እነሆ ጉዞ! ከሜክሲኮ ወደ ቦሌ ልንጓዝ ነው። መንገድ ማደሪያና መጨረሻ የለውም። ተጓዥም ጉልበቱ ቢዝል ነው። መንገድና መንገደኞች ዛሬም ተገናኝተናል። ወደፊት የሚታይ ስናጣ ቆም ብለን የኋላውን የምናጠና ብዙዎች፣ የፊቱን ብቻ ውለዱ የሚሉትን እያደናቀፍን እናበሳጫቸዋለን። በብስጭት የተጀመረ መንገድ ስፋቱና ርዝመቱ ከምንም ነገር ጋር አይወዳደርም። አሁን አሁን ተስፋ መቁረጥ ብቻ ሳይሆን ተስፋ የመቁረጥ አቅም ብድር ፍለጋ የሚንከራተቱም መንገዱን ተቀላቅለዋል። ዙሪያ ገባው ትርምስ ነው። ጩኸት ነው። እሪታና ወዮታ ነጠላ ዜማዎቻችን ሆነዋል። ደጋግመን እንደ አዲስ ጥለት የምንዘንጥባቸውና የምንታወቅባቸው ብሶት ወለድ ሸማዎቻችን ናቸው። እዚያ ወያላው መንገደኛ አሠልፎ እንደ ወታደር ይመለምላል። ‹‹አንተ እዚያ። አንቺ ነይ እዚህ፤›› እያለ ይቆጣል። ‹‹ማን እሱ ጋ ተቀመጡ አላችሁ? ውረዱልኝ በቃ አልፈልግም፤›› እያለ ንጭንጩን ያቀልጠዋል። ‹‹ኧረ ስለፈጠረህ ተወን። የአንተን? የመንግሥትን? ወይስ የራሳችንን እንስማ? ምናለበት ለቀቅ ብታደርገን?›› ሲሉት አንዲት ወይዘሮ፣ ‹‹እኔ አስሬዎታለሁ እንዴ? ማን ያሰረውን ማን ይለቃል?›› ይላል ነገረኛው ወያላ።
‹‹ምነው አንተ እንዲህ አፍ ለቀቀብህ?›› አለው ሾፌሩ። ገባ ያለ ከርዳዳ ፀጉሩን በጄል ለድፎ መከራውን ያያል። ‹‹ተወው እንጂ ይናገር። ምኅዳሩን ለማስፋት መሰለን እየተፈታታን ያለነው። በነካ እጃቸው ደግሞ የቋጠሩብንን ሰዎች እጅ ቢያስፈቱልን አሪፍ ነበር። ይልቅ አሁን ንዳው ሞልቷል፤›› ይላል አንድ ዓይኑ የማያርፍ ወጣት ፊት ኋላ እየዞረ። ‹‹መጨረሻ ወንበር ተቀምጦ የሚዞረው ማንን ለማየት ነው?›› ሲል ከጎኔ ያለው ወይዘሮዋ ሰምተውት፣ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ አላለም እንዴ መጽሐፉ? እንኳን መስኮት ከቦት ሰው በጨለማ ግድግዳ ታጥሮም እኮ ማየት ይችላል። ዋናው ልብ ነው፤›› አሉት። ይኼን ሲሉ አጠገባቸው የተሰየመች የቀይ ዳማ፣ ‹‹ያደርግላቸው…›› ብላ በረዥሙ ተነፈሰች። ‹‹እነ ማንን?›› ሲሏት፣ ‹‹የአፍሪካ መሪዎችን ነዋ፤›› ከማለቷ ተሳፋሪው በተስፋዋ ተገርሞ አሽሟጠጣት። ሰውስ እሺ ተስፋ ይሽሟጠጣል እንዴ?
ጉዟችን ከመጀመሩ ሾፌራችን፣ ‹‹በደንብ ፈትሸሃል? ሳይፈተሽ የገባ እንዳይኖር…›› ብሎ መንዳቱን አቆመ። ‹‹ደግሞ ምን መጣ? ብለችሁ ብላችሁ እዚህ ታክሲ ላይ ፍተሻ?›› ተቆጣች አንዷ። ‹‹ታላቁ ስብሰባ እኮ ተጀምሯል። ከፈነዳ በኋላ ከመጠራጠር አሁን መበራበር አይሻልም?›› ወያላው ተለሳልሶ ተጠጋት። ‹‹እውነት ነው ታጣቂው በዝቷል። ወዳጅና ጠላት መለየት ከብዶናል። ደግሞ ሚሊሻ ተማምነን ወጥተን እንቅር?›› ትላለች አንዲት ወይዘሮ። ‹‹ማን አስታጥቆት ማን ያፈነዳል? እናንተ የተጠመደ ስታስሱ ሰው በሰው ፈንጂ እኮ እያለቀ ነው። ኧረ የተማረ ይግደለኝ፤›› ትላለች። ‹‹የተማረ ነው የተሾመ? ተምታቷል እኮ፤›› ይላል ከወይዘሮዋ ጀርባ ሽብርክ ብሎ የቆመ ሠልፈኛ።
ቁጣ ቁጣ ያላት ለግላጋ ተራዋን፣ ‹‹ጫፌን እንዳትነካኝ ሰውዬ። ወንድም ሴትም በጅምላ ሲፈትሽ ዝም ትላላችሁ? ምንድነው ጉዱ?›› ብላ ከመስመሯ አፈንግጣ ወጣች። ይኼኔ አንዱን ትተው ሌላ ሲያሲዙት ዘራፍ ማለት የለመደው ሠልፈኛ፣ ‹‹ለካ እሱም አለ?›› እያለ ወያላውን ገፍትሮ ገባ። ሾፌሩ የሚያደርገውን አሳጣው። ‹‹ሰውዬ ፖሊስ ነው የምንጠራው። አርፈህ ሥራህን ሥራ። ይኼ በልጅ አመካኝቶ አንክቶ መብላት ድሮ ቀረ፤›› ስትል እንዳልነበር ያቺ ወይዘሮ፣ ‹‹ምን በልጅ ብቻ፣ በሕዝብ ድምፅ፣ በሥልጣን፣ በልማት አሳቦ መበስበስም ቀርቷል። ዘመኑ የተሃድሶ ነው፤›› ይላል ቀድሞን ዘሎ ገብቶ መጨረሻ ወንበር ላይ ጥጉን የያዘ ዓይነ ድፍርስ። ይኼኔ ወያላው እኩያው መሆኑን አስልቶ፣ ‹‹እስኪ መጀመሪያ የዞረ ድምሩ ይልቀቅህ። ከዚያ ትፖተልካለህ፤›› አለው። ያ ዘሎ ተነሳ። ካልተጋደልን አሉ። ቋንቋም እንደ መጠጥ ተሳክሮ ማሳከሩ ሳያንስ ጭራሽ ያደረ ነገርና ስካር ሲደረብበት ጎዳናው በአንድ እግሩ ቆመ። ዳሩ ልብ እንደ ዋዛ ቀጥ አይልምና የቆመው ጉዞ ቀጠለ።
ወይዘሮዋ ነገር ለማብረድ፣ ‹‹የተፈጠረውን እርሱትና እስኪ ስለመሠረተ ልማት ምናምን አውሩ፤›› አሉ። በዚህ መሀል የወያላው ማን አለብኝ የንቀት ንቀት ያጠቆረው እጅ ከወይዘሮዋ አጠገብ የተሰየመች የቀይ ዳማ እጅን በስልት ነካ። ‹‹ትንሽ ቆይተህ ጠጋ በይ ለማለት ነው ነቅቼብሃለሁ። ሥነ ሥርዓት ያዝ። ምነው ግን እንዲህ ሥርዓት አስከባሪ ጠፋ?›› ብላ ጮኸች። ወያላው በስጨት ብሎ፣ ‹‹ምን ስለሆንሽ ነው የማትጠጊው? ዘለዓለም ከአንቺ ጋር ድብድብ? ቆይ ለምን የእኔን ታክሲ መርጠሽ ትሳፈሪያለሽ?›› ብሎ ጮኸባት። የወያላውና የለግላጋዋ ትውውቅ የዛሬ ብቻ አይመስልም። ‹‹ማንነትን ትርፍ መሀል ምን አመጣው? ትርፍ መጫን ወንጀል ነው፤›› ብላ በስምንት ነጥብ ዘነጋችው። ‹‹አንተ በቃ ተዋት። የራስህ ጥፋት ነው። ገና በሩቁ ስታያት አልጭንሽም አትላትም? የዘሩን እሳት ሳናጠፋ ደግሞ በፆታ ልታሠልፈን ነው፤›› ብሎ ሾፌሩ መዓት ከወረደበት በኋላ ጋቢና ወደ ተሰየሙት ሹክክ ብሎ፣ ‹‹ይኼ ሁሉ ሰው ቆሞ በፀሐይ ሲቀቀል እያየች ምንም አይመስላትም ስልህ። እሷም እንዲችው ስትቀቀል ትውላታለች እንጂ ትርፍ ልጫንሽ ብትላት እሺ አትልም፤›› ይላል።
ይኼኔ ሰምታው፣ ‹‹ፀሐይ ብርቅ ነው ታዲያ? እንኳን የክረምቱን ፀሐይ ለበጋውም አልተበገርን፤›› ቱግ አለች። ‹‹ተረፋችኋ! እናንተ ስትተርፉ እኛ ምን እናድርግ?›› ወያላው የሚያቆም አይመስልም። አዛውንቷ ይኼኔ፣ ‹‹እባካችሁ ይብቃችሁ። አንቺም አንዴ አቋምሽ ታውቋል ዝም በይ። አንተም ገና ለገና በአገሩ አንድ ሰው ዘራፍ አለብኝ ብለህ አትወብራብን። መብቷ ነው። መደራረብ እኮ ለእኛም ቢሆን የውዴታ ግዴታ ሆኖብን እንጂ ፍላጎታችንም አይደለም። ዱላውን እስኪያቀብሉን ድረስ ማራቶኑን መቻል ነው። እንዲያው ሌላው ቀርቶ በአንድነት ስም ብላችሁ እስኪ ልብ ግዙ፤›› ብለው ውኃ ሲቸልሱበት ነገሩ በረደ። መትረፋችን ሳያንስ ትርፍ የምንነጋገረው ነገር ባሰን!
ጉዟችን ቀጥሏል። አዛውንቱ ገንዘብ ለመቀበል ከሄዱበት እየተመለሱ መሆናቸውን ያወራሉ። ጋቢና የተቀመጠ ደላላ አልሸጥ ስላለው ቤት እያነሳ፣ ‹‹ምነው ሰውን ነፈሰበት?›› ሲል እንሰማዋለን። ‹‹እንዴት አይነፍስበት በየሄደበት የሚያስተነፍሰው በዝቶ። ቢዝነሱ ሁሉ እኮ ሞተ…›› ይለኛል ከጎኔ። ‹‹ያለው ማማሩ የሌለው መደበሩ ሆነና አመዳሞች በዛን። ከብረት የተሠራን ይመስል እንዲህ የብረት ጨዋታ ሲበዛብንና ሲያገረጣን ግን አይገርምም? ብረት ነው አምላክ በአምሳሉ የሠራን ግን? ኧረ ጎበዝ በቸርነቱ እንጂ እኮ ዝገን አለቅን፤›› ሲል መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጠ ግምበኛ የሚመስል ታክሲያችን በሳቅ ተሞላች፡፡ ሾፌራችን ቦታ ይዞ ታክሲያችን ስትቆም ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው።
‹‹ገና ሩዋንዳን ሳናልፍ የምን መጨረሻ ነው?›› ብሎ ሰው ሲያፈጥበት፣ ‹‹በዩቲውብ ካልሆነ በቃ ቀልድ አልገባን አለ አይደል?›› ብሎ ተቅለሰለሰ። ይኼን ጊዜ በግል አውቶሞቢል ዘና ቀብረር ብለው ወደ ሚሄዱበት የሚያዘግሙትን ቦሌያውያንን እየታዘበ ከጎኔ ያለው፣ ‹‹ያለው ምን አለበት?›› ከማለቱ ጎልማሳ ተሳፋሪ፣ ‹‹ያለውማ ምን አለበት! የሌለው ነው እንጂ የሚያብላላበት። የሰው ከማየትና ከመመኘት የራሳችንን ኑሮ መኖሩ አይሻልም?›› አለው። ወጣቱ ‹‹መቼ ወደን ሆነ ወዳጄ? ቅድም አንዲት ልጅ ያለችኝ እየረበሸን እንጂ፤›› አለው። ‹‹ምንድን ነበር እሱ?›› ቢለው ጎልማሳው፣ ‹‹በማጭበርበርና በሌብነት እንደ ፊት ጎማ የሚያስተነፍሰን በዛ ስትል ሠልፉ ላይ አልነበርክም እንዴ?›› ብሎት ዝም አለ። ‹‹ዘመኑ የአቤል ይሁን የቃየል መለየት ከበደን እኮ? ወንድም በወንድሙ ዓይኑ ሲጠነቆል ጠብታ የሚያድል ይጠፋል? ይኼን ያህል ጆሮ ዳባ ልበስ ግን ያዛልቃል እንዴ?›› ሲል ተሳፋሪው በሆዱ የሰማው መስሎኝ ሥጋና መንፈስን ተጠራጠርኩ!
ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። በኅብረቱ መሪዎች መደበኛ ስብሰባ ሰበብ ቦሌን አመድ ወርሷታል። ይኼን አይቶ አንዱ፣ ‹‹ምንድነው እንዲህ ጭርታው? ትራምፕ ቦሌን ወደ አሜሪካ ግዛትነት ጠቀለሏት እንዴ?›› አለ። ‹‹ውይ? እንዲያው የዚህን ሰውዬ ስም የት አገር ይሆን የማልሰማው? ምናለበት ብትተውት። ከሰውዬው እብደት እኮ የእናንተ ማዳነቅ ባሰን። ለምን ስለጆርጅ ዊሐ አታወሩም?›› ትላለች ከወይዘሮዋ ጎን። ‹‹ኧረ እባክሽ ሴትዮ ቀስ በይ። ደግሞ ኢትዮጵያውያን ረሱኝ አሉኝ ብሎ እኛንም ‘ብላክ ሊስት’ ይክተተን እንዴ? አንድ ያለን ተስፋ ተሟጠጠ ማለት እኮ ነው። መቼም ሁላችንም እንደምንስማማው፣ ተስማምተንም እንደ ተረትነው ከአሜሪካና ከሞት መቅረት አንፈልግም፡፡ አይደለም እንዴ?›› ይላል ከኋላ ጥግ የተቀመጠው። ‹‹አይ የነፃነት ወሮታ። በቃ እኛ ቅኝ አልተገዛንምና ሰውዬው ሰሞኑን አፍሪካን ጠቅሎ የወቃበት ንግግር አይመለከተንም እያልክ ነው? ወይ ኅብረትና ነጠላነትን አለማወቅ?›› ሲል ከወደ ጋቢና አዛውንቱ፣ ‹‹ታመን እኮ ነው። ምን ይደረግ? ይልቅ ከሞትና ከአሜሪካ ላልከው ከሞትማ ወደድንም ጠላንም አንቀርም። ከአሜሪካ ግን እንጃ። ጊዜ የማያሳየን የለም። ብለን ብለን በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ይኼን ሰማን። እግዚኦ…›› ይላሉ አዛውንቱ።
‹‹አፍሪካን አሜሪካ ማድረግ ከቻልንስ? ያኔም መሄድ ያምረን ይሆን? ሲል አንዱ ከጋቢና፣ ተሳፋሪው በሙሉ መብረቅ እንዳደረቀው ዛፍ ንፍስ ሳይል ተያይቶ፣ ‹‹እሱማ በምን ዕድላችን?›› አለው። ‹‹እስኪ በዕድል የቆመች አገር ጥሩልኝ?›› ሲል መልሶ ወያላው አንባርቆ ‹‹መጨረሻ›› አለን። ዕድልና እውቀት እየተምታቱ እንዲህ ሲያስቸግሩ ምግባር የማያውቅ ወሬኛን ለመበተን ወያላችንን የመሰለ ገላጋይ ማግኘት ግድ ይላል። እንኳን አገር፣ እንኳን አኅጉር በምግባር የማይመራ እምነትም የመንግሥተ ሰማይ ዋስትና የለውማ። ምግባር ሲጎድል ሰብዓዊነት ይነጥፋል እንዲሉ፡፡ ከታክሲ ወርደን ወደ ጉዳዮቻችን ስናመራ አንዱ ‹‹ደመወዛችን ሃምሳ ችግራችን መቶ፤›› እያለ ሲጮህ ሌላው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹አትሥራና ችግርህን አስታም…›› ሲለው ወይዘሮዋ ቆጣ ብለው፣ ‹‹ልፋ ያለው ገለባ ይወቃል፤›› አሉ፡፡ እንግዲህ ሁሉም በመሰለው መንገድ የልቡን ይተነፍሳል፡፡ አንዳንዴማ ፀጥታውም ጩኸት ይመስላል፡፡ ንጭንጩ ደግሞ ብሷል፡፡ ግን የስንቱን ንጭንጭ ነው መስማት ያለብን? መልካም ጉዞ!