Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የወርቅ ኢዮቤልዩ ላይ የደረሰው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት

ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የተመሠረተው በ1960 ዓ.ም. ሲሆን፣ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩውን ከጥር 3 ቀን እስከ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. አክብሯል፡፡ በክብረ በዓሉ ትምህርት ቤቱ በሙዚቃ ዘርፍ ስላበረከተው አስተዋፅኦ፣ ስለገጠሙት ተግዳሮቶችና የወደፊት እቅዶቹ ውይይት ተደርጓል፡፡ በትምህርት ቤቱ የ50 ዓመት ጉዞ ዙሪያ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ኃላፊና የቫዮሊን መምህርት ሰላማዊት አራጋውን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ቤቱ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ምን ይመስል ነበር?

መምህርት ሰላማዊት፡- የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት 50ኛ ዓመት በተለያዩ ፕሮግራሞች ለሦስት ቀናት ተከብሯል፡፡ ጥር 3 ቀን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት የመምህራንና የቀድሞ ተማሪዎች ኮንሰርት ተካሂዷል፡፡ ከወጣት እስከ አንጋፋ መምህራንና ለረዥም ዓመታት በኮንሰርት ያልተሳተፉ ነበሩ፡፡ ጥሩ ሙዚቀኞች የሚባሉና ሰው ሊያያቸው የሚፈልግ አክሊሉ ዘውዴ፣ ኃይሉ ዓለማየሁና ዓለማየሁ ፈንታን የመሳሰሉ መምህራን አቅርበዋል፡፡ በፕሮግራሙ የቀድሞ ምሩቃን፣ ከትምህርት ቤቱ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ኤምባሲዎች አምባሳደሮችና በክብር እንግድነት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያም፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና አካዳሚክ ፕሬዚዳንት ተገኝተዋል፡፡ ጥር 4 ቀን የትምህርት ቤቱን የ50 ዓመት ጉዞ በተመለከተ እንዲሁም በአጠቃላይ የሙዚቃ ትምህርት በኢትዮጵያ ምን ይመስላል? ምን መሻሻል አለበት? ምን ችግሮች አጋጠሙት? የሚለውን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡ እንዳሰብነው ሰው ባይገኝም የሚመለከታቸው የሙዚቃ መምህራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ በቀጣይ የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ምሩቃን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሚያቀርቡት የሙዚቃ ኮንሰርት ይኖራል፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ ኮንሰርቱ አዘጋጅተን ገቢውን ለትምህርት ቤቱ ለማዋል አስበናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ባለፉት 50 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ አበርክቷል ብላችሁ በውይይቱ ያነሳችኋቸውን ነጥቦች ብትገልጭልን?

መምህርት ሰላማዊት፡- ትምህርት ቤቱ በ50 ዓመት ውስጥ ብዙ ሠርቷል፡፡ ማበርከት የነበረበትን ያህል አላበረከትም የሚሉ አንዳንድ አስተያየቶች አሉ፡፡ ሙዚቃ ትምህር ቤት ባለፉት ዓመታት ስንት ተማሪ አበርክቷል? ምን ተግዳሮቶችስ ነበሩት? የሚለውንም መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ፣ የዛሬ 50 ዓመትና እስከ ቅርብ ዓመት የነበረው ለሙያው የሚሰጠው ዓምት አለ፡፡ ሙዚቃ እንደ ትምህርት ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶታል? የሚለው አሁንም አነጋጋሪ ነው፡፡ ካለው የባለሙያ እጥረት አንፃርና ከሙዚቃ መሣሪያ ውድነት አንፃር ትምህርቱ ውድ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ እያለ ትምህርት ቤቱ እስከ ቅርብ ዓመት ድረስ በየዓመቱ 25 ተማሪዎችን ያስመርቃል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከሙዚቃ አስተማሪነት ጀምሮ በምርምር፣ ሙዚቃ በማቅረብ (ፐርፎርማንስ)፣ በሙዚቃ ፕሮዳክሽን ወይም በሪክርዲንግ በመሳተፍና ገበያ ላይ ያለውን (ኮሜርሽያል) ሙዚቃ በመሥራት ብዙ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው፡፡ ትምህር ቤቱ በ50 ዓመት ውስጥ ወደ 1,200 ተማሪ አስመርቋል፡፡ ለምን? ሲባል፣ የባለሙያና የቦታ እጥረት አለ፡፡ የሙዚቃ ትምህርት ጊዜ፣ ቦታና ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ ይጠይቃል፡፡ ትምህርት ቤቱ የተቻለውን እያበረከተ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ያሉትን ፍላጎቶች ከግምት በማስገባት የተለያዩ ለውጦች እያደረገ ነው፡፡ ከትምህርት ክፍል አንፃር ብዙ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የስትሪንግ፣ የብራስ፣ የፒያኖና የጃዝ ክፍል አለ፡፡ በቅርቡ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች እንደ ጊታር፣ ቤዝ ጊታርና ድራም ያሉትን ማሰልጠን ጀምሯል፡፡ የኛ ተማሪዎች ሪከርዲንግ ወይም የሙዚቃ ፕሮዳክሽን የሚሠሩት ካላቸው እውቀት በተጨማሪ ቴክኖሎጂውን በራሳቸው ተምረው ነበር፡፡ አሁን ግን ከአውሮፓ ሕብረት ባገኘነው ለሦስት ዓመት የሚቆይ የገንዘብ ድጋፍ ስቱዲዮ እንገነባለን፡፡ ስቱዲዮው ፕሮፌሽናል ነው የሚሆነው፡፡ ይኼንን በሥርዓተ ትምህርት አካተን ተማሪዎች በትምህርት የተደገፈ እውቀት ይዘው እንዲወጡ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በ50 ዓመት ጉዞው የገጠሙ ተግዳሮቶችስ?

መምህርት ሰላማዊት፡- አንደኛው፣ የሥርዓተ ትምህርት ጉዳይ ነው፡፡ የኛ ተማሪዎች ሙዚቃ መማር የሚጀምሩት ከዜሮ ነው፡፡ በዚህ አገር ሥርዓት ትምህርት ሙዚቃ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ሙዚቃ እስከሆነ ክፍል ቢማሩም ሙዚቃ ተብለው የሚማሩት ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ ምን ያህል ውጤታማ ያደርጋቸዋል? ስንቶቹ የሙዚቃ መሣሪያ ይማራሉ? ለሙዚቃ ትኩረት ሰጥቶ እንደ አንድ ትምህርት በመስጠት በኩል በሥርዓተ ትምህርቱ ችግር አለ፡፡ ሁለተኛው፣ የሙዚቃ ትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሲመጣ ልጆቹ በአምስት ዓመት የሚገባቸውን እውቀት ይዘው እንዲወጡ ይደረግ ነበር፡፡ አሁን ግን የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ (ሞጁላር ሲስተም) ሲመጣ አምስት ዓመቱ ወደ አራት ዓመት ተቀነሰ፡፡ ትምህርት ቤቱ በ50 ዓመት ልምዱ ሥርዓት ትምህርት በተደጋጋሚ እየሠራን እያፈረስን መጥተናል፡፡ በሌላ በኩል የሙዚቃ ትምህርት ክፍል የከፈቱ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ የሚያስተምሩት ከኛ ትምህርት ቤት የወጡ ልጆች ናቸው፡፡ የተወሰኑት ዩኒቨርሲቲዎች አራት ዓመት ሌሎቹ አምስት ዓመት እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ያለ ትምህርት ቤቱ ፍላጎት ትምህርቱ ወደ አራት ዓመት መጥቷል፡፡ ምንም ብንከራከር ወደ አምስት ዓመት መመለስ አልተቻለም፡፡ ከዚህ በፊት አራት ዓመት ማስተማር ተሞክሮ አልሠራም፡፡ በቂ አይደለም፡፡ ልጆቹ ልክ ሙዚቃ ሲበራላቸው ይወጣሉ፡፡ አንድ ዓመት በጣም ዋጋ አለው፡፡ ወደ በፊቱ መመለስ ከትምህርት ቤቱ አቅም በላይ ቢሆንም በተደጋጋሚ እየጠየቀን ነው፡፡ ወደ አምስት ዓመት እንደሚመለስ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሦስተኛው፣ በኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ላይ ብዙ ትኩረት አይሰጥም የሚል ነገር አለ፡፡ እውነት ነው፡፡ እንደሚፈለገው ያህል ባይሰጥም ትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ ትቶታል ማለት አይደለም፡፡ አንድ መሣሪያ በስፔሻላይዜሽን ወይም እንደ ሜጀር ሲሰጥ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንድን ተማሪ አምስት ዓመት ሙሉ አንድ የባህል መሣሪያ ስናስተምር፣ መጀመርያ በሙዚቃ መሣሪያው መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በሥርዓተ ትምህርት ደረጃ በትክክል ተቀርፆ መቀመጥ ያለበት ነገር አለ፡፡ ይኼ ከተሟላ በኋላ በባህላዊ መሣሪያዎች በደንብ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሲባል ባህላዊ ሙዚቃ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ተማሪዎቻችን የቡድን (ግሩፕ ፐርፎርማንስ) ክፍሎች አሏቸው፡፡ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ የሆነ ነገር ጽፈው እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡ በባህላዊ ሙዚቃ በግልና በቡድንም የሚማሩት አለ፡፡ መሻሻል እንዳለበት እናምናለን፡፡ ክፍሉ አሁን በአዲስ መልኩ ተጠናክሮ እየሠራ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ትምህርት ቤቱ ለኢትዮጰያ ባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ በቂ ትኩረት አልሰጠም የሚለው ነገር ከሙዚቀኞችና ከተማሪዎችም በተደጋጋሚ የሚሰነዘር ትችት ነው፡፡ ትምህር ቤቱ ይኼንን ለማሻሻል ምን አድርጓል?

መምህርት ሰላማዊት፡- ትምህርቱን ለማስቀጠል በቂ መምህራን ያስፈልጋሉ፡፡ አሁን በተወሰነ መልኩ የባህላዊ መሣሪያ መምህራን አሉን፡፡ በዕቅድ የያዝነው በቡድን የሚማሩ ተማሪዎችን ቁጥር ቀንሶ ማስተማር ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ በሚቀጥለው ዓመት የሚከፍተው የድህረ ምረቃ መርሐ ግብር ዋነኛ ትኩረቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ነው፡፡ በብዛት የጥናትና ምርምር ጽሑፎች እንዲመጡ ያደርጋል፡፡ የአገሪቱ ሙዚቃ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሲሆን ዕድገት ያመጣል፡፡ የባህል ሙዚቃ እንዳያድግ አድርጓል ብዬ የማምነው የድህረ ምረቃ መርሐ ግብር አለመኖሩን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃና የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ እንደ ፐርፎርማንስ ይሰጣል፡፡ ያሬዳዊ ዝማሬና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክም ተካተዋል፡፡ ተማሪዎች በቅድመ ምረቃ ደረጃ ይዘውት የወጡትን የፐርፎርማንስ ደረጃ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ እንዲያተኩሩ እናደርጋለን፡፡ ብዙ የጥናት ወረቀቶች ሲወጡ ለችግሩ መፍትሔ ይሰጣሉ ብዬም አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ብቻውን ለአገሪቱ በቂ አይደለም የሚል አስተያየት በሚሰነዘርበት ወቅት፣ አዳዲስ በተከፈቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሙዚቃ ትምህርት መሰጠት ተጀምሯል፡፡ ሆኖም አንጋፋው ትምህርት ቤት ራሱ የመምህራንና የሙዚቃ መሣሪያ እጥረትና ሌሎችም ችግሮች እየተፈታተኑት፣ አዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ምን ያህል ብቁ ተማሪዎች ሊያፈሩ ይችላሉ?

መምህርት ሰላማዊት፡- መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የ50 ዓመት ዕድሜ ያለውና የሦስትና አራት ዓመት ዕድሜ ያለው ሰው እኩል ሊራመዱ አይችሉም፡፡ የሙዚቃ ትምህርት ልምድ ይፈልጋል፡፡ በሙዚቃ አስተማሪነት አምስት ዓመት ከተጫወተው 10፣ 15፣ 20፣ ዓመት የተጫወተው የተሻለ ነው፡፡ የውጭ አገሮች የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ፕሮፌሰሮች ምናልባትም በዱላ የሚሄዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ሙዚቃ እንደሌላው ሙያ 60 እና 70 ዓመት ሆነ ተብሎ ጡረታ የሚወጣበት አይደለም፡፡ በተቆየ ቁጥር የተሻለ ነገር መሥራት ይቻላል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቹ ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ቢችሉም የተሻለ ነገር የሚመጣው ችግሮቹ ሲታለፉ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ብዙ ልምድ ስላለው ከትምህርት ቤቱ ጋር እየተመካከሩ ቢሠሩ የተሻለ ይሆናል፡፡ የሙዚቃ ትምህርት በምደባ የሚሆን አይደለም፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የመደባቸውን ሁሉ ተቀብሎ ለማሠልጠን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እኛ ጋር ያለው ጥሩ ነገር ተማሪዎችን ትምህርት ሚኒስቴር በፐርፎርሚንግና ቪዥዋል አርትስ ትምህርት ክፍል ሲመድብልን እንፈትናቸዋለን፡፡ ያሬድ ከዛሬ 50 ዓመት ጀምሮ የሚያደርገው የተማሪ ቅበላ ሒደት ነው፡፡ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በፊት ትምህርት ሚኒስቴር የላከላቸውን በሙሉ ይወስዱ ነበር፡፡ አሁን እንደኛ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የላከውን በሙሉ መቀበል አንደኛ ተማሪው ፍላጎቱ ከሌለው፣ ፍላጎት ቢኖር እንኳን ችሎታ ከሌለው፣ የተማሪውንና የመምህሩንም ጊዜ ማባከን ነው፡፡ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ያለበት ቦታ የተመቸ ሲሆን፣ አንዳንድ ክፍለ አገር የተከፈቱ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ አስቸጋሪ ነገር እንደሚገጥማቸው አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በሒደትና ከሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ጋር በጋራ በመሥራት ችግሮቹ የሚፈቱ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቃን ጨምሮ ሥነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍን የመሰሉ ሙያ ትምህርት ክፍሎች እንደ ሌሎች ትምህርቶች በመንግሥት በቂ ትኩረት አልተሰጣቸውም የሚሉ አሉ፡፡ ይኼ ምን ያህል ተፅዕኖ አሳድሮባችኋል?

መምህርት ሰላማዊት፡- ሙያውን ካለማወቅና ካለመረዳት የሚመጡ ነገሮች አሉ፡፡ የሙዚቃ፣ የሕክምናና የአካውንቲንግ ትምህርት የሚጠይቁት ነገር አለ፡፡ ሙዚቃ ችሎታና ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ሙዚቃን ከመዝናኛ ባለፈ ያለማየት ነገር አለ፡፡ ዋና (ሜጀር ኢንስትሩመንት) ትምህርት የሚሰጠው በግል እንጂ በጋራ ሊሆን አይችሉም፡፡ ለዚህ መምህራኖች ያስፈልጋሉ ስንል የሚረዳን የለም፡፡ በአዲሱ ሕንፃችን፣ አንድ የማጥኛ ክፍል ቢበዛ ለሦስት ተማሪ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ ቀኑን ሙሉ ከፍል ይውላሉ፡፡ ከዛ ማታ ያጠናሉ፡፡ አሁን እንደውም ማደሪያቸውም ከኤፍቢ ወደዚህ ስለዞረ ለማጥናት ምቹ ነው፡፡ ሕንፃው ሲታይ ትልቅ ቢሆንም ካሉን ተማሪዎች አንፃርና አሁን ካለን የመርሐ ግብር ማስፋፋትና የተማሪ ቁጥር መጨመር ዕቅድ አንፃር በቂ አይደለም፡፡ አሁን ያለን የተማሪ ቁጥር (የአምስተኛ ዓመት ተማሪዎችን ጨምሮ) ወደ 180 አካባቢ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ሕንፃ ምን ያደርግላችኋል? የሚል ነገር አለ፡፡ አንድ ክፍል ለሦስት ተማሪ እንጠቀማለን ስንል እንደ ቅንጦት ይታያል፡፡ ያለመረዳት ችግር አለ፡፡ በዚህ ላይ የመሣሪያ ግዢ ስንጠይቅ በጣም ችግር ይገጥመናል፡፡ እኛ የምንጠይቀው በተማሪ ደረጃ ያለ የሙዚቃ መሣሪያ ቢሆንም የሙዚቃ መሣሪያ ባጠቃላይ ውድ ነው፡፡ በጀት ስንጠይቅ በጀቱን የመቀነስ ነገር አለ፡፡ ይኼ ሁሉ ምን ያደረጋል? ይባላል፡፡

ሪፖርተር፡- በዋነኛነት እንቅፋት የሆነውን የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ በተመለከተ፣ ትምህርት ቤቱ ችግሩን ለመቅረፍ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል?

መምህርት ሰላማዊት፡- የተቻለንን ያህል ተዋግተናል፡፡ እኔም የሥርዓተ ትምህርት ኮሜቴ ውስጥ ነበርኩ፡፡ መቐለና ጂማ ዩኒቨርሲቲ አራት ዓመት እንዲሆን ፈለጉ፡፡ ያሬድና ወሎ ዩኒቨርሲቲ አምስት ዓመት በሚለው ፀናን፡፡ በስተመጨረሻ አጣጥሙ (ሐርመናይዝ አድርጉ) ተባለ፡፡ ማጣጣሙን የማልደግፍበት የራሴ ምክንያት አለ፡፡ ማጣጣም የሚቻለው ወይም አንድ ዓይነት ሥርዓተ ትምህርት የመስጠት ሐሳቡ ጥሩ ቢሆንም የሰው ኃይልና መሣሪያ ከግምት መግባት አለበት፡፡ ያሬድ ማስተማር የሚችለውን በሙሉ አዲስ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር አይችልም፡፡ ልዩነቶቹን ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ በሒደት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ገና ካልተከፈተ ትምህርት ክፍል ጋር ማጣጣም አያስኬድም፡፡ አንደኛው ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ስለሌለኝ ይኼንን ትምህርት መስጠት አልችልም ካለ ሌሎቹም ትምህርቱን ይቀንሳሉ ማለት ነው፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም፡፡ እኛ በልዩነት በአምስት ዓመት ቀጥለን ሁለት ባች ከተቀበልን በኋላ (አሁን የሚጨርሱና አምና የጨረሱትን) ምንም ሳያማክሩን አራት ዓመት ይሁን የሚል የውሳኔ ሐሳብ ተነበበልን፡፡ ለውጥ ይኖራል ብለን ማብራሪያ ጽፈን ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔ ነው ተባልን፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር ያስደነግጣል፡፡ የትምህርት ጥራት ብለን ካሰብን ለውጡ የሚያመጣውን ችግር ስንናገር መሰማት ነበረብን፡፡ አሁንም ችግሮቹን በተጨባጭ እናስቀምጣለን፡፡ የሚመለከታቸው አካላት ሰምተው ምላሽ እንደሚሰጡን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የአራት ዓመት ምሩቃን ከታዩ በኋላ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ማድረግ ይቻላል፡፡ ግን መጠነኛ ለውጥ ነው፡፡ ለባህላዊ ሙዚቃ ትምህርት በቂ ትኩረት ካልተሰጠበት ምክንያት አንዱ ትምህርቱ ከአምስት ዓመት ወደ አራት ዓመት መቀነሱ ነው፡፡ በሙዚቃ ትምህርት የምናስተምረው የሙዚቃ መሣሪያ ብቻ አይደለም፡፡ አንድን ሙዚቀኛ ሙሉ ሙዚቀኛ እንዲሆን የሚያደርጉ የሐርመኒ፣ ሶልፌጆ፣ የሙዚቃ ንድፈ ሐሳብና ብዙ ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ አንዱ ቢጎድል አንድ ተማሪ ሙሉ ሆኖ አይወጣም፡፡ በተለይ ተግባራዊ በሆኑ ትምህርቶች በመቆየት ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ አራት ዓመት ከሆነም ብለን በተቻለ መጠን ልጆቹ ጥሩ ነገር ይዘው እንዲወጡ በሚል ሥርዓተ ትምህርቱ ተቀርጿል፡፡ ቢሆንም የአንድ ዓመት ጭማሪውን እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ያሬድ እንደ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ቀዳሚ ሥራው ተማሪዎችን ማፍራት ቢሆንም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፍ ምን ያህል ተሳትፎ ያደርጋል? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ ለምሳሌ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ልኬት (ስታንዳርድ) የማጣት ችግርን በመቅረፍ ረገድ ትምህርት ቤቱ የድርሻውን መወጣት ነበረበት የሚሉ አሉ፡፡  ትምህርት ቤቱ በሙዚቃው ዘርፍ ያለው አጠቃላይ ተሳትፎ ምን ይመስላል?

መምህርት ሰላማዊት፡- የመጀመሪያና ትልቁ ኃላፊነት ማስተማር ነው፡፡ የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀሉት የኛ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ዓላማችን የመድረክ መሣሪያ ተጫዋቾች (ፐርፎርመርስ) ማስመረቅ፣ የመዚቃ መምህራን ማውጣትና በጥናት ዘርፍና የተለያዩ የሙዚቃ መርሐ ግብሮችን የሚያስተባብሩ ማፍራት ነው፡፡ ከዛ ባለፈ ግን በሙዚቃ ኢንዱስትሪው መሳተፍ አለበት፡፡ ከሙዚቀኞች ማኅበራት ጋር በጋራ የመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ ከኮፒራይት ጋር በተያያዘም መሳተፍ እንዳለበት እናምናለን፡፡ ትምህርት ቤቱ በተሳታፊነት አብሮ ለመሥራት ፍቃደኛ ነው፡፡ በእቅድ ደረጃ የያዝናቸውም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ የኮፒራይት ጉዳይ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ እነዚህን በመሰሉ ጉዳዮች በተጨባጭ ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች ብትነግሪን?

መምህርት ሰላማዊት፡- ከሙዚቃ ማኅበራት ጋር መደበኛ ያልሆነ ውይይት ነበረን፡፡ እነሱም በቀጣይ ስብሰባዎች ይኖሯቸዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ በቀጥታ ተሳትፎ የሚያደርግበትን ነገር ለመለየት በዕቅድ ላይ ነን፡፡ በማንኛውም ነገር መርዳት እንፈልጋለን፡፡ ቀጥተኛ ኃላፊነትም ተሳትፎም ሊኖረው የሚገባው ሙዚቃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ እዛ ያሉት ከሙዚቃ ትምህርት ቤቱ የወጡና ያልወጡም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሙያው ግን አንድ ያደርገናል፡፡ ዞሮ ዞሮ እየሠራን ያለነው ሙያውን ለማስከበር ነው፡፡ አንድ መደበኛ ስብሰባቸውን ሙዚቃ ትምህርት ቤት የማድረግ ዕቅድ ነበራቸው፡፡ ካለን የአዳራሽ ጥበት አንፃር ወደሌላ ቦታ ቢዘዋወርም በአንዳንድ ምክንያት አልተካሄደም፡፡ ባህልን በማስተዋወቅ ደረጃ ትምህርት ቤታችንን ወክለው ተማሪዎችና እኔን ጨምሮ ሌሎች መምህራንም በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡ ሙዚቃ ትምህርት ቤቱና አገርን ወክለን ለባህል ልውውጥ ወደተለያዩ አገሮች ሔደናል፡፡ የአገርን ገጽታ ከመገንባት አንፃር ትልቅ ነገር ነው፡፡ እንደ ቀዳሚ የሙዚቃ ትምህርት ቤትነቱ በሙዚቃ አገርን ከማስተዋወቅ አንፃር ከደቡብ ኮርያ፣ ከጀርመን የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ጋር የባህል ልውውጥ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ የአዲስ አበባ እህት ከተማ በሆነችው ላይፍሊሽ ከተማ ወደሚገኝ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎቻችንን እንልካለን፡፡ እነሱም ይመጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የመዚቃ ዘርፉን አቅጣጫ የሚያመላክት ፖሊሲ ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑ ባለሙያዎች፣ ትምህርት ቤቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው ይገልጻሉ፡፡ የፖሊሲ መኖር፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች ከውጭ ሲገቡ ያለውን ቀረጥ በመቀነስና ለሌሎችም ችግሮች መፍትሔ ይሆናል ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ በእናንተ በኩል የተሠሩ ሥራዎች አሉ?

መምህርት ሰላማዊት፡- ፖሊሲን በተመለከተ በኛ ትምህርት ቤት በኩል የሚቀርቡ ብዙ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ፖሊስ ሲረቀቅ መጠየቅ ያለበት ማን ነው? በቀጥታ የሚመለከተው ማነው? ሙዚቃን ወክሎ፣ የሙዚቃ አቅጣጫ ይኼ ነው ብሎ ማሳየት ያለበት ማነው? አንዳንዴ ግራ ያጋባል፡፡ እኛ ሳናውቀው ፖሊሲዎች ተቀርፀው እናያለን፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርበናል፡፡ የባህል፣ የፊልም፣ የሙዚቃ ፖሊሲ ለመቅረጽ ባለሙያ እንፈልጋለን የሚል ደብዳቤ ይመጣል፡፡ ይወክላል የምንለውን ሰው ካላወቅን በኋላ ጥሪ አይደረግም፡፡ ጉዳዩ ምን እንደደረሰ አይታወቅም፡፡ ነገሮች ወረቀት ላይ ሰፍረው እናገኛለን፡፡ ይኼ መሆን የለበትም፡፡ ፖሊሲ የሚያዘጋጀው አካል የሚመለከተው ሰው ማነው? የሚለውን ማሰብ አለበት፡፡ እኛ በተቻለን ለመሳተፍ እንሞክራለን፡፡ ዕድሉን ግን አላገኘንም፡፡ አንዳንዴ ለሙዚቃ ፖሊሲ የሚያወጣው ስለ ሙዚቃ የማይመለከተው ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ያሉት፣ በተለይ አንጋፋ መምህራን ምን መደረግ እንዳለበት መጠየቅ አለባቸው፡፡ የግድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ሰው ባይሆንም በሙዚቃ ሽያጭና በሌላም የሚሳተፉ ሙዚቃ ምን እንደሚያስፈልገው በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት መጋበዝ አለባቸው፡፡ ይኼንን ዕድል ያለማግኘት እንጂ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ቸል ብሎ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ ርቀት የያዛችኋቸው ዕቅዶች ምንድን ናቸው?

መምህርት ሰላማዊት፡- የሪከርዲንግ ስቱዲዮው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ትልቅ የሰው ኃይል ይጠይቃል፡፡ ለድኅረ ምረቃ መርሐ ግብሩ የመምህራን ቁጥር መጨመር ሌላው ነገር ነው፡፡ ትምህርቱን በአግባቡ የሚሰጡ መምህርና ኤክስፐርቶች ያስፈልጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ አተኩረንም በተሻለ መልኩ እንሠራለን፡፡ በሐሜት ደረጃ ምንም አልተሠራም የሚለውን ሙሉ በሙሉ እቃወማለሁ፡፡ ምክንያቱም ከዛሬ 50 ዓመት በተወሰነ መልኩ የዛሬ 30 ዓመትና ከዛ በኋላም እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በተሻለ መልኩ የመሥራት እቅድም አለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...