በንጉሥ ወዳጅነው
ከሰሞኑ መንግሥት በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ለዓመታት የተጠረቃቀመውን ወቀሳ ለማሻሻል አንዳንድ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ እየተወሰዱ ካሉ የማሻሻያ ተግባራትና የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ሊያጠናክሩ ከሚችሉ ሥራዎች መካካል ገዥው ፓርቲ ዋናው ችግር ያለው በራሴ ድርጅት ውስጥ ነው ብሎ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› በማድረግ ላይ መሆኑ፣ ከሰላማዊና ሐሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ገዥው ፓርቲ እያደረገው ያለው ውይይት ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ቢያንስ የእስካሁኑ የምርጫ ሒደትና ውጤት አሁን ያለውን የሕዝብ ፍላጎት እንደማይመጥን ተገንዝቦ፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ሳይቀር ማሻሻያ ለማድረግ መሞከሩም እንደ በጎ ዕርምጃ የሚታይ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ድርድር እያደረጉ መሆናቸው፣ በአገሪቱ የፖለቲካ እስረኛ ‹‹አለ፣ የለም›› የሚለው ንትርክ እንዳለ ሆኖ ለሰላምና ለዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ መነቃቃት ሲባል የታሰሩ ሰዎች በሕግ አግባብ እየተፈቱ መሆናቸውም አዲስ መንፈስ የሚያጭር በጎ ዕርምጃ ነው፡፡ በዜጎች የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች አጠባባቅና አጠቃቀም ላይ ያለው ዝንፈት በየአካባቢው ግልጽ የመነጋገሪያ አጀንዳ እየሆነ መመምጣቱም የነገን በተስፋ ለማየት ማገዙ አይቀርም፡፡
በዚህ ረገድ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የዜጎች የአገር መረጃ የማግኘት መብት ጉዳይ ቀዳሚው መዘውር ሆኖ እየወጣ መሆኑም ይታያል፡፡ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 19 መሠረት፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ላይም ሆነ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 አገራችን ሕጋዊ ዋስትና የሰጠችው ይኼ ጉዳይ በአተገባባር በኩል ያጋጠመው ክፍተት ግን የገነገነ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ራሱ ሕዝቡ ለዘመናት የኖረበት የግልጽነትና የተጠያቂነት አለመኖር፣ በየደረጃው ያለው የሚዲያ ሙያተኛና ኃላፊ አመለካካት መዛናፍና አቅም አለመጎልበት፣ እንዲሁም አጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ ባህሉ አለማደግ ያደረሱት ጉዳት ቀላል አይመስለኝም፡፡ የዚህ ውጤትም የዴሞክራሲ ምኅዳር መጥበብና የመልካም አስተዳዳር መዳከምን ብቻ አይደለም ያስከተለው፡፡ በልማቱ መስክም የሥርጭት ፍትሐዊነትና አሳታፊነት ላይ ጥያቂ የሚያነሱ ወገኖች እንዲበራከቱ አድርጓል ባይ ነኝ፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተደጋግመው በሚቀሰቀሱ ግጭቶችና አለመደማማጦች የሕዝቦች አንድነት እየላላ፣ ግለኝነት እየበዛና የተጀመረው ፈጣን የለውጥ መንገድ እየተደናቀፈ መሆኑ ሲታይ በመስኩ አንዳች ዓይነት ለውጥና ማሻሻያ ለማምጣት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንደተገኘን ይሰማኛል፡፡
ስለሆነም በአዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት መሠረት መንግሥትና የመንግሥት አካላት መረጃን በምን አግባብ መስጠት እንዳለባቸው የሚነሳውን ነጥብ በይደር ለሌላ ጊዜ አቆይቼ፣ በመገናኛ ብዙኃኑ ሚና ላይ ለማተኮር ልሞክር፡፡ የዜጎች ሐሳብን መግለጽና መረጃ የማገኘት መብቶች ዕውን እንዲሆኑ ብሎም ዴሞክራሲው እንዲጠናከር የአገራችን የመንግሥት (የሕዝብ)ም ሆነ የግል ሚዲያዎች እንዴት ይሥሩ? ለወዲፊትስ ዘርፉ እንዴት ቁመናውን አስተካክሎና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት? የሚሉት ቁም ነገሮች ላይ መነጋገር አስፈላጊና ግድ የሚል እምነት በመያዝ አንዳንድ የግል ዕይታዎችን ለመሰንዘር እወዳለሁ፡፡
በግሌ ባለፉት 16 ዓመታት ገደማ በሕዝብ ግንኙነት ሙያተኝነት፣ በጋዜጣ ሪፖርተርነት፣ በአዘጋጅነትና በዋና አዘጋጅነት ሠርቻላሁ፡፡ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በብሮድካስት ሚዲያውም ሆነ በመረጃ ነፃነት ትግበራ ላይ በኃላፊነት ጭምር አገሬን በማገልገሌ በመስኩ ያለውን ጥንካሬም ሆነ ክፍተት በቅርብ ለመገንዝብ እንድችል አድርጎኛል፡፡ እንዲያው ትንሽ ግልጽ ለመሆን ከተፈለገም ራሴ የተሳተፍኩባቸውና አሁን ላይ ለሕዝብ መገናኛ ብዙኃኑ መዳከም አሉታዊ አስተዋፅኦና ድርሻ እንደነበረኝ የሚፀፅቱኝ ችግሮችንም እየተረዳሁ መሆኔ፣ እንደ ዜጋ ነገሩን ፈጥነን በጋራ ማቅናት የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል የሚል ቁጭት እያጫረብኝ ነው፡፡ አሁን ላለው ተጨባጭ ሁኔታ የአገራችን የሚዲያ ሥነ ምኅዳር ከ26 ዓመታት ወዲህ አዲስ ምዕራፍ መጀመሩ ባይካድም፣ በመጠኑና በጥራቱ ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ አመለካከቶችን በማስተናገድ አቅሙ ግን ከጀመረው ለውጥ አንፃር እየቀነሰ መጥቷል ብሎ ለመናገር ይቻል የመስለኛል፡፡ የመስኩ ሙያተኛም በብቃትና በተወዳዳሪነት ረገድ እየተዳከመ፣ ሙያው ጠንካራ ማኅበርና ካውንስልም ሳያገኝ (በሚዲያ የደሰኮረው ሁሉ አፉን ሞልቶ ጋዜጠኛ ነኝ ብሎ ሙያ እያራከሰ) የመንሸራተት ጉዞ ላይ መውደቁ ብዙዎችን የሚያስማማ ሆኖ ይገኛል፡፡ በግሉ (የንግዱ) ሚዲያ አካባቢም የገበያ፣ የስፖንሰርሺፕና መረጃ የማግኘት መብት የጎላ ፈተና ከመሆኑም በላይ፣ የኅትመቶቹ ሚዲያዎች በኮፒ ብዛትና በሥርጭት ረገድ ያለባቸው ተግዳሮት የቁልቁለት ጉዞው አመላካች እንደሆነ ጸሐፊው በቅርቡ በተደረገ ዳሰሳ ጥናት ለማረጋጋጥ ችሏል፡፡
በድምሩ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ሥርዓቱንም ሆነ ሕዝቡን በገንቢ ሒስ ሲሳሳቱ የማያርሙ መሆን አልጀመሩም፡፡ አለፍ ሲልም በውስጣቸው ጭምር አፍጣጭ ገልማጭ ያለባቸው (በተለይ የመንግሥቶቹ)፣ የንግድ ብሮድካስቶቹም በአብዛኛው የእንቶ ፈንቶ መዝናኛ ዘገባና የውጭው ዓለም ቧልት ላይ የተጠመዱ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ሚዲያዎቻችን በጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባር፣ በሙያው መርሆዎችና በአገሪቱ ገዥ ሕጎች ላይ ተመሥርተው አለመሥራታቸው ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱ የቀደመው የአብሮነትና ውህደት፣ የጀግንነትና የአርበኝነት ታሪክን በማቀንቀን አዲሱን ትውልድ በአገራዊ ስሜት ለመቅረፅ አለመነሳሳታቸውና በወቅታዊዎቹ የጽንፈኝነትና የልዩነት ፖለቲካ ማዕበል ሲላጉ መዋልና ማደራቸው ክፉኛ የሚያሳዝን እውነታ ሆኖ ይገኛል፡፡ እንዲያውም በቅርቡ የብሮድካስት ባለሥልጣን ሞኒተር በተደረጉ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ እንደገለጸው አንዳንድ ሚዲያዎች በተለያዩ ጊዜዎች ሁከት እንዲባባስና የሕዝብ ለሕዝብ ግጭትም እንዲያገረሽ የሚገፉ መረጃዎችን እስከ ማሰራጨት ይደርሱ እንደነበር በአፅንኦት ማስረዳቱ፣ የዘርፉን አደገኛ አካሄድ ቁልጭ አድርጎ ያመለክታል፡፡
በመሠረቱ በየትኛውም ዴሞክራሲ እየገነባ ባለ አገር ውስጥ እንደሚታየው ሚዲያው በየደረጃው በነፃነት መሥራት ሲችል ነው የዴሞክራሲ ባህል የሚገነባው፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት አገራዊ አለት የሚነጠፈው፣ ብሎም ብሔራዊ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት፡፡ ለዚህም ሲባል የአገራችን መገናኛ ብዙኃን (ሚዲያዎች) ነፃነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ብቻ ሳይሆን፣ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት 590/2000 አዋጅ መሠረትም የተከበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እውነቱ ይኼ ይሁን እንጂ ሚዲያው በነፃነት እንዲሠራ፣ በነፃነት እንዲዘግብ፣ በነፃነት እውነትን ለሕዝብና ለመንግሥት እንዳያደርስ በርካታ እንቅፋቶች እንደተጋረጡ መፈተሽ ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ ያግዛል፡፡
እንግሊዛዊው የሕግ ባለሙያ፣ ጋዜጠኛና የመስኩ ተመራማሪ ዊሊያም ብላክስተን (1723-1780 ) ገና በጠዋቱ ያስቀመጠው ተወዳጅ አባባል አለ፡፡ “The liberty of the press is indeed essential to the nature of a free state. But this consists in laying no previous restraints up on publications, not in freedom from censure for criminal matter when published. To do this all information accessibility is very vital!” በማለት ነፃ መንግሥትን ለመገንባት የፕሬስ ነፃነት ያለውን ፋይዳ፣ የሐሳብ ነፃነቱ ሊጠነቅቅባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮችና ይኼን ለማሳለጥ ደግሞ የመረጃ አቅርቦትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጿል፡፡
ከዚህ አንፃር በአገራችን የሚዲያ ንፍቀ ክብብ አለመጠናከር ውስጥ ቀዳሚው ችግር ከመንግሥት በኩል የሚያጋጥመው ተግዳሮት መሆኑን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ የፕሬስ ነፃነት ሕግ በአንፀባራቂ ቀለም ተጽፎ በሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም፣ አሁንም በተለይ የመንግሥት ሚዲያው (ደጋግመን እንደ ምንወቅሳቸው የቀድሞዎቹ ሥርዓቶች) የሥርዓቱ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያና ስኬት ብቻ ነጋሪ እንዲሆን የተፈረደበት መስሎ መቀጠሉ፣ ለውጥ የሚያሻው ነው የሚሉ ጥናቶች እንዳሉ መካድ አዳጋች ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየሚዲያ ተቋሙ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ቢቀረፅም በአንድ ዕዝ ላይ የተመሠረተ የሚመስል የኤዲቶሪያል ኮሚቴና የፖለቲካ ተሿሚ ተፅዕኖ የበረታ መሆኑ፣ መፈናፈኛውን እንዳጠበበው ጋዜጠኞች በሹክሹክታ ማንሳታቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ የተነሳ ወጣ ብሎና በነፃነት ሊሠራ የሚችለው ሙያተኛ እየተገፋ ታዛዡና አድርባይነቱ የሞቀው ወገን ብቻ ሕግ እየጣሰ (ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከአዋጅ 590/2000 ጋር እየተጋጨ) ለወር ደመወዝ እንዲኖር የተገደደ መስሏል፡፡ የተሻለ ሊሠራ የሚችለውም የማያምንበትን እየሠራ በምንቸገረኝ አገርን እየጎዳ የጋዜጣ ገጽና የአየር ሰዓት ያባክናል፡፡
በኅትመትም ሆነ በብሮድካስት ሚዲያው የግሎቹ ጋዜጠኞቹም ሆኑ የሚዲያ ባለቤቶች አልጋ በአልጋ ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ እየተፍገመገሙ የኅትመት ወጪን ሸፍነውና በመረጃ ክልከላም ውስጥ ቢሆን የቀጠሉ ቢኖሩም፣ ቀላል ቁጥር የሌላቸው በተለያየ ምክንያት ከጨዋታው ወጥተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአንዳንዶቹ የራሳቸው የሙያ ድክመት፣ ሕግን መፃረር፣ ጽንፈኛና የጥላቻ አካሄድ ዋነኛ እንቅፋት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዘገባቸው በደግና በመልካም አፈጻጸሞች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ (ምንም ዓይነት የዕርምት ሒስ እንዲነሳ የማይፈልጉ) የሚሹና ለዚህም እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ የመንግሥትና የፓርቲ ሰዎች፣ ድርጅቶችና ተቋማትም አይገፏቸውም ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ በጥናት እንደታያውም የግሉን ሚዲያ እንደ ጠላትና አነስ ሲልም እንደተገዳዳሪ የሚመለከት የመንግሥት ሹም ቁጥሩ ትንሽ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡ በዚህ በኩል መረጃ እንዲያደረጁና በቀላሉ እንዲሰጡ የተመደቡ የሕዝብ ግንኑኙትና የኮሙዩኒኬሽን ሙያተኞች የችግሩ ሰለባ ሆነው ማየት ደግሞ የአደጋውን ክፉነት የሚያሳይ ነው፡፡
እነዚህን አንዳንድ የፀረ ዴሞክራሲ ሥርዓቶች የዞረ ድምር ያለቀቃቸው (ለመንግሥትም ለሕዝብ የማይበጁ) ጭፍን ካድሬዎችና መንቻካ ሰዎች ለመሆኑ እናንተ እነማን ናችሁ? ብሎ መንግሥት፣ ሕዝቡና ጋዜጠኛው መጠየቅ ያለባቸው ጊዜ አሁን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ገንቢ ሒስን፣ የሕዝብ ድምፅንና የአገር ፍላጎትን ወደ ጎን ብለው ራሳቸውን ብቻ ለማዳመጥ የሚሹ ገዳቢዎችና የደረስንበትን የመረጃ ዓለምነት ያልተገነዘቡ ኃይሎች ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም በላይ አይደላችሁም ማለት የሚያስፈልገውም አሁን ላይ ነው (እዚህ ላይ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ተሸካሚ የሚዲያ ባለቤቶችና የሥራ ኃላፊዎችም ስለማይጠፉ በጥብቅ ሊወገዙ ይገባቸዋል)፡፡
በመሠረቱ ሳንሱር (ቅድመ ምርመራ) በአገሪቱ ሕግ መሠረት የተከለከለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከቀድሞው ሥርዓት ጋር አብሮ ወደ መቃብር እንደ ወረደ ተደጋግሞ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ይኼ እውነታ በውል እየታወቀ ዛሬም በሥውር የሳንሱር መቀስ የተጠመዱ ኃላፊዎችና ሹማምንት በየመሥሪያ ቤቱ መታጎራቸውን መሸሸግ ግን ለመማር አለመዘጋጀትን የሚያሳብቅ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ይኼን ማድረግ የሚዳዳቸው የሚዲያ ኤዲተሮችና ኃላፊዎች በመንታ ልብ ውስጥ ሆነው በአንድ በኩል ስለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የሐሳብ ነፃነት ይሰብካሉ፡፡ በሌላ በኩል ይኼ ይተላለፍ ይኛው ይቅር እያሉ ያፍናሉ፡፡ ሚዲያው በአግባቡ ሙያዊ ኃላፊነቱን እንዳይወጣ በየቦታው የጎን ውጋት ሆነው አላሠራ ያሉትም እነዚህን የመሳሰሉ ወገኖች በመሆናቸው፣ ፈጥኖ የሚዲያውን ሥነ ምኅዳር አጋርነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ለረዥም ጊዜ በሙያው ውስጥና በአንጋፋ የኅትመት ተቋማት የሠሩ ጋዜጠኞች እንደሚናገሩት፣ መንግሥት በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ (በየትም አገር ስለሚሠራበት) የሚዲያ ትኩረት አቅጣጫ መስጠቱ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹ይህን ጻፍ፣ ያንን አትጻፍ፣ እገሌ በሚዲያው እንዳይስተናገድ ወይም ሕዝቡ የሚነጋገርበትን ጉዳይ አትንካው፣ ወይም ይኼን ዘፈን ከዚህ አርካይቭ አጥፋ …›› እያለ የሚገድብ መንግሥታዊ አካል ካለ ሞቶ የተቀበረው ቅድመ ምርመራ ተመልሶ ላለመምጣቱ ዋስትና የለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የመገናኛ ብዙኃን አንዳንድ ሙያተኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግል ጥረት የሚያሳዩትን ምርጥ ተሞክሮዎችን የማስፋት፣ ሁሉንም ወገን የማሳተፍና መንግሥታዊ ሒስ ጭምር ሊገፉበት እንደማይችሉ ዕሙን ነው፡፡ እዚህ ላይ ዶ/ር ጀማል መሐመድ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹ደንባራዎቹ መገናኛ ብዙኃን›› ሲሉ በጥልቀት የተቹበትን ጽሑፍ በነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ መመልከት ለመሻሻል ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡
በመሠረቱ ሀቁን በመመርመር ማንኛውንም የዘገባ መረጃ ሚዛናዊ አለማድረግ፣ ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚቀዳ ዘገባን አለማስተናገድ፣ በፕሮቶኮልና በድል ወሬ የታጨቀ ዘገባን ብቻ አየሩን መሙላት፣ ብሎም ሚዲያዎቹ ከሁለትሽዮና ከሦስትዮሽ የውይይት መድረክ እንዲርቁ ማድረግ በቀዳሚነት የሚጎዳው መንግሥትን ራሱን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት የሕዝብ በምንላቸው የራሳችን ሚዲያዎች ላይ ያለው የሕዝብ አመኔታና ተቀባይነት እየቀነሰ መምጣቱ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ትናንት በአርዓያነት የተጠቀሱ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግንባታዎች፣ የስኳር ፕሮጀክቶችና ኮንትራክተሮቻቸው፣ እንዲሁም የሴክተሩ ኃላፊዎች ሁሉ ዛሬ በሙስናና ሕዝብን በመበደል ከመከሰሳቸው በፊት ነገሩን ሳያመዛዝን (አንዳንዶቹ በብልጣ ብልጥ ሕዝብ ግንኙነታቸው ተደብቀው) በሐሰት ሪፖርት እያሞካሸ የካባቸው ሚዲያው ስለነበር ነው፡፡ ችግሮች እንዳሉባቸው ሕዝቡ ራሱ የሚናገርባቸውን መሥሪያ ቤቶች አንኳን መፈተሽ ባለመቻሉ ሕዝብና መንግሥት ከመጎዳታቸው ባሻገር አጨብጭብ ሲባል መዳፉ እስኪላጥ የሚያጨበጭብ፣ አልቅስ ሲባል ላንቃው የሚቀደድ ሚዲያ እየተበራከተ እዲመጣ ሆኗል የሚሉን ብዙዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ውሎ አድሮ እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ሁላችንንም ያሳፍራል፡፡ አንገትም ያስደፋል፡፡
እዚህ ላይ በተለይ በመንግሥት ሚዲያው አካባቢ ያለው አሠራርና የሙያተኛው የዘገባ ሥነ ልቦና መርማሪነት የጎደለው መሆኑና ሕዝብ አሳታፊ አለመሆኑ አንዱ ችግር ቢሆንም፣ ዋነኛው ችግር ግን አስፈጻሚው፣ ሕግ አውጪውም ሆነ ሕግ ተርጓሚው ስኬት እንጂ ውድቀትን መዘገብ እንደ ነውር መቁጠሩ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ የተሠሩ ሥራዎችን ከመጠንና ከቁጥር አኳያ ብቻ እንጂ ከጥራት፣ ከወጪ፣ ከጊዜና ከሕዝብ ተጠቃሚነት አንፃር የማይመዝነው የሥራ ኃላፊ ሁሉ ለከንቱ ሙገሳና ላልተገባ ፉክክር ሲጠቀምበት የቆየው ሚዲያውን መሆኑም የውድቀቱ መጀመርያ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ሚዲያው የሚፈለግበትን ያህል ኃላፊነቱን አልተወጣም በሚል የገደል ማሚቱ ሆነው የሚጮሁትም እነዚሁ ወገኖች መሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም በቀዳሚነት መንግሥት በውስጡ ያሉ የሥራ ኃላፊዎችን፣ ባለሙያዎችን በተለይም የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ሰዎችን በማረም ለፕሬስ ነፃነትም ሆነ ለሕዝቦች የአመለካከት ብዝኃነት መስተናገድ እንዲተጉ ማድረግ አለበት፡፡ ውግንናውም ለሕጋዊ፣ ሚዛናዊና ዴሞክራሲያዊ ሚዲያዎችና ሙያተኞች ሊሆን ይገባል፡፡
በቅርቡ ኢቢሲና የእንባ ጠባቂ መሥሪያ ቤት ባዘጋጁት መድረክ ላይ በቀረበ ጽሑፍ እንደተገለጸው፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 19 ልክ) የሐሳብ ነፃነትን በተሟላ መንገድ ዋስትና ሰጥቷል ሊባል ይችላል፡፡ እዚያው ላይ ቅድመ ምርመራና ክልከላም አክትመዋል፡፡ ስለሆነም በሕግ ከተከለከሉት በስተቀር ማንኛውም የሕዝብና የመንግሥት መረጃ በጋዜጠኞች በተጠየቀበት ጊዜ ሁሉ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የትኛውም የመንግሥት አካል መስጠት እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ይኼም በተለይ በመገናኛ ብዙኃንና በመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት ላይ አስፈጻሚውና ሁሉም የመንግሥት አካል የተጣለበት ግዴታ ተደንግጓል፡፡ ይሁንና ዕንባ ጠባቂ ተቋምና የኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት መረጃ የመስጠት ግዴታ አለብን የሚል አመራር ገና እንዳልተፈጠረ ማስረዳታቸው አሁንም የሥራውን ክብደት አመላካች ነው፡፡ በአዋጁ ላይ በመረጃ ክልከላ፣ ቅሸባና መጓተት ምክንያት የተቀመጠው ገንዘብና የእስር ቅጣት እስካሁን በአንድም መረጃ ሰጪ ላይ አለመተግበሩም መዘናጋቱን እንዳራዘመው ተገምቶል፡፡
በመሠረቱ የመረጃ ጥያቄዎቹ በደል ከደረሰባቸው፣ ብሶት ካለባቸው ሰዎች፣ የመልካም አስተዳደር የፍትሕ ችግር አጋጥሞናል ከሚሉና በተጨባጭ ማስረጃ ለማቅረብ ከሚችሉ ክፍሎች ሁሉ ሊነሱም ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኛውም ሆነ የሚዲያ ተቋሙ የመጀመርያው ኃላፊነት ማጣራትና የሚመለከታቸውን አካላት በሚዛናዊነት ማነጋገር መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጪም ሚዲያው አስተያየቶችን፣ ሐሳቦችንና ምልከታዎችን የመቀበልና የማስተናገድ ኃላፊነትም አለበት፡፡ የለም እውነቱ ይኼ አይደለም የሚል ወገን ደግሞ በወጣው ጽሑፍ ላይ ምላሽ የመስጠትና እውነታውን ለሕዝብ ግልጽ የማድረግ መብት አለው፡፡ በዚህም የተለያዩ አስተሳሰቦች ይንሸራሸራሉ፣ ሕዝቡም ይተነፍሳል፣ የአገሪቱ ፖለቲካም ውስጡን ለማየት ዕድል ያገኛል፡፡ መንግሥትም እውነተኛውን የሕዝብ ስሜት እየመረመረ ፈጣን የእርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ይችላል፡፡ መኬድ ያለበትም ወደዚሁ ብርሃን ይመስለኛል፡፡
ማጠቃላያ
ንሰኃ መግባት በሚመስል ለዓመታት በዋና ተዋናይነት የሠራሁት ሥራ አሁን አገሪቱና ሕዝቦቿ ከሚፈልጉት ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ አንፃር የተሟላ እንዳልሆነ ተሰማኝና ያስታወስኩትን ያህል ክፍተቱን ለማንሳት ወደድኩ፡፡ ይኼን ያደረግኩትም ከእውነተኛ አገራዊ ተቆርቋሪነት እንጂ ማንንም ለማስከፋት ወይም ለማስደሰት በሚል አይደለም፡፡ በእኔ እምነት አሁን የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋትም ሆነ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋጋጥ ምክንያታዊነት መጎልበት፣ የጥላቻና የጽንፈኛ መንገዶችም መጥበብ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሐሳብ ነፃነት ሳይደነቃቀፍ መረጋጋጡ ብቻ ሳይሆን፣ የአመለካካት ብዝኃነቱም መፈናፈኛ ቦታ ሊያገኝ ግድ ይለዋል፡፡ ይኼን ማድረግ የሚቻለውም በዋናነት የሚዲያው ንፍቀ ክበብ በብቃት፣ በተወዳዳሪ ዴሞራሲያዊነት ሲታነፅና በሙያው ሥነ ምግባርና መርሆ ላይ ተመሥርቶ መሥራት ሲችል ነው፡፡ የወጡ ወሳኝ ሕጎችም ሳይጎደሉ መተግበር ሲችሉ ነው፡፡
እዚህ ላይ ‹‹የልማት ጋዜጠኝነት›› የሚለውን የአገራችንን የሕዝብ (መንግሥት) ሚዲያዎች ፍልስፍና ማወቅና መተግበር ብቻ ሳይሆን፣ መፈተሽም የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ የምንገኝም ይመስለኛል፡፡ ጽንሰ ሐሳቡን በተሸራረፈ መንገድ ተገንዝቦ ዴሞክራሲን ለመገንባት በሚታትር ሕዝብ ውስጥ መተግበር አዳጋችነቱ ግልጽ መሆኑ ለአባባሌ አንድ መነሻ ነው፡፡ ያውም ኮሙዩኒንኬተሩና ጋዜጠኛው ሚናቸው ተቀላቅሎ ሁሉም ዜና ሠሪዎች በሆኑበት፣ ፕሮፓጋንዳውና መሬት ላይ ያለው እውነታ በሚጋጭበት፣ የምርመራ ዘገባን አጥብቆ ለመያዝ ባልተቻለበት ሁኔታ፣ እንዲሁም ዴሞክራሲ ብዝኃነት ላለው ሕዝብ የህልውና ጉዳይ ሆኖ በመጣበት ፈታኝ ጊዜ የልማት ጋዜጠኝነትና የኮሙዩኒኬሽን ደጋፊ እንደ ብቸኛ አማራጭ ‹‹ይሁን›› መባሉም በጥልቀት ሊፈተሽ የሚገባው ነው፡፡ ካልሆነ ግን የሐሳብ ነፃነትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አደጋ ላይ መውደቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ በተጨባጭም እየወደቁ እንደሆነ ተገንዝቦ ዘላቂ መፍትሔ ለማመላከት የሚደፍር የአገር መሪ፣ የሚዲያ አመራር፣ የዘርፉ ምሁራና ሙያተኛም ሊታይ ይገባል፡፡ ‹‹ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም›› አይበጀንምና፡፡
በመሠረቱ ተራማጅነት (Progressiveness) የሚመዘነው የተለያዩ አዳዲስ አስተሳሰቦችን፣ ጊዜው የሚጠይቀውን ብቃት በመያዝና በመተግበር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አገራችንም ሆነች ሕዝቦቿ ከአሥር ዓመታት በፊት በነበሩባት ቁመና ላይ እንዳልሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የሚዲያ ኢንዱስትሪው ራሱም ቢሆን በማኅበራዊ ድረ ገጾችና እንደ አሸን በሚፈሉ የሳተላይት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በግልጽ እየተፈተነ ነው፡፡ የአገራችን የሕዝብና የንግድ ሚዲያ አብዛኛው አመራርና ሙያተኛም ይኼን ‹‹ፈተና›› ተገንዝቦ ለለውጥና ለመሻሻል መነሳት አለበት፡፡ ይኼ ሲሆን የሚዲያው ንፍቀ ክበብ ከጋረደው ጭጋግ ፈልቅቆ በመውጣት እንደ ማለዳ ፀሐይ መፍካት ይችላል፡፡ አገርና ሕዝብም ይበልጥ ይጠቀማሉ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡