Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየዋሻ ሥዕሎች ድምፅ ከለገኦዳ እስከ እምባ ፈቃዳ

የዋሻ ሥዕሎች ድምፅ ከለገኦዳ እስከ እምባ ፈቃዳ

ቀን:

ለኢትዮጵያዊ ጥንታዊነት ምስክርነት የሚቆሙ በተለያዩ ሥፍራዎች በርካታ ባህላዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ለዘመናት ‹‹የሦስት ሺሕ ዓመት›› ታሪክ የሚለውን ይትበሃል የሚቀይሩ፣ ከአራት ሺሕ ዓመታት በላይ የሚያስቆጥሩ ግኝቶች፣ በሥነ ቁፋሮ ባለሙያዎች መገኘታቸው ከአሠርታት ወዲህ ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡  ለዚህም በምሥራቅ በድሬዳዋ አካባቢ፣ በሰሜን በዓዲግራት አካባቢ የተገኙት ዕድሜ ጠገብ የዋሻ ሥዕሎችና ሌሎችም የጥበብ ውጤቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የዋሻ ሥዕሎች ሙዚየም ብትባል ማጋነን አይሆንም፤›› እንደሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር አቶ ተክሌ ሐጎስ አገላለጽ፣ የዋሻ ሥዕሎች ከሱዳን ጠረፍ ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ ጀምሮ በተምቤን በኩል አድርጎ፣ በምሥራቅ ትግራይ እስከ አፋር፣ በምሥራቅ ከድሬዳዋና ደቡብ አካባቢ በተዘረጋ ሰንሰለት ውስጥ በርካታ የዋሻ ሥዕሎች አሉ፡፡ በዘመን ስሌት ከስድስትና ሰባት ሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ የተሣሉ ናቸው፡፡

ለገኦዳ

- Advertisement -

ድሬዳዋ ከሚያስጠሩ መስህቦች መካከል የለገኦዳ የዋሻ ሥዕሎች ይገኙበታል፡፡ ከከተማዋ 38 ኪሎ ሜትር ርቀት በኋላ ከሚታየው ሰንሰላታማ ተራራ ጉያ የሚገኙት የዋሻ ሥዕሎች ከ6,000 ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

1920ዎቹ አካባቢ በተመራማሪዎች ዕውቅና ያገኙት የዋሻው ሥዕሎች ፍየል፣ ዝሆን፣ ግመልና ሌሎች የቤትና የዱር እንስሳት፣ የመገልገያ ቁሳቁሶችና የሰዎችም ምስሎች የያዙ ናቸው፡፡

በለገኦዳ የሚገኙት ሥዕሎች ሰው፣ እንስሳ ወይም ቁስ አካል ሙሉ በሙሉ ባያንፀባርቁም በግልጽ የተቀመጡ መሆናቸው፣ ይህም  እንዲተላለፍ ወደተፈለገው መልዕክት ወይም እንዲታይ ወደተፈለገው ቁስ በቀጥታ የሚወስዱ እንደሆኑና ተቀጥላ ነገሮች አለመካተታቸው ሥዕሎቹን ለዕይታ እንዳቀለላቸው በአንድ ወቅት ለሪፖርተር የገለጹት የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና መምህር ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ፣ ‹‹ሥዕሎቹ የወቅቱ ማኅበረሰብ አረዳድ ከፍ ያለ እንደነበር ያሳያሉ፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በድሬዳዋ አቅራቢያ ጥንታዊ ሥዕሎች ከሚገኙባቸው ዋሻዎች መካከል ፓርክ ኢፒክ ዋሻ፣ ሒንኩፍቱ ዋሻና ጎዳ አጀዋ ዋሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፓርክ ኢፒክ ከድሬዳዋ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ሲሆን፣ ዝሆን፣ አንበሳና ጅብን የመሰሉ የዱር እንስሳት ሥዕሎችና ጥንታዊ የሰው ልጅ መገልገያ ቁሳቁሶች በዋሻው ተገኝተዋል፡፡

ስለ ሒንኩፍቱ ዋሻ የተሠራ በቂ ጥናት ባይኖርም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በውስጡ  በደማማቅ ቀለማት የተዋቡ ሥዕሎች እንዳሉና ውስጥ ለውስጥ ረዥም ርቀት እንደሚያስጉዝ ይናገራሉ፡፡ ከድሬዳዋ 28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው ጎዳ አጀዋ እንደ ሌሎቹ ዋሻዎች ልዩ ልዩ ዘዬ ያላቸው ሥዕሎችና ጽሑፎች የሰፈሩበት ነው፡፡

የዋሻ ሥዕሎች ድምፅ ከለገኦዳ እስከ እምባ ፈቃዳ

 

እምባ ፈቃዳ

በምሥራቃዊ ትግራይ ከዓዲ ግራት ከተማ ዛላምበሳ በሚወስደው መንገድ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው እምባ ፈቀዳ (እንዳ ጊሄ) የዋሻ ሥዕሎች ባለጸጋ ነው፡፡

ይህ የዓዲ ግራት ሰሜናዊ ክፍል ማራኪ መልክአ ምድር ያለው ሆኖ በርካታ ቅርሶችን በመሬትና በዋሻ ውስጥ መያዙ ይነገርለታል፡፡ በተለይ ዑና ዓዲ በሚባለውና በመነበይቲ መንደር በቁፋሮ የተገኘው ግኝት የሚያሳየው መነበይቲ ከአክሱም ሥልጣኔ በፊትና በዘመነ አክሱም መካከል የነበረ መሆኑን ነው፡፡

ከመነበይቲን ደሀነን አጠገብ በእምባ ፈቃዳ ኮረብታዎች ውስጥ የሚገኙ የዋሻ ሥዕሎች በሚመለከት እ.ኤ.አ. በ1941 የጻፈው ጣልያናዊው የአርኪኦሎጂ ባለሙያ ግራዚዮስ፣ በዋሻው ከተሣሉት ሥዕሎች ጥቂቶቹ ተመሳሳይነት ያላቸውና ጦር የያዙ ተዋጊዎች በእርሻና በአደን ላይ ሆነው የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ሥዕሎች የሰው ምስል በቀስት በመሮጥ ላይ ያሉ የተለጠጠ ሰውነት ያላቸው የዱር እንስሳዎችን ሲያድኑም የሚያሳይ ነው፡፡ በዋሻው በስተቀኝ በኩል የሚገኘው ሥዕል ደግሞ የእርሻ ተግባር በጥማድ በሬ ሲታረስ ማሳየቱ በኢትዮጵያ በበሬ የማረስ ዕድሜ የራቀ ጥንታዊነት እንዳለው አመላካች መሆኑን የአርኪዮሎጂ ባለሙያው አቶ ጌታቸው መረሳ ንጉሥ እ.ኤ.አ. 2006 ባቀረቡት ጥናት ገልጸዋል፡፡

በሳቸው ትንታኔ መሠረት እነዚህ በዋሻው ግድግዳ ላይ ተሥለው የሚገኙት ሻኛ አልባ በሬዎች በሳይንሳዊ አጠራር (ቦስ ታውሩስ) የሚባሉት በአንደኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከታዩት ሻኛ ካላቸው የተለዩ ዝርያዎች በሳይንሳዊ አጠራራቸው (ዘቡ ቦስ እንዲከስ) ከሚባሉት ቀድመው የታዩ ሲሆኑ፤ በበሬ የማረስ ዘዴ የሚያሳየው የዋሻ ሥዕል በአፍሪካ ቀንድ ብቻ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል፡፡

በዋሻው ግድግዳ ላይ የተሠሩትን ሥዕሎች ዕድሜ ለመገመት አስቸጋሪ ቢሆንም በሥዕሎቹ ላይ የሚገኙ ምልክቶች ለምሳሌ ሻኛ የሌላቸው በሬዎች፣ የካናዳ አርኪዮሎጂ ባለሙያ ዶ/ር ካትሪን ዲ’አንድርያና ሌሎችም በመስኩ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ባደረጉት የፓናል ውይይት የተስማሙት ሥዕሉ የተሣለው በዘመነ አክሱም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ200 ዓመትና ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ200 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ነው፡፡

የዋሻ ሥዕሎች አሳሳቢ ሁኔታ

ሪፖርተር ከዓመት በፊት የለገኦዳን ቦታ በጎበኘበት ወቅት ከሥዕሎቹ መካከል ከፊል አካላቸው የደበዘዘ ተፈርክሶ የጎደለም አይቷል፡፡ ሥዕሎቹ በቂ ጥበቃ እየተደረገላቸውም አይደለም፤ ለሰው ሠራሽና የተፈጥሮ እክሎችም ተጋርጠዋል፡፡

በወቅቱ እንደተገለጸውም፣ ሥዕሎቹን ለአደጋ ካጋለጡት ምክንያቶች አንዱ ወደ አካባቢው የሚሄዱ አንዳንድ ጎብኚዎች ደንታቢስነት ነው፡፡  ሥዕሎቹ ረዥም ዘመን ስላስቆጠሩና የተሣሉትም በድንጋይ ላይ በመሆኑ አቧራ ስለሚለብሱ በግልጽ አይታዩም፡፡ ጎብኝዎች ሥዕሎቹ በግልጽ እንዲታዩዋቸውና ፎቶግራፍ ለማንሳት እንዲመቻቸው ውኃ ይደፉበታል፡፡ በዚህ ምክንያት የሥዕሎቹ ቀለም እየደበዘዘ ነው፡፡ በሰዎች ሳቢያ ከሚደርሰው ጉዳት የአካባቢው ነዋሪዎች ዋሻው ላይ ጭስ መልቀቃቸው ይነሳል፡፡ ዋሻው አናት ላይ ቤት የሚሠሩ ንስሮችና ሽኮኮዎችም በዋሻው ይፀዳዳሉ፡፡

በአካባቢው ያሉ የቤትና ዱር እንስሳትም በቦታው ስለሚፀዳዱ ሥዕሎቹ የቀደመ ይዘታቸውን እያጡ ነው፡፡ ዋሻው በዚሁ ከቀጠለ ሥዕሎቹ ሊጠፉ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በወቅቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪው  ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ፣ ‹‹ከኢትዮጵያ አንድ ጫፍ ተነስተን ወደ ሌላው ስንሄድ በርካታ የዋሻ ሥዕሎች እናገኛለን፤ አሳሳቢው ግን እንክብካቤ እየተደረገላቸው አለመሆኑ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ አቶ አህመድ፣ በተለይ ለገኦዳ ትኩረት ካልተቸረው፣ ሥዕሎቹ በቅርብ መጥፋታቸው አይቀሬ ነው ከማለትም አልተቆጠቡም፡፡

በኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ ሁነኛ ቦታ እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አገኘሁ አዳነ እንደሚያሳስቡት፣ ሥዕሎቹ ከጊዜ ብዛት በተፈጥሯቸው ይዘታቸውን እየቀየሩ ቢሄዱም በቸልተኝነት ከሚደርስባቸው አደጋ መከላከል ዕድሜያቸውን ያራዝመዋል፡፡ ሥዕሎቹ በኢትዮጵያ ሥነ ሥዕል ታሪክ ያላቸው አስተዋጽኦ በተመራማሪዎች መጠናት እንደሚኖርበት፣ የጥናቶቹ ውጤቶች ቢሰነዱ አሻራቸው ለዘመናት እንዲዘልቅ ማገዙንም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

ዓጋመ፣ ክልተ አውላሎና ኢሮብን የሚያካልለው የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን፣ የዋሻ ሥዕሎችን ጨምሮ በርካታ ባህላዊ ቅርሶች ሐውልቶች፣ የቤተ መንግሥት ፍራሾች፣ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት፣ እንዲሁም የድንጋይ ላይ ጽሑፎችንም አቅፎ ይዟል፡፡

ከአገር ቤት አልፎ የአውሮፓውያን ተመራማሪዎች ትኩረት የሳበው አካባቢው ያሉትን ሀብቶች ከመጠበቅና ከመንከባከብ አንፃር ክፍተት እንዳለበት ይልቁንም በተለያዩ ምክንያቶች በቅርሶቹ ላይ ጥፋት እየደረሰ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዓዲ ግራት ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የመስቀል በዓል አጋጣሚ በመስከረም 2010 ዓ.ም. ባዘጋጀው አራተኛው የአርኪዮሎጂ ኢንተርናሽናል ዐውደ ጥናት ላይ ይኼው ተንፀባርቋል፡፡

በሰሜንም ሆነ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የዋሻ ሥዕሎች አሁን ያሉበት ሁኔታ ከተፈጥሮ ሠራሽ ችግር አኳያ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ይደመጣል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ተክሌ ሐጎስ፣ በምሥራቃዊ ዞን ከዋሻ ዘመን ጀምሮ እስከ 19ኛው ምዕት ባሉት ዘመናት የታዩ ባህላዊ ቅርሶች፣ የሚገኙበትንና እየደረሰባቸው ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ ‹‹Condition Assessments of the Tangible Cultural Heritage Resources of Eastern Tigray›› በሚል ባቀረቡት ዳሰሳ የዋሻ ሥዕሎቹና ቦታቸው ባለቤት የሌላቸው ለመሆናቸው በምክንያትነት ያመለከቱት ዋሻዎቹ በገጠር ሰው በሌለበት መኖራቸውን ነው፡፡

በአቶ ተክሌ አነጋገር፣ በምሥራቅ ትግራይ የሚገኙት የዋሻ ሥዕሎች ከዕድሜ ብዛት ከመደብዘዛቸውም በተጨማሪ እረኞችም እየሄዱ በቀለም ይነካኩዋቸዋል፡፡ ቱሪስቶች ኬሚካል እየረጩ ፎቶ ያነሳሉ፡፡ ስለዚህ በጣም በአሥጊ ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ እነዚህን በቅጽበት መመዝገብ ያስፈልጋል፡፡

 (ለዚህ መጣጥፍ ምሕረተሥላሴ መኰንን አስተዋጽኦ አድርጋለች)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...