በሳዑዲ ዓረቢያ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን የሚመራው የፀረ ሙስና ኮሚቴ ከሁለት ወራት በፊት በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው ባለሀብቶችና ልዑላን ቤተሰቦች መካከል የተወሰኑትን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለቋል፡፡
በባለወርቃማው ባለአምስት ኮከቡ ሪትዝ ካርልተን ሆቴል በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ቱጃሮች መካከል ከዚህ ቀደም 23 ያህሉ የተለቀቁ ሲሆን፣ የአብዛኞቹ ስም ግን አልተገለጸም ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ማብቂያ ተለቀዋል ከተባሉት መካከል ግን ቢሊየነሩ ልዑል አልዋሊድ ቢን ታላል እንደሚገኙበት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
አልጋ ወራሽ ሰልማን መሐመድ ቢን አልጋ ወራሽነቱን ከተቆናጠጡ ወዲህ፣ በሳዑዲ ንጉሥ ሰልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑዲ አነሳሽነት ሳዑዲ በየመን የእርስ በርስ ጦርነት ጣልቃ እንድትገባ አድርገዋል፡፡
ሳዑዲ እ.ኤ.አ. በ2030 ይኖረኛል ብላ ያስቀመጠችውን የዕድገት ዕቅድም ነድፈዋል፡፡ በነዳጅ ምርት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች ላይ በማተኮር ጤና፣ ትምህርት፣ መሠረተ ልማት፣ መዝናኛና ቱሪዝምን ለማበልፀግ ያለመው ዕቅዳቸውም በዕድሜ በበሰሉት ዘንድ ብዙም ትኩረት አልሳበም፡፡ ወጣቶች ግን ይሁንታቸውን ሰጥተውታል፡፡
በዕለት ፍጆታና በምርታማነት ላይ በማተኮር የወጪ ንግዱ ነዳጅ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ፍላጎትንም ያማከለ እንዲሆን ማቀዳቸውም ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡ የቱጃሮቹና የፖለቲከኞች መታሰር ምክንያትም ከ2030 የልማት ዕቅድና አዳዲስ ይፈጠራሉ ከተባሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ያሉ ቅሬታዎችን ለማርገብ ታቅዶም ነው ሲባል ከርሟል፡፡
አልጋ ወራሹ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ መፍቀዳቸው፣ ካለፉት 40 ዓመታት ወዲህ ማዕቀብ የተጣለባቸውን ፊልሞችና ቴአትሮች መፍቀዳቸውና በአብዛኛው የምዕራቡ ልማድ ተብለው የተፈረጁ የአኗኗር ዘይቤዎችን ማንፀባረቃቸው በወጣቱ ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረውም አዛውንቶች ጥያቄ ያነሱባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ባልተቋጩበት 200 የሚጠጉ ልዑላንና ባለሀብቶች መታሰራቸው ጉዳዩን ፖለቲካዊ ይዘት አላብሶት ከርሟል፡፡ ሆኖም የሳዑዲ መንግሥት ባለሀብቶቹንና ፖለቲከኞቹን ያሰረው በሙስና ተጠርጥረው መሆኑን በወቅቱ አሳውቋል፡፡
ያለፉት ሁለት ወራት መንግሥትና ታሳሪዎች የተደራደሩበት ጊዜ ሲሆን፣ በድርድሩም የተወሰኑ ባለሀብቶች ተለቀዋል፡፡ ለመለቀቃቸውም ምክንያት ካላቸው ሀብት 70 በመቶ ያህሉን ለመንግሥት እንዲያስረክቡ መስማማታቸው እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በዚህም አብዛኞቹ ታሳሪዎች የተስማሙ ሲሆን፣ ጥቂቱ ደግሞ በፍርድ ቤት እንደሚከራከሩ አሳውቀዋል፡፡
ባለሀብቶቹ ካላቸው ንብረት አብላጫውን ለመንግሥት እንዲያስረክቡ ከመጠየቃቸውም በተጨማሪ በሆቴሉ እንግልት ገጥሟቸዋል ቢባልም፣ አገሪቷ በምትችለው አቅም ሁሉ ፍላጎታቸው መሟላቱን የሳዑዲ መንግሥት አሳውቆ ነበር፡፡
ቢሊየነሩ ልዑል አል ዋሊድ ቢን ታላልም በሆቴሉ ተመችቷቸው እንደ ከረሙ ምስክርነት ከሰጡት አንዱ ናቸው፡፡ በ60ዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኙት አል ዋሊድ ቢን ታላል በሳዑዲ ቁጥር አንድ ሀብታም ናቸው፡፡
ከሁለት ወራት እስር በኋላ ከመለቀቃቸው ሰዓት አስቀድሞ ከሮይተርስ ጋር በሪትዝ ካርልተን ሆቴል ስለነበራቸው ቆይታ አውግተዋል፡፡
ምንም እንኳን ይደርስባቸዋል የተባለውን በደል ለማስተባበል ብለው ያደረጉት ነው ቢባልም፣ እሳቸው ለሮይተርስ የተናገሩት እንደ ቤታቸው ተመችቷቸው በሆቴሉ መክረማቸውን ነው፡፡
ሮይተርስ የሳዑዲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ነግሮኛል ብሎ እንዳሰፈረው፣ ልዑል አል ዋሊድ የተለቀቁት ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጋር በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ከስምምነት በመድረሳቸው ነው፡፡ ሆኖም በገንዘብ ድርድሩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ለማግኘት አልተቻለም፡፡
ከሮይተርስ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ልዑል አል ዋዲም ከመንግሥት ጋር በነበራቸው ውይይት በሙስና ውስጥ አለመሳተፋቸውንና ንፅህናቸውን አስጠብቀው እንደወጡ ተናግረዋል፡፡
በታሰሩበት ጊዜ ድርጅቶቻቸውን ከሚመሩ ኃላፊዎች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው አስታውሰው፣ ለመንግሥት ምንም ዓይነት ንብረት አስተላልፈው እንዳልሰጡና በመንግሥት እንዳልተጠየቁም ገልጸዋል፡፡
መታሰራቸውን ‹‹ካለመግባባት የመነጨ›› የሚሉት አል ዋሊድ፣ በአልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን የተረቀቀውን የኢኮኖሚ ሪፎርም እንደሚደግፉ አክለዋል፡፡ ‹‹ምንም ቅጣት የለም፡፡ በመንግሥትና በእኔ መካከል ውይይት ብቻ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
እንግልት ደርሶባቸዋል የተባሉት ልዑል አል ዋሊድ በሪትዝ ካርልተን ሆቴል የነበራቸውን አኗኗር ሲያስጎበኙ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ቀርበዋል፡፡ ‹‹የምደብቀው ነገር የለም፡፡ ተመችቶኝ ነበር፡፡ እንደ ቤቴ እዚህ ፂሜን እላጫለሁ፣ ፀጉር አስተካካዬም ይመጣ ነበር፤›› በማለት ከምግብ ቤታቸው ቢሮዋቸው፣ መፀዳጃ ቤትና መኝታ ክፍላቸውን እየተዘዋወሩ አሳይተዋል፡፡
አትክልት ተመጋቢ መሆናቸውን በማስታወስም የፈለጉት ሁሉ ይቀርብላቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኛት ይችሉ እንደነበርም አሳውቀዋል፡፡ በቢሯቸው ውስጥም የእሳቸው ምሥል ያለበት የትኩስ መጠጥ መጠጫ ኩባያ ተቀምጦ ተስተውሏል፡፡
ከእስር ከተለቀቁ በኋላም ‹‹በእርግጠኝነት ከሳዑዲ ዓረቢያ አልወጣም፡፡ ይህ የእኔ አገር ነው፤›› ብለዋል፡፡
አል ዋሊድን ጨምሮ 90 ባለሀብቶች ቅጣታቸው ተነስቶላቸው የተለቀቁ መሆናቸው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ለነፃነታቸው ሲሉ ገንዘብ፣ ሪል ስቴታቸውንና ሌሎች ተቀማጭ ንብረታቸውን እንዲሰጡ መገደዳቸው ይነገራል፡፡ 95 ባለሀብቶች ደግሞ አሁንም ያልተለቀቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ የተወሰኑት ክስ ይመሠረትባቸዋል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ዘብ አዛዥ የነበሩት ልዑል መቲብ ቢን አብደላ አል ሳዑድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ከፍለው መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩት ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ጉዳይ ግን አልታወቀም፡፡
ገልፍ ኒውስ እንደ ዘገበው፣ የሳዑዲ ዓረቢያ ፀረ ሙስና ዘመቻ 107 ቢሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡ የሳዑዲ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሼክ ሳዑድ አል ሞጀብ እንዳሉት፣ ከታሳሪዎቹ ጋር በተደረገ ድርድር የተጠቀሰው መጠን ተገኝቷል፡፡ ይህ መጠን የተገኘው በሪል ስቴት፣ በንግድ ተቋማት፣ በዋስትና ሰነዶች፣ በጥሬ ገንዘብና በሌሎች ሀብቶች ነው ተብሏል፡፡ በእስር ላይ ከነበሩ 381 ሰዎች 56 ያህሉ አሁንም በቁጥጥር ሥር መሆናቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
የልዑል አል ዋሊድም ሆነ የሌሎች ታዋቂ ባለሀብቶች ከእስር መለቀቅ የሳዑዲን ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ፖለቲካ በተመለከተ ነግሦ የነበረውን ውጥረት እንዳረገበው የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡