌ ስልት የሰላም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ጊንድ የእንግሊዝኛ ስዋሒሊ ውህድ በሆኑ ሙዚቃዎች አፍሪካውያን በአንድነት እንዲቆሙ ጠይቋል፡፡

የብሩንዲው የቭስ ካሚክዌ ሙዚቃውን ካስደመጠ በኋላ የደቡብ ሱዳን ገጣሚዎች መድረኩን ተረከቡ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት እያደረሰ ያለው ጥፋት በግጥሞቻቸው ተስተጋብቷል፡፡ በአፍሪካ አገሮች የተንሰራፋው ሙስና ካልተቀረፈ ዕድገት እንደማይኖር በገጣሚዎቹ ሥራዎች ተደምጧል፡፡

የኮንሰርቱ መደምደሚያ የሲድኒና ኢምፔሪያል ማጅስቲክ ባንድ ነበሩ፡፡ በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ጣልያኖችን ድል መንሳታቸው የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆኑን የሚገልጸው ‹‹ሳንጃው ሰው በላ›› ዘፈንን ጨምሮ በርካታ ዜማዎች አቅርበዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ሲካኤድ ውይይቱ የሚካሄደው በመሪዎች መካከል ነው፡፡ በአንፃሩ አርቲስቶች በውይይቱ የሚነሱ ነጥቦች ሕዝብ እንዲደርሱ ለማድረግ ይጣጣራሉ፡፡ በተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎች ማኅበራዊ ለውጥ የሚያመጣ መልዕክትም ያስተላልፋሉ፡፡ መሰል የውይይት መድረኮች የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን ተከትለው በየዓመቱ አዲስ አበባ ውስጥ ይካሄዳሉ፡፡ አርቲስቶችም በሙዚቃ፣ በሥነ ጥበብ፣ በሥነ ጽሑፍና ሌሎችንም የጥበብ ውጤቶች ሐሳባቸውን ለሕዝቡ ያደርሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...